ለምን ኢትዮጵያዊያን ጥቂት ሥጋ ይመገባሉ?

ጥሬ ሥጋ Image copyright Getty Images

ኢትዮጵያዊያን የተለያየ አይነት ባሕላዊ ምግቦች ያሏቸው ሲሆን በተለይ ጥሬ ሥጋና ከሥጋ የሚሰሩ ምግቦች ጎልተው ይታያሉ፤ በዚህም በርካቶች ኢትዮጵያዊያን የሥጋ አዘውታሪዎች እንደሆኑ ይሰማቸዋል። ነገር ግን እውነታው ይህ አይደለም።

በቅርቡ የተደረገ አንድ ጥናት እንዳመለከተው ኢትዮጵያዊያን ዝቅተኛ መጠን ያለው ሥጋ ከሚመገቡ ዜጎች መካከል ቀዳሚዎቹ እንደሆነ አመልክቷል።

የተገኘው መረጃ እንደሚለው በመካከለኛ የኑሮ ደረጃ ላይ የሚገኙ ኢትዮጵያዊያን በዓመት 7 ኪሎግራም ሥጋ ብቻ ይመገባሉ። ይህ ደግሞ በአፍሪካ ደረጃ ሲታይ እንኳን በታችኛው ደረጃ ላይ የሚገኝ ነው።

ልጆችዎ ጤናማ ምግብ እንዲመገቡ ማድረጊያ መላዎች

ሩዋንዳዊያን 8 ኪሎ ግራም እንዲሁም የናይጄሪያ ዜጎች 9 ኪሎ ግራም ሥጋን ይመገባሉ። ጎረቤት የኬንያና የሱዳን ዜጎችም ከኢትዮጵያዊያን ከፍ ያለ የሥጋ መጠን እንደሚመገቡ ተጠቅሷል።

በመንግሥት ድርጅት ውስጥ ተቀጥረው የሚሰሩት 46 ዓመቱ ጎልማሳ አቶ መላኩ ጥላሁን አዘውትረው ሥጋን መመገብ ከሚፈልጉ ሰዎች መካከል መሆናቸውን ቢያምኑም በዋናነት የሥጋ ዋጋ መናር እንደፈለጉት እንዳይመገቡ እንዳገዳቸው ይናገራሉ።

"ጾም ካልሆነ በስተቀር በየእለቱ ሥጋ ብመገብ ደስ ይለኛል። ነገር ግን 200 እና 300 ብር ለአንድ ኪሎ እያወጡ መግዛት ለእንደ እኔ አይነቱ የወር ደሞዝተኛ አስቸጋሪ ነው" ይላሉ።

አቶ መላኩ አልፎ አልፎ አምሮታቸውን ለማስታገስ ሲሉ በጥቂቱ ሥጋ እንደሚገዙ ይናገራሉ። "በአብዛኛው ግን በበዓላት ሰሞን ነው የሥጋ አምሮቴን የምወጣው" ይላሉ።

ስለ አንጀታችን የማያውቋቸው ስድስት አስገራሚ እውነታዎች

አንዳንዶች ለጤንነታቸው ከሚያደርጉት ጥንቃቄ የተነሳ ለሥጋ ያላቸው ፍላጎት ዝቅተኛ በመሆኑ ከሥጋ ቢርቁም የዋጋው ውድነት በርካቶችን ከሥጋ እንዲርቁ አድጓቸዋል። ከዚህ አንጻር የአትክልትና የፍራፍሬ ዋጋ ዝቅተኛ መሆን ለጤና ብቻ ሳይሆን ከወጪ አኳያም ተመራጭ እየሆነ ነው።

የቤት እመቤት የሆኑት ወ/ሮ የማርሸት ጽጌ የሥጋ ዋጋ ከጊዜ ወደጊዜ እየተወደደ መሄዱ እንጂ ሥጋ ከቤተሰባቸው ማዕድ ላይ በየእለቱ ባይለይ ይመርጣሉ። "ለሥጋ የሚወጣው ወጪ ከሌሎች የምግብ ሸቀጦች አንጻር ከፍ ያለ በመሆኑ ለማብቃቃት ስል ከተቻለ በሳምንት አንድም ሁለትም ጊዜ ለቤተሰቤ ከሥጋ የተዘጋጀ ምግብ አቀርባለሁ" ይላሉ።

እንደ ወ/ሮ የማርሸት ሁሉ በርካታ ሰዎች አዘውትረው ሥጋ መብላትን ቢፈልጉም የዋጋው መናር እንዲሸሹት እንዳደረጋቸው ይናገራሉ። በአዲስ አበባ ውስጥ የሥጋ እንደየቦታው እና 'ጥራቱ' በተለያየ ዋጋ ለሽያጭ ይቀርባል። አንድ ኪሎ ሥጋ ከ150 ብር እሰከ 400 ብር የሚሸጥባቸው ቦታዎች አሉ።

ስለዚህም ለበርካቶች ከሥጋ መራቅ ዋነኛው ምክንያት የመግዛት አቅም እንደሆነ በርካቶች ይስማማሉ። የተደረገው ጥናትም በታዳጊ ሃገራት የሥጋ ፍጆታ ዝቅተኛ እንዲሆን ያደረገው የገቢ ጉዳይ ነው። በተጨማሪም የሥጋ ፍጆታቸው በጨመሩ ሃገራት ውስጥ የታየው እድገት ከገቢ ጋር እንሚያያዝ ይታመናል።

Image copyright Getty Images

ሥጋ በብዛት የሚበላባቸዉ ሀገራት

ይህ በተጨማሪ ጤናማ ለመሆን፣ አካባቢ ላይ ያላቸዉን ተፅዕኖ ለመቀነስ እና የእንስሳትን ደህንነት ለመጠበቅ ያላቸዉን ሚና ያሳያል።

ጥናቱ እንዳመለከተው 1/3ተኛ የሚሆኑ እንግሊዛዊያን ሥጋ መመገብን እንዳቆሙ ወይም እንደቀነሱ ሲናገሩ 2/3ተኛ የሚሆኑት አሜሪካዊያን ደግሞ ከአንድ ኪሎ ሥጋ በታች እንደሚመገቡ ይናገራሉ።

ባለፉት 50 ዓመታት የሥጋ ፍጆታ በፍጥነት አድጓል፤ በምርት በኩልም ዛሬ የሥጋ ምርት በ1960ዎቹ ከሚመረተው አምስት እጥፍ አካባቢ ጨምሯል።

የአለም የምግብ ቀን: አስገራሚ የአለማችን ምግቦች

በዚህ ጊዜ ዉስጥም የህዝብ ቁጥር ከእጥፍ በላይ አድጓል። ነገር ግን ይህ ብቻ ለሥጋ ፍጆታ መጨመር በቂ ምክንያት አይደለም።ሌላኛዉ ምክንያት የሰዎች ገቢ መጨመር እንደሆነ ይታመናል።

የተለያዩ የዓለም ሀገራት የሥጋ ፍጆታ ሲወዳደር ሀብታም የሆኑት ሀገራት የበለጠ ሥጋ እንደሚጠቀሙ ያሳያል። ይህም በዓለማችን የህዝብ ቁጥር መጨመር ብቻ ሳይሆን ሰዎች ሥጋን የመግዛት አቅም መጨመርም ለፍጆታ መጨመር ምክንያት ነዉ።

ብዙ ጋ የሚበላዉ ማን ነዉ?

በዓለም ላይ ያለውን ሥጋን የመመገብ ልምድ ስንመለከት ከሃብት ጋር ከፍተኛ ቁርኝት ኖሮት እናገኘዋለን። በዚህም በበለፀገው የምዕራቡ ዓለም ሥጋ በከፍተኛ ሁኔታ ይበላል። በብዙዎቹ ምዕራብ አውሮፓ ሀገራት አንድ ሰዉ ከ80 እስከ 90 ኪሎ ሥጋ በዓመት ይመገባል።

በተቃራኒዉ የድሃ ሀገራት ዜጎች እጅግ አነስተኛ መጠን ያለው ሥጋ ይመገባሉ። ኢትዮጵያዊያንም ከዚሁ ምድብ ውስጥ የሚካተቱ ሲሆን በአማካይ አንድ ኢትዮጵያዊ 7 ኪሎ ግራም ብቻ ይመገባሉ። ይህ ማለት ደግሞ አሃዙ አንድ አዉሮፓዊ ከሚመገበው የሥጋ መጠን በአስር እጥፍ ያንሳል።

የመከለኛ ገቢ ሃገራት የስጋ ፍላጎት መጨመር

የዓለማችን ሃብታም ሃገራት ነዋሪዎች ከፍተኛ መጠን ያለው ሥጋ ሲመገቡ ዝቅተኛ ገቢ ያላቸዉ ሀገራት ደግሞ አነስተኛ የሥጋ ይመገባሉ። ይህ ላለፉት 50 ዓመታት የቀጠለ ሲሆን አሁን ግን መጠኑ እየጨመረ እንደሆነ ይታመናል። ለዚህ ምክንያቱ የመካከለኛ ገቢ ሃገራት ቁጥር መጨመር ነዉ።

ባለፉት 10 ዓመታት ፈጣን የሆነ የኢኮኖሚ እድገት ያሳዩ ሀገራት እንደ የቻይና እና የብራዚል ዜጎች በመጠኑ ከፍተኛ የሆነ ሥጋን እየተመገቡ ነው።

ቁርስ የቀኑ እጅግ አስፈላጊ ምግብ ነውን?

በኬንያ የሥጋ ፍጆታ ላለፉት 50 ዓመታት በጣም በትንሹ የተለወጠ ሲሆን በተቃራኒዉ ግን በቻይና በ1960 በአማካኝ በዓመት ከ5 ኪሎ በታች ይመገብ የነበረ ሰው በመጨረሻዎቹ 1980 መጠኑ ወደ 20 ኪሎ አድጓል። በተጨማሪም ላለፉት ጥቂት አስርት ዓመታት ከ3 እጥፍ በላይ አድጎ ወደ 60 ኪሎ ግራም ደርሷል።

በተመሳሳይ መልኩ በብራዚል የሥጋ ፍጆታ ብዙዎቹን አዉሮፓ አገራት በመብለጥ ከ1990ዎቹ ከጥፍ በላይ አድጓል።

የሥጋ ፍጆታ በምዕራቡ ዓለም እየቀነሰ ነዉ ወይስ?

ብዙ አውሮፓዉያን እና አሜሪካውያን የሚመገቡትን የሥጋ መጠን ለመቀነስ እየሞከርን ነው ይላሉ። ነገር ግን ውጤቱ ይህን አያመለክትም።

በቅርቡ የአሜሪካ የግብርና መስሪያ ቤት እንዳወጣው መረጃ ከሆነ የአንድ ሰው የሥጋ ፍጆታ ላለፉት ጥቂት ዓመታት ጭማሪ አሳይቷል።

የምዕራቡ ዓለም ነዋሪዎች የሚጠቀሙት የሥጋ መጠን በትንሹ ጭማሪ ቢያሳይም የሚመገቡት የሥጋ አይነት ግን ለውጥ ይታይበታል። የአእዋፋት የሥጋ ውጤቶች መጨመር ሲያሳይ የበሬ እና የአሳማ ሥጋ አጠቃቀም ግን ቅናሽ አሳይቷል።

የሥጋ ተፅእኖ በአካባቢ ላይ

የተመጣጠነ የሥጋ እና የወተት ውጤቶችን መጠቀም የሰዎችን ጤና ያሻሽላል። በተለይ አነስተኛ ገቢ ላላቸዉ ሀገራት ነዋሪዎች ጠቀሜታቸዉ የላቀ ነው ምክንያቱ ደግሞ የተለያዩ አይነት ተመጣጣኝ ምግቦች ስለማያገኙ ነው።

ነገር ግን ከመጠኑ ያለፈ ቀይ ሥጋን መመገብ ለልብ፣ ለስትሮክ እና ለካንሰር በሽታዎች ያጋልጣል።

የዶሮ ሥጋን በቀይ ስጋ ምትክ መመገብ በጎ ምርጫ ነው። ይህ ለውጥም ለተፈጥሮ አካባቢ ደህንነት እጅጉን ይጠቅማል። ከብቶች የሚመገቡትን መኖ ወደ ሥጋ በመቀየር ረገድ የሌሎቹን እንስሳት ያህል ብቁ አይደሉም።

አመጋገባችን ማረጥን ሊያፋጥን ወይም ሊያዘገይ ይችላል

ከብቶች ከዶሮዎች አንፃር ከ3 እስከ 10 እጥፍ የመሬት፣ ውሃ እና አካባቢን የሚበክል ጋዝ ልቀት ላይ አስተዋፅኦ አላቸው። አሳማዎች ደግሞ ከሁለቱ መሃል ላይ የመደባሉ።

ለወደፊቱ የተመጣጠነና አስተማማኝ የሆነ የሥጋ አጠቃቀምን በሀገሮች መካከል ለመፍጠር በጥቂት የማይባሉ ለውጦች ያስፈልጋሉ፤ ይህም የምንመገበውን የሥጋ አይነት መቀየር ብቻ ሳይሆን መጠኑንም መቀነስ ያካትታል ተብሏል።