በአማራ ክልል 5685 የጋብቻ ጥያቄዎች በዕድሜ ምክንያት ዉድቅ ተደርገዋል

ያለ ዕድሜ ጋብቻ Image copyright Eric Lafforgue/Art in All of Us

በቅርቡ በማህበራዊ ሚዲያ ላይ የ 14 አመት ታዳጊ ልጅ የባህል ልብስ ለብሳ በዕድሜ ትልቅ ከሆነ ሰው ጋር በተክሊል የጋብቻን ስነ ስርዓት የፈፀመች መሆኗን የሚያሳይ ፎቶ መታየቱ ከፍተኛ ውዝግብን ፈጥሯል።

ብዙዎችም በማህበራዊ ሚዲያዎች ላይ ህፃንን መዳር ወንጀል መሆኑን በምሬት ተናግረዋል። ይህንንም እሮሮ ተከትሎ የትግራይ ክልል የሴቶች ጉዳይ ቢሮ ፣ የወረዳ አስተዳደርና በክልሉ የሚገኙ የፍትህ አካላት በጉዳዩ ላይ ጣልቃ ገብተው እሁድ ሊደረግ የነበረውን ሰርግ እንዲቀር አድርገውታል።

"የመከላከያ ሚኒስቴርን በተሻለ መልኩ መምራት ይቻላል" ኢንጂነር አይሻ መሀመድ

የዚህ ፎቶ መሰራጨት ያለ እድሜ ጋብቻ አሁንም ቢሆን በሀገሪቱ ላይ የሚፈፀም መሆኑን ፍንጭ ሰጥቷል። የአንድ ህፃን ታሪክ ብቻ ሳይሆን ብዙ ታዳጊዎች ዕድሜያቸው ሳይደርስ እንደሚዳሩ መረጃዎች ያሳያሉ።

ለዚህም እንደማሳያነት የሚሆነው በ2009 እና 2010 ዓ.ም በአማራ ክልል ብቻ 5685 የጋብቻ ጥያቄዎች በዕድሜ ምክንያት ዉድቅ ተደርገዋል።

የተነጠቀ ልጅነት

በአማራ ክልል ሁሉም ወረዳዎች የህፃናት ጋብቻን ለማስቀረት ከጋብቻ በፊት የህክምና ምርመራ ይደረጋል። በዚህ ሂደት ሁሉም ለጋብቻ የተዘጋጁ ጥንዶች ጋብቻቸውን ለመፈጸም የባለሞያ ማረጋጋጫ ሊኖራቸው ይገባል።

ምርመራውን ሳያልፋ ጋብቻ ከፈጸሙ ግን በአካባቢው ፍትህ ጽ/ት ቤት ተከስሰው ለፍርድ የሚቀርቡበት የህግ ማዕቀፍ ተዘጋጅቶ ስራ ላይ ውሎ በመተግበር ላይ ነው።ቢሆንም ግን እንዲህ አይነት የህግ ማዕቀፍ ቢኖርም አሁንም ቢሆን ያለ እድሜ ጋብቻ በክልሉ ይፈፀማል።

ችግሩ ከሚስተዋልባቸው አካባቢዎች መካከል የፋርጣ ወረዳ አንዱ ነው።በዚህ አመት በቤተሰቦቻቸው የተዘጋጀላቸውን ጋብቻ ሸሽተው ስድስት ህጻናት ከወረዳው ሴቶች ህጻናትና ወጣቶች ፅ/ት ቤት በመጠለል ከትዳር ወጥመድ አምልጠዋል።

"ከሞቱት አንለይም" የሶማሌ ክልል እስረኞች

የ14 አመቷ እና የ5ኛ ክፍል ተማሪዋ ህጻን መሰረት በላይ ከስድስቱ ህጻናት መካከል አንዷ ናት። በእናቷ ወ/ሮ ይመኝ በላቸዉ አማካኝነት ቢቢሲ አግኝቷት 'ኩታራዉ ነዉ እንዳላገባ ያደረገኝ' ብላለች።

ነገሩን ስታብራራ በእድሜ ከሷ የሚያንሰዉ የ4ኛ ክፍል ተማሪ የሚዳሩ ልጆችን ስም ዝርዝር ለትምህርት ቤት ያመለክታል።

ከዛም ተማሪዎች እንዲያዉቁ ተደረገ። ወዲያዉ ለሴቶች ህጻናትና ወጣቶች ጽ/ት ቤት አመልክተዉ ሰርጉ እነዲያልፋቸዉ ተደርጓል። እናቷንም ቢቢሲ ያናገረ ሲሆን 'መጀመሪያማ ያዉ ታስቦ ነበር እንግዲህ ያዉ የድንቁርና ሁኔታ ነዉ። ሁሉን ነገር መጥቼ አይቼ ስለተማርኩ አሁንማ እየደባኝ(እየጸጸተኝ)ነዉ።አሁን ግን ትምህርቷን ነዉ የማስተምራት' ብለዋል።

የፋርጣ ወረዳ ሴቶች ህጻናትና ወጣቶች ፅ/ት ቤት ሃላፊ አምሳል ተስፋ በበኩላቸው እንደሚናገሩት በ2009 ዓ.ም 210 ፤ በ2010 ዓ.ም ደግሞ 124 የሚጋቡ ሰዎች ጥቆማ አቅርበዋል።

በ2010ዓ.ም ሌሎቹን የጋብቻ ጥያቄዎች ማቋረጥ ሲቻል አምስት የህጻናት ጋብቻዎች ግን ተፈፅመዋል። ይህንንም ተከትሎ የሶስቱ ሴት ልጅ አባቶችና ባሎቻቸው የአንድና የሁለት አመት እስራት ተፈርዶባቸዋል።

የሁለቱን ህጻናት ጉዳይ ግን መረጃ በመጥፋቱ ክሱ መቋረጠን ወ/ሮ አምሳል ገልጸዋል።

በክልሉ ሴቶች ህጻናትና ወጣቶች ጉዳይ ቢሮ የሴቶች ንቅናቄና ማስፋፊያ ዳይሬክተር አቶ ስማቸው ዳኘው ችግሩ ቢቀንስም አሁንም መኖሩን ለቢቢሲ ተናግረዋል።

በተለይ ምርመራውን ማለፍ ያልቻሉ ህጻናትን መደበኛ ሰርግ ደግሶ ከመዳር ይልቅ በማህበርና ሰንበቴ እያሳበቡ ህጻናትን መዳር እየተለመደ መምጣቱን ተናግረዋል።

ከሌሎች የክልሉ አካባቢዎችበተለየ መልኩ ምስ/ጎጃም፣ደ/ጎንደር፣ ሰሜን ሸዋ እና በኦሮሚያ ክልል ችግሩ በብዛት የሚታይባቸው አካባቢዎች መሆናቸውን ዳይሬክተሩ ገልጸዋል።

ከክልሉ ፍትህ ቢሮ የተገኘው መረጃ እንደሚያመለክተውበአማራ ክልል በ2009 እና 2010 ዓ.ም 24,259 የጋብቻ ጥያቄዎች ቀርበዋል። ከነዚህ መካከል 17,667 አመልካቾች ብቻ ጋብቻ እንዲፈጽሙ ከፍትህ ጽ/ቤቶች ይሁንታ አግኝተዋል።

በነዚሁ ሁለት አመታት ብቻ 5685 የሚሆኑት የጋብቻ ማመልከቻዎች ደግሞ በምክር እንዲቋረጡ ተደርጓል። ነገር ግን የጋብቻ ጥያቄያቸዉ ዉድቅ ከተደረገባቸዉ አመልካቾች መካከል 79 የሚሆኑት ህጉን በመተላለፍ ጋብቻ ፈጽመው ክስ ተመስርቶባቸዉ በፍርድ ሂደት ላይ ይገኛል።