ሜድ ኢን ቻይና- የሀገር ባህል አልባሳቶቻችን

የቻይና ዓይን ያረፈበት ባህል ልብሳችን

የቻይና እጅ ሽሮ ሜዳ ድርሷል፤ እርግጥ ነው የቻይና እጅ ያልገባበት የለም። አዲስ አበባን ዞር ዞር ብሎ ለቃኘ ቻይናውያን ከዚህ በፊት ያልመድናቸውን ተግባራት ሲፈፅሙ ማየት አዲስ አይሆንበትም።

የባህል ልብስ ውበት ነው፤ የባህል ልብስ 'ባህል' ነው፤ በዓል ነው፤ መለያም ጭምር። እኒህ አልባሳት በባህላዊ መንገድ ተሠርተው ከአራቱም የሃገሪቱ ማዕዘናት ጉዟቸውን ወደ አዲስ አበባ፤ በተለይ ደግሞ ሽሮ ሜዳ ያደርጋሉ።

አሁን አሁን ግን አደጋ የተጋረጠባቸው ይመስላል። ቻይና ውስጥ ተሠርተው የሚመጡ ጨርቆች ገበያውን መቀላቀል ከጀመሩ ሰንበትበት ብለዋል።

አቤል ብርሃኑ ሽሮ ሜዳ ግድም አንዲት የባህል አልባሳት መሸጫ ሱቅ አለችው። ገበያ ነውና ቱባውንም ይሁን የቻይና እጅ ያረፈባቸውን አልባሳትን ይሸጣል።

የኑሮ ነገር

«በሃገራችን እጅ የተሠራውን አንድም ሳልሸጥ የምውልበት ቀን በርካታ ነው፤ ነገር ግን ቻይና ሰራሹን በቀን እስከ 30 ድረስ ልሸጥ እችላለሁ» ሲል አቤል የገበያ ውሎውን ይናገራል።

ለዚህ ደግሞ ዋነኛው ምክንያት የዋጋ ልዩነቱ ነው፤ የቻይናው ከ400 ብር ጀምሮ ሲገኝ በሃገር ልጅ እጅ የተሠራው ከ2000 ብር አንስቶ እስከ አሰራዎቹ ድረስ ሊሸመት ይችላል።

ሌሎችም ሽሮ ሜዳ አካባቢ ያሉ መሰል አልባሳትን የሚሸጡ ነጋዴዎች የሚሉት ይህንን ነው። በሸማኔ ከሚሠራው የባህል ልብስ ይልቅ እየተቸበቸበ ያለው በማሽን ታትሞ በርካሽ ዋጋ ለገበያ የሚቀርበው የቻይና እጅ ያረፈበት ልብስ ነው።

የቱባውን ባህላዊ ልብስ ክብር የሚያውቅና አቅሙ ያለው ብቻ በሺህ ቤቶች አውጥቶ እንደሚገዛ አቤል ምስክርነቱን ይሰጣል።

ወደ ኤግዚቢሽን ማዕከል. . .

ዕለተ አርብ ነበር 10ኛው ከተማ አቀፍ የባህል ቀን በኤግዚቢሽን ማዕከል የተዘከረው፤ በርካታ ባህላዊ ልብሶችን የሚሸጡ ነጋዴዎች በተገኙበት።

ደርጉ ደሌ ሸማኔ ነው፤ ከባልደረባው ጋር በመሆን ትርዒቱ ላይ የሽመና ሥራን ለማስተዋወቅ ነበር ኤግዚብሽን ማዕከል የተገኘው።

«በሸማኔ የሚሠሩ ባህላዊ ልብሶች ብዙ ውጣ ውረድ አልፈው ነው እዚህ የሚደርሱት። ከጥጥ ማምረት ጀምሮ፤ መፍተል እንዲሁም ከሳባ ወይም ከመነን ጨርቅ ጋር አስማምቶ መሸመን ትልቅ ጥበብ ነው፤ አድካሚም ነው» ይላል።

የቻይኖቹ ነገርስ?. . .«በጣም ፈተና የሆነብን ነገር ነው» ይላል ደርጉ። «የቻይናዎቹ አቡጀዲ ጨርቅ ላይ እነሱ ያተሙት ጥለት መሰል ጨርቅ ይለጠፍበታል። ለመሥራት በጣም ቀላል ነው። ለዚያ ነው በርካሽ ዋጋ የሚሸጠው።»

አቤልም በዚህ ይስማማል። «ይሄ አሁን ለምሣሌ. . .» ይላል ከተንጠለጠሉት ቻይና ሠራሽ ልብሶች ወደ አንዱ በመጠቆም። «ይሄ አሁን ለምሳሌ 'ልጥፍ' ይባላል። አቡጀዲ ጨርቅ ነው። ከዚያ በቻይናዎች ማሽን የታተመ ጥለት መሳይ ነገር ይለጠፍበታል።»

ፋና የባህል ልብስ መሸጫ ሱቅ አላት። ቱባ ምርቶቿን ማስተዋወቅ ያመቻት ዘንድ ነው ኤግዚቢሽኑ ላይ የተገኘችው።

«እኔ የምሸጣቸውን ልብሶች የማሠራው በሸማኔ ነው» ትላለች። ነገር ግን የቻይና እጅ አርፎባቸው በረከሰ ዋጋ ገበያውን ያንበሸበሹት አልባሳት ጉዳይ ሳያስጨንቃት አልቀረም።

«እኛ ትክክለኛውን እና ባህሉን የጠበቀውን ልብስ ወደ ገበያ ለማቅረብ ብዙ ነገር እናደርጋለን፤ ወጪውም ቀላል አይደለም። ነገር ግን አሁን አሁን ገበያ ላይ የሚታዩ የቻይና እጅ ያረፈባቸው ጨርቆች ጉዳይ እጅግ ሞራልን የሚነካ ነው።»

የሃገራችንን ባህላዊ ጥለት መስለው በማሽን የሚታተሙት ጨርቆች ግማሾቹ ከቻይና ተመርተው እንደሚመጡ፤ ኢትዮጵያ ውስጥም የሚመረቱ እንዳሉ የሽሮ ሜዳ ሰዎች ይናገራሉ።

መርካቶ ውስጥ በጣቃ መልክ መጥተው በሜትር እንደሚሸጡም ነው ነጋዴዎቹ የሚያስረዱት። ቢቢሲ እንደታዘበውም አንዳድንድ ቦታ ጨርቆቹ በመጋረጃ መልክ ተሰቅለው ይታያሉ።

የተቆጣጣሪ ያለህ

በአዲስ አበባ ከተማ መስተዳድር የቱሪዝም ቢሮ የባህል፣ እሴቶች እና ኢንዱስትሪ ልማት ዳይሬክተር የሆኑት ወ/ሮ አዳነች ካሳ ቢሯቸው «ሁኔታውን እየተከታተለው እንደሆነ» ይናገራሉ።

ነጋዴዎች ግን ግብር ለማስከፈል በየወቅቱ ከሚጎበኟቸው የመንግሥት ሰዎች በዘለለ የቻይና እጅ መርዘምን ተመልክቶ በጀ ያላቸው ማንም ሰው እንደሌለ ያስረዳሉ።

«እኔ እስከማውቀው ድረስ ማንም ሰው መጥቶ አላነጋገረንም፤ የሚመለከተው የሚባለው የመንግሥት አካል ቢመጣ እንኳ የቻይናውን ገዝቶ ይሄዳል እንጂ (ሳቅ) ነገሩ ሲገደው አላየሁም» ይላል አቤል።

የሽማና ሙያተኛው ደርጉም ማንም ወደ ሽሮ ሜዳ ብቅ ብሎ 'የቻይናን ነገር ለእኔ ተዉት' ያለ የመንግሥትም ሆነ በግሉ የሚንቀሳቀስ ሰው እንዳላጋጠመው አውግቶናል።

ወ/ሮ አዳነች ግን ዋናው የጉዳዩ ተባባሪ ሕብረተሠቡ እንደሆነ ያስረግጣሉ። «ይህ ጉዳይ የአዲስ አበባ ከተማ ብቻ አይደለም። በፌዴራል ደረጃም ሊታይ የሚገባው ነው። እኛ ከሚዲያውም ጋር ሆነ ከሚመለከታቸው ጋር ለመሥራት ዝግጁ ነን። ነገር ግን ዋናው ተዋናይ ሕብረተሰቡ ነው። ሕዝቡ አይሆንም ካለ፤ እኒህ የቻይና ጨርቆች ከገበያ የማይወጡበት ምክንያት የለም» ይላሉ።

ያም ሆነ ይህ የቻይና እጅ ሽሮ ሜዳ መድረስ ግድ ሊለን የሚገባ ይመስላል። በጥንቃቄ ካልተያዘ ዘመናዊነት ይዞ የሚመጣው ለውጥ መልካም የባህል እሴትን ሊያጠፋ እንደሚችል የሁሉም ስጋት ነው።

በሽመና ባለሙያዎች ጥበብ አምረው የሚሰሩት ባሕላዊ አልባሰት በቻይናዊያን ታትመው ከሚመጡት ጋር ተወዳድሮ ገበያ ውስጥ መዝለቁ እያነጋገረ ነው።