በደቡብ ወሎ ሙሽራና ሚዜውን የገደለው ቦምብ የማን ነበር?

የእጅ ቦምብ Image copyright AFP

በደቡብ ወሎ ዞን ቦረና ወረዳ በታ መንደጋ ቀበሌ የሰርግ ሥነ ሥርዓታቸውን ፈፅመው በጫጉላ ሥነ ሥርዓታቸው ላይ በፈነዳ ቦምብ ሙሽራውን ጨምሮ የሁለት ሰዎች ሕይወት አልፏል።

ሙሽሪት እጮኛዋ መቃብር ላይ ድል ባለ ሠርግ ተሞሸረች

የቦረና ወረዳ ኮሚዩኒኬሽን ባለሙያ የሆኑት አቶ ሲሳይ ክፍሉ በሌሎች 3 ሰዎች ላይም ጉዳት መድረሱን እንደሰሙ ለቢቢሲ የገለፁ ሲሆን ቦምቡ ሙሽራውና ሚዜው ሲነካኩት ሊፈነዳ እንደቻለ ተናግረዋል።

በወቅቱ ሙሽራዋ ወደ ቤተሰቦቿ ጋር ሄዳ ስለነበር ከአደጋው ልትተርፍ እንደቻለች ባለሙያው ጨምረው አስረድተዋል።

የበታ ቀበሌ ምክትል ሊቀመንበር አቶ አበበ ጌቶ የአካባቢው ማኅበረሰብ እጅግ ማዘኑን ገልጸው፤ "ሕብረተሰቡ ጥንቃቄ እንዲያደርግና ህገወጥ መሳሪያ ያላቸው እንዲያጋልጡ ግንዛቤ የመፍጠር ሥራ እየሰራን ነው" ብለዋል።

ለማጭበርበር የሞተ ያስመሰለው አባት ሚስቱንና ልጆቹን አጣ

የቦረና ወረዳ ፖሊስ ፅ/ቤት ኃላፊ ምክትል ኮማንደር ንጋቱ ታመነ በበኩላቸው ጋብቻው ጥር 14፣ 2011 ዓ.ም የተፈፀመ ሲሆን ከሠርጉ ቀን ጀምሮ ለ10 ተከታታይ ቀናት በጫጉላ ከቆዩ በኋላ በአካባቢው ባህል መሰረት አስርት (ልብስ አጠባ) የሚባለውን ስርዓት ጨርሰዋል።

ከዚያም ሙሽሮቹ ወደ ቤተሰቦቻቸው ተቀላቅለው በሙሽራው ቤተሰቦች ቤት መኖር ጀምረው እንደነበር ኮማንደሩ ያስረዳሉ።

ጥር 26፣ 2011 ዓ.ም ከቀኑ ስምንት ሰዓት አካባቢ F1 የተሰኘ የእጅ ቦምብ ከሚዜው ጋር በመሆን ከቤት በስተጀርባ ሲቀጠቅጡ ፈንድቶ የሁለቱም ሕይወት ወዲያወኑ ሊያልፍ እንደቻለ ለቢቢሲ አረጋግጠዋል።

ኮማንደሩ አንዲት ህፃን በፍንጣሪው ቀላል የሚባል ጉዳት እንደደረሰባት አክለዋል።

ሟቾቹ በሃያዎቹ መጀመሪያ የእድሜ ክልል የሚገኙ ሲሆን የቀብር ሥነ ሥርዓታቸው ጥር 27/2011 ዓ.ም መፈፀሙን ኮማንደር ንጋቱ ገልፀዋል።

"ከመንግስት ታጣቂዎች ውጭ ህብረተሰቡ በሠርግ፣ በኃይማኖት ተቋማትና፣ ሠዎች በሚበዙባቸው ቦታዎች የጦር መሳሪያን ይዞ መንቀሳቀስ መመሪያው የሚከለክል ቢሆንም ህብረተሰቡ ግን የጦር መሳሪያ ይዞ የመንቀሳቀስ ልምድ አለው" የሚሉት ኮማንደሩ ይህንንም ልማድ ለመለወጥ የግንዛቤ ስራ እየተሰራ መሆኑን ገልፀዋል።

የፈነዳው ቦምብ ሙሽራው በህገ ወጥ መንገድ ያስቀመጠው መሆኑን መረጃ በማግኘታቸው ሌላ በህግ የሚጠየቅ አካል እንደሌለ ለቢቢሲ ጨምረው ተናግረዋል።

የጫጉላ ሥነ- ሥርዓት

የወረዳው ኮሚዩኒኬሽን ባለሙያ እንደገለፁልን በአካባቢው ባህል የጫጉላ ሥነ ሥርዓት፤ ከሠርጉ ቀን ጀምሮ ለተከታታይ 10 ቀናት ሙሽራው፣ ሙሽሪትና የወንድ ሚዜዎች ከሙሽራው ቤተሰብ ቤት በተዘጋጀላቸው 'መጨጉያ' ጊዜያዊ ቤት በእንክብካቤ የሚቆዩበት ሥርዓት ነው፤ በአስራ ሁለተኛው ቀን የልብስ አጠባ ሥነ ሥርዓት ከተከናወነ በኋላ ሽልማትና ስጦታ ተበርክቶላቸው ወደ ቤተሰብ ይቀላቀላሉ። በባህሉ መሰረት የሴት ሚዜዎች ከሠርጉ ቀን በኋላ ወደየራሳቸው ቤት ይመለሳሉ እንጂ ከሙሽሮቹ ጋር አይቆዩም።

ተያያዥ ርዕሶች