ጤፏን ለማስመለስ እየተውተረተረች ያለችው ኢትዮጵያ

የጤፍ እንጀራ Image copyright AFP

በዛሬው ዕለት አምባሳደር ፍፁም አረጋ በትዊተር ገፃቸው ላይ የሄግ ዓለም አቀፍ የገላጋይ ድርጅት የጤፍ ባለቤትነት ይዞት የነበረው ድርጅት መብቱ መቀማቱን ጠቅሰው ለኢትዮጵያ ከፍተኛ ድል እንደሆነ የደስታ መልዕክት አስተላልፈው ነበር።

በዚሁ ትዊተር ገፅ ላይ የደች ፍርድ ቤት ውሳኔንም አብረው አያይዘውታል።

ይህ ጉዳይ ከኢትዮጵያ ጋር በጭራሽ እንደማይገናኝና በሁለት የደች ኩባንያዎች መካከል የተካሄደ የጥቅም ክርክር እንደሆነ በአፍሪካ ዓለም አቀፍ ግልግል ዳኝነት አማካሪ የሆነችውን ልዩ ታምሩ ትናገራለች።

ጤፍን ሰዳ የምታሳድደው ኢትዮጵያ

በሆላንድ የጤፍ ዱቄት አዘገጃጀት ላይ በባለቤትነት የተመዘገበው ኤንሺየንት ግሬይንስ የተባለ ኩባንያ ፍቃዴን ሳይጠይቅ የባለቤትነት መብቴን ተጋፍቷል ያለውን ቤክልስ የተባለ በጤፍ ምርቶች ዳቦና ኩኪስ የሚያመርት ድርጅት ላይ ክስ መስርቷል።

ጤፍ ሃገሩ የት ነው? ደቡብ አፍሪካ? አውስትራሊያ? . . .

ፍርድ ቤት የቀረበው የጤፍ ባለቤትነት ጉዳይ

በዚህም የሎያሊቲ (የባለቤትነት መብት) ክፍያ ሊከፈለኝ ይገባል፤ ለፈጠራዬ ገንዘብ ይሰጠኝ የሚል ክስ ማቅረቡን ተከትሎ፤ በምላሹ ቤክልስ የተሰኘው ድርጅት የባለቤትነት መብቱ ሊሰጠው አይገባም፤ ምክንያቱም አዲስ ፈጠራን ስላልጨመረ የባለቤትነት መብቱ ሊነጠቅ ይገባል የሚል መከራከሪያን ይዞ ቀርቧል።

ፍርድ ቤቱም ኤንሺየንት ግሬይንስ የተባለው ድርጅት ምንም አይነት አዲስ ነገር ባለመጨመሩ የባለቤትነት መብቱን ከመንጠቅ በተጨማሪ ቤክልስ የተሰኘው ድርጅት ላወጣው ወጪ በሙሉ ካሳ እንዲከፈል ውሳኔ አስተላልፏል።

በተጨማሪም የሆላንድ ኤምባሲ በትዊተር ገፁ እንዳሰፈረው የፍርድ ሂደቱ መከናወኑንና በብይኑ ላይም አቤቱታ ባለመቅረቡ የአቤቱታው ጊዜ በማለፉ ውሳኔው የፀና እንደሆነ የሚገልጽ መልዕክት አስፍሯል።

ምንም እንኳን ከኢትዮጵያ ጋር የሚያገናኘው ምንም ጉዳይ ባይኖርም ለኢትዮጵያ በር ከፋችና ፋይዳ ያለው ጉዳይ መሆኑንና ኢትዮጵያ ወደፊት ለምታቀርበው ክስም መሰረት ሊሆን እንደሚችል ልየ ታምሩ ትናገራለች።

ጉዳዩን በዋነኝነት የያዘው የፌደራል ጠቅላይ አቃቤ ህግ የሆኑት አቶ ብርሃኑ ፀጋዬ በበኩላቸው በትዊተር ገፃቸው ላይ በጤፍ ላይ እየተሰራጨ ያለው መረጃ ወደ ስህተት የሚመራና ትክክል እንዳልሆነ ገልፀው፤ ይህ ጉዳይ በሁለት ኩባንያዎች መካከል እንደሆነና ከኢትዮጵያ የጤፍ ባለቤትነት መብት ክርክር ጋር ምንም እንደማይገናኝ አስፍረዋል።

ጨምረውም ኢትዮጵያ ክስ ለመመስረት ዝግጅቷን ማጠናቀቋን አሳውቀዋል።

አምባሳደር ታየ አፅቀሥላሴ በበኩላቸው በትዊተር ገፃቸው ላይ እንዳሰፈሩት ይህ ጉዳይ ለረጅም ጊዜ እየተጓተተ ያለ መሆኑን ጠቅሰው፤ ኢትዮጵያ ቡናን ለማስመዝገብ በሄደችበት መንገድ ምርጥ የሚባል ጠበቃዎች ሊወክሏት እንደሚገባ አስረድተዋል።

በአሁኑም ወቅት በአውሮፓ ሃገራት ላይ የጤፍ ምርቶች ባለቤትነቷን የተነጠቀችው ኢትዮጵያ ከአንድ ድርጅት ጋር ባደረገችው ስምምነት ምክንያት ነው።

ከአስርት ዓመታት በፊት ኢትዮጵያ 'ሄልዝ ኤንድ ፐርፎርማንስ ፉድ ኢንተርናሽናል' ከተባለ የሆላንድ ድርጅት ጋር በአውሮፓ ላይ የጤፍ ምርትን ለማሳደግና የቴክኖሎጂ ሽግግርን ከግምት ውስጥ በማስገባት ስምምነት ተፈራርማ ነበር።

ስምምነቱ በኦስትሪያ፣ ቤልጂየም፣ እንግሊዝ፣ ጣልያንና ሆላንድ የጤፍ ምርቶች ላይ ያላትን መብት የነጠቃት ሲሆን የኢትዮጵያ መንግሥትም የባለቤትነት መብቱን ለማስጠበቅ ለአስራ አምስት ዓመት ዓመታት ሲታገል ቆይቷል።

ውዝግቡን የበለጠ ግራ አጋቢ ያደረገው ነገር ደግሞ ከኢትዮጵያ ጋር የተፈራረመ ድርጅት 'ሄልዝ ኤንድ ፐርፎርማንስ ፉድ ኢንተርናሽናል' የሚባል ድርጅቱ መፍረሱ ነው።

በእነዚህ ሀገራት ላይ የጤፍ ምርቶች ባለቤት ሆኖ የተመዘገበው ጃንስ ሩዝጀን የተባለው ግለሰብ የሌላ ኩባንያ ዳይሬክተር ሲሆን ቢቢሲ ግለሰቡን ለማናገር ያደረገው ጥረትም አልተሳካም።