አሳሳቢ እየሆኑ የመጡት አዳዲሶቹ የአባላዘር በሽታዎች

ከወገብ በታች የሚታይ ወንድ Image copyright iStock
አጭር የምስል መግለጫ አዳዲስ የአባላዘር በሽታዎች አሳሳቢ እየሆኑ ነው

በግብረ ሥጋ ግንኙነት የሚተላለፉ በሽታዎችን ጨምሮ በዓለማችን በተለያዩ ጊዜያት አዳዲስ በሽታዎች ይከሰታሉ።

ለሕብረተሰብ ጤና እጅግ አደገኛ ስጋት ሊሆኑ ይችላሉ ከሚባሉት መካከል በግብረ ሥጋ ግንኙነት የሚተላለፉት በሽታዎች መካከል አዲስ ክስተት እየሆኑ ናቸው ስለሚባሉት አራት የጤና ችግሮች እንንገራችሁ።

1. ኔይሴሪያ ሜኒንጃይቲዲስ

Image copyright iStock
አጭር የምስል መግለጫ ኔይሴሪያ ሜኒንጃይቲዲስ አደገኛ ሲሆን በተለይ አንጎልንና የአከርካሪ ሽፋንን ያጠቃል

ይህ ኔይሴሪያ ሜኒንጃይቲዲስ በአብዛኛው ሜኒንጎኮከስ እየተባለ የሚጠቀስ ሲሆን በቀላሉ የሚስፋፋ የማጅራት ገትር አይነት ነው። በሽታው አደገኛ ሲሆን በተለይ አንጎልንና የአከርካሪ ሽፋንን በማጥቃት እስከሞት ሊያደርስ ይችላል።

ጋናውያኑን ያስቆጣው የስነ ወሲብ ትምህርት

ስለ ወሲብ እንዲያስቡ የማይፈቀድላቸው ኢራናውያን

በአብዛኛው እየታወቀ የመጣው የሽንት ቧንቧና የመራቢያ አካላት ኢንፌክሽን ተብሎ ነው። የበሽታው ባክቴሪያ በንክኪ ጭምር ሊተላለፍ የሚችል እንደሆነ ይነገራል።

ከአምስት አስከ አስር በመቶ በሚጠጉ ጎልማሶች አፍንጫና ጉሮሮ ውስጥ የኔይሴሪያ ሜኒንጃይቲዲስ ባክቴሪያ ስለሚገኝ በግብረ ሥጋ ግንኙነት፣ በመሳሳም እንዲሁም በሽታውን ሊያስተላልፉ በሚችሉ ከሰውነት በሚወጡ ፈሳሾች አማካይነት ይተላለፋል።

ከአራት ዓመት በፊት በበርካታ የአሜሪካ ከተሞች የተከሰተው ይህ በሽታ የቅርብ ተዛማጁ ከሆነው ጨብጥን ከሚያመጣው ባክቴሪያ የዘር ቅንጣት ጋር በመዋሃድ መከሰቱን ሳይንቲስቶች ገልጸዋል።

ይህ ሽግግር በግብረ ሥጋ ግንኙነት የሚተላለፈውን ይህን በሽታ በአደገኛ ሁኔታ እንዲስፋፋ አድርጎታል።

አምስት አይነት የኔይሴሪያ ሜኒንጃይቲዲስ በዓለም ዙሪያ እየተከሰቱ ላሉት አብዛኞቹ ወረርሽኞች ምክንያት ናቸው። ጥሩው ነገር ደግሞ አምስቱን የበሽታው አይነቶች የሚከላከሉ ሁለት ክትባቶች አሉ።

2. ማይኮፕላዝማ ጄኒታሊየም

Image copyright iStock
አጭር የምስል መግለጫ ማይኮፕላዝማ ጄኒታሊየም በሴቶች ላይ አደገኛ ነው

በጣም ትንሽ ከሆኑት ባክቴሪያዎች መካከል የሚመደበው ማይኮፕላዝማ ጄኒታሊየም ከመጠኑ በላይ እጅግ አሳሳቢ እየሆነ የመጣ በግብረ ሥጋ ግንኙነት የሚተላለፍ በሽታ ሆኗል።

በ1980ዎቹ የታወቀው ይህ በሽታ በአሁኑ ጊዜ ከአንድ እስከ ሁለት በመቶ የሚሆኑ በተለይ ወጣቶችና ጎልማሶች ላይ በስፋት ይስተዋላል።

ማይኮፕላዝማ ጄኒታሊየም በአብዛኛው የህመም ምልክቶች የማይታዩበት ሲሆን አንዳንድ ጊዜ በሽንት ቧንቧ አካባቢ የሚሰማ የማይመች ስሜት ከሌሎች የአባላዘር በሽታዎች ጋር ያመሳስለዋል።

ኃይል የተቀላቀለበት ወሲብ መፈጸም ''እየተለመደ መጥቷል''

በሽታው በመራቢያ ክፍሎች ላይ በሚያስከትለው አሉታዊ ውጤት ምክንያት ከመሃንነት፣ ከጽንስ መቋረጥ፣ ከጊዜ በፊት የሚከሰት ወሊድ እና ከመሰል ችግሮች ጋር ይያያዛል።

ኮንዶም መጠቀም በበሽታው ከመያዝ የሚከላከል ሲሆን፤ አጥኚዎች ይህ በሽታ አንቲባዮቲክ መድሃኒቶችን የመላመድ ባህሪን እያዳበረ በመሆኑ አሳሳቢ እንደሚሆን ማስጠንቀቂያ እየሰጡ ነው።

"የሚያሳስበኝ ይህ በሽታ መድሃኒት የመቋቋም አቅሙ እየተጠናከረ መምጣቱና መስፋፋቱ ነው" ያሉት አሜሪካ ውስጥ የሚገኝ የአንድ የጤና ተቋም ዳይሬክተር የሆኑት ማቲው ጎልደን ናቸው።

የከፋ ጉዳት ሊያደርስ የሚችልን የማይኮፕላዝማ ጄኒታሊየምን ተህዋስ አይነት መፈጠርን ለመከላከል ተጨማሪ ምርመራ በጣም አስፋለጊ እንደሆነም ተነግሯል።

3. ሺጌላ ፍሌክስኔሪ

Image copyright iStock
አጭር የምስል መግለጫ ሺጌላ የሆድ ቁርጠትና ደም የቀላቀለ አሰጨናቂ ተቅማጥን ያስከትላል

ሺጌሎሲስ (ወይም የሺጌላ ተቅማጥ) በመባል የሚታወቀው በሽታ የሚተላለፈው ከሰው ልጅ አይነ ምድር ጋር በቀጥታም ሆነ በተዘዋዋሪ በሚኖር ንክኪ ነው።

በሽታው ከባድ የሚባል የሆድ ቁርጠትና ደም የቀላቀለ አሰጨናቂ ተቅማጥን ያስከትላል፤ በዚህም በሽታው ከሰው ወደ ሰው በቀላሉ እንዲተላለፍ እድል ያገኛል።

ምንም እንኳን ይህ በሽታ ዝቅተኛና መካከለኛ ገቢ ባለቸው አገራት ውስጥ ባሉ ተደጋጋሚ ጉዞ በሚያደርጉና በታዳጊ ልጆች ላይ በስፋት የሚስተዋል ቢሆንም፤ በ1970ዎቹ አጥኚዎች የተመሳሳይ ጾታ ግንኙነት ውስጥ ባሉ ሰዎች ላይም እንደሚታይ መዝግበዋል።

ኢንተርኔትን የሚሾፍረው የወሲብ ፊልም ይሆን?

በኒውዮርክ ከተማ የጤና ጉዳዮች ባለስልጣን ከሆኑት መካከል አንዱ ዲሜትሪ ዳስካላኪስ ስለሺጌሎሲስ አደገኛ እየሆነ መምጣት ሲናገሩ፤ ይህ በግብረ ሥጋ ግንኙነት የሚተላለፈው በሽታ ጨብጥን ለማከም ጥቅም ላይ የሚውለውን አዚትሮማይሲን የተባለውን መድሃኒት እየተላመደው ነው።

የሕዝብ ጤና ተቋማት ይህ በሽታ ከራሱ አልፎ አደገኛ አይነት ጨብጥ እንዲፈጠር ሊያደርግ ይችላል የሚል ስጋት አላቸው። በብዙ ቦታዎችም ለየት ያለ የማከም ዘዴ እየተተገበረ መሆኑም ተነግሯል።

4. ሊምፎግራኑሎማ ቬኔሩም (ኤልጂቪ)

Image copyright iStock
አጭር የምስል መግለጫ አብዛኛዎቹን የአባላዘር በሽታዎች ኮንዶም በመጠቀም መከላከል ይቻላል

ይህ በግብረ ሥጋ ግንኙነት የሚተላለፍ በሽታ የሚታወቀው በክላይሜዲያ ትራኮማሲስ ዝርያ አማካይነት የሚመጣ ሲሆን "እጅግ የከፋ ህመምን ሊያስከትል ይችላል" ሲሉ የሳን ፍራንሲስኮው ዶክተር ክሪስቶፈር ስኪዝል ይናገራሉ።

በሽታው በመጀመሪያ ላይ በብልት አካባቢ ጊዜያዊ እብጠት፣ ውሃ መቋጠር ወይም መድማት ካጋጠመ በኋላ የሰውነታችንን የሊምፍ ሥርዓት በመውረር ያጠቃል። በሽታው ፊንጢጣንና የመጸዳጃ አካል ላይ እብጠትና የከፋ ህመምን በማስከተል ፊስቱላን የመሰለ ሌሎች ችግሮችንም ያመጣል።

ባለፉት አስር ዓመታት ሊምፎግራኑሎማ ቬኔሩም በአውሮፓና በሰሜን አሜሪካ ውስጥ በስፋት የሚታይ በሽታ ሲሆን፤ በተለይ የተመሳሳይ ጾታ ግንኙነት በሚፈጽሙ ሰዎች መካከል በሚከሰቱ የተለያዩ ወረርሽኞች ጋርም ሲዛመድ ቆይቷል።

ወንዶች፤ የወሊድ መቆጣጠሪያ ክኒና ለመዋጥ ዝግጁ ናችሁ?

ከክላይሜዲያ ጋር ተያይዞ እንደሚከሰተው ሊምፎግራኑሎማ ቬኔሩም የሰዎችን በኤችአይቪ የመያዝ አጋጣሚን ይጨምረዋል።

ምንጊዜም በተገቢው ሁኔታ ኮንዶም መጠቀም በበሽታው የመያዝ ስጋትን የሚቀንስ ሲሆን፤ በሊምፎግራኑሎማ ቬኔሩም የተያዙ ሰዎች ታከመው ለመዳን ለሦስት ሳምንታት የሚሰጠውን የጸረ ተህዋያን መድሃኒትን መውሰድ ይኖርባቸዋል።

በዚህ ዘገባ ላይ ተጨማሪ መረጃ