በኢትዮጵያ 6 የካንሰር ሕክምና ማዕከላት በቅርቡ አገልግሎት ይጀምራሉ

የጡት ካንሰር መለያ ሪባን

በኢትዮጵያ በየዓመቱ በርካታ ሰዎች በካንሰር እንደሚያዙ የፌደራል ጤና ጥበቃ ሚኒስቴር መረጃ ያሳያል። ከዚህ ውስጥ በከፍተኛ ቁጥር ተጠቂ የሆኑት ደግሞ ሴቶች ናቸው።

በዚህም በዓመት ውስጥ ከ60 እስከ 70 ሺህ የሚሆኑ ሰዎች በተለያዩ የካንሰር አይነቶች እንደሚያዙ ባለፉት ሁለት ዓመታት በጤና ጥበቃ ሚኒስቴር የተደረገው ጥናት ያመለክታል።

አስጊነቱ እየጨመረ ያለው ካንሰር

ከእነዚህም መካከል 67 በመቶ የሚሆኑት ሴቶች ሲሆኑ፤ የጡት ካንሰርና የማህፀን ካንሰር ደግሞ ሰፊውን ድርሻ እንደሚይዙ የጤና ጥበቃ ሚኒስቴር ሚኒስትር ዲኤታ ዶክትር ሊያ ታደሰ ይናገራሉ።

ከዚህ ቀደም የተደረጉ ጥናቶች በቂ ባይሆኑም የህፃናት ካንሰርም በተለይ የደም ካንሰር፣ የኩላሊት እንዲሁም የጭንቅላት ካንሰር ዓይነቶች በህክምና ተቋማት በስፋት እንደሚታዩ ይናገራሉ።

"የህፃናት ካንሰር በተለያየ ህክምና እስከ 80 በመቶ የመዳን እድል አለው" የሚሉት ዶ/ር ሊያ ችግሮቹ በጊዜ ስለማይታወቅና በአገር ውስጥ በቂ ህክምና ባለመኖሩ የመዳን እድላቸው ዝቅተኛ እንዲሆን አድርጎታል ይላሉ።

የማቲዎስ ወንዱ የኢትዮጵያ ካንሰር ሶሳይቲ ዋና ሥራ አስፈፃሚ አቶ ወንዱ በቀለ ደግሞ "በሃገራችን የካንሰር ጉዳይ ተዘንግቷል" ይላሉ።

"የካንሰር ህክምና ባለሙያዎች እጥረት አለ፤ በአገር አቀፍ ደረጃ ሦስት ወይም አራት የካንሰር ስፔሻሊስት ብቻ ናቸው ያሉት። ሁለቱ ደግሞ የሚገኙት ጥቁር አንበሳ ሆስፒታል ነው፤ መድሃኒቱም ተሟልቶ አይቀርብም" ይላሉ።

ይሁን እንጂ አሁን አሁን ቀደም ካሉት ጊዜያት በተሻለ ሁኔታ ችግሮቹን ለማቃለል ከጤና ጥበቃ ሚኒስቴር ጋር እየሰሩ መሆናቸውን አቶ ወንዱ ያስረዳሉ።

የህፃናት ካንሰር አስቀድሞ ለመከላከል አስቸጋሪ ቢሆንም ቶሎ ከተገኘና ህክምናው በጊዜው ከተጀመረ የመዳን እድላቸው በጣም ከፍተኛ ቢሆንም ቶሎ ወደ ህክምና ተቋም ይዞ መሄድ በአገሪቱ አለመለመዱ ችግሩን ያባብሰዋል ብለዋል።

ብክለት የዓለምን ድሃ ህዝብ እየጨረሰ ነው?

አቶ ወንዱ አክለውም ህሙማን ወደ ህክምና ተቋምም ከሄዱ በኋላ የመድሃኒቶች ተሟልቶ አለመገኘትና የባለሙያዎች አለመኖር የሚፈለገውን ያህል ህክምናው ውጤታማ እንደማይሆን የግብፅና የደቡብ አፍሪካን ተሞክሮ በማንሳት ይናገራሉ።

በኢትዮጵያ በአሁኑ ወቅት ያለው የካንሰር ሥርጭት መጠን ቀደም ሲል ከነበረው ጋር ሲነጻጸር ጨምሯል ወይም ቀንሷል ለማለት ቀድሞ የተካሄደው ጥናት በቂ ስላልነበር ለመናገር እንደሚቸገሩ የሚናገሩት ዶ/ር ሊያ ነገር ግን "ቁጥሩ ከጊዜ ወደ ጊዜ እየጨመረ እንደመጣ ይገማታል" ብለዋል።

በሴቶች ላይ ከሚከሰቱ የካንሰር አይነቶች ውስጥ የጡት ካንሰር ቀዳሚውን ደረጃ ሲይዝ የማህፀን ካንሰር ይከተለዋል፤ እንቁላል የሚመረትበት የማህፀን ክፍል (እንቁልጢ) ካንሰርም በሦስተኛ ደረጃነት ተጠቅሷል።

የትልቁና የትንሹ አንጀት ካንሰር በወንዶች ላይ በስፋት የሚከሰት ሲሆን፤ ምንም እንኳን ከዕድሜ ጋር ተያይዞ የሚመጣ ቢሆንም የዘር ፍሬ ካንሰርም ስርጭቱ ቀላል አይደለም።

የደም ካንሰር የሚያጋጥማቸው ሰዎች ቁጥርም ቀላል የሚባል እንዳልሆነ ዶክተር ሊያ ይናገራሉ።

"ወንዶች በጡት ካንሠር እንደሚያዙ አላውቅም ነበር"

"ካንሰር ከተማ በሽታ ብቻ አይደለም" የሚሉት ሚኒስቴር ዲኤታዋ በገጠር አካባቢ ያለው የኑሮ ዘይቤም እየተቀየረ በመምጣቱ የካንሰር ሥርጭት ዝቅተኛ ነው የሚባል አይደለም ብለዋል።

የአመጋገብ ሁኔታም ከካንሰር ክስተት ጋር ተያያዥነት ሊኖረው ይችላል የሚሉት ዶ/ር ሊያ "በገጠር አካባቢ የሚኖሩ ሰዎችም በብዛት ባይሆንም በፋብሪካ የተመረቱ ምግቦችን ወደ መመገብ እያዘነበሉ መሆኑ ተጋላጭነታቸውን ከፍ እያደረገው ነው" ይላሉ።

ይሁን እንጂ የበሽታው ሥርጭት ሰፊ ቢሆንም በአገር አቀፍ ደረጃ የካንሰር ህክምና ሙሉ በሙሉ የሚሰጠው በጥቁር አንበሳ ሆስፒታል ውስጥ ብቻ መሆኑ ችግሩን ያጎላዋል።

ለዚህም "የተሟላ የካንሰር ህክምናን ለማስፋፋት ጥቁር አንበሳን ጨምሮ ስድስት በክልሎች ያሉ የዩኒቨርሲቲ ሆስፒታሎች የካንሰር ህክምና ማዕከል እንዲኖራቸው እየተሰራ መሆኑንና በስድስት ወር ውስጥ ሥራ ይጀምራሉ ተብሎ ይጠበቃል" ሲሉ ዶ/ር ሊያ ጨምረው ተናግረዋል።

በተለይ በሴቶች ላይ በስፋት የሚታየውን የማህፀን በር ካንሰርን ቀድሞ ለመከላከል ልጃገረዶች የግብረ ሥጋ ግንኙነት ከመጀመራቸው በፊት ክትባት እየተሰጠ መሆኑንም ጠቅሰዋል።

ይህን ክትባት ያገኙ ሴቶች ለማህጸን በር ካንሰር የመጋለጥ እድላቸውን 70 በመቶ ስለሚቀንስ "እድሜያቸው 14 ዓመት ለሞላቸው ሴት ተማሪዎች እየተሰጠ ይገኛል። እስካሁን 1.1 ሚሊዮን የሚሆኑ ልጃገረዶች የመጀመሪያውን ዙር ክትባት ተከትበዋል" ብለዋል ዶ/ር ሊያ።

ካንሰርን ለመከላከል ከህክምናው ባሻገር የተለያዩ ጥረቶች እየተደረጉ ሲሆን በከተሞች ከተሽከርካሪ ፍሰት ነፃ ቀን እንዲሁም በቅርቡ በአልኮል መጠጦች ላይ በሚኒስትሮች ምክር ቤት የፀደቀው ረቂቅ አዋጅ ካንሰርን ቀድሞ ለመከላከል እየተወሰዱ ካሉ እርምጃዎች መካከል የተወሰኑትን ጠቅሰዋል።

ተያያዥ ርዕሶች

በዚህ ዘገባ ላይ ተጨማሪ መረጃ