ከ300 በላይ የሚዛን ቴፒ ዩኒቨርሲቲ፤ ሚዛን ካምፓስ ተማሪዎች መታመማቸው ተሰማ

የሚዛን ቴፒ ዩኒቨርሲቲ ሚዛን ግቢ Image copyright Mizan Tepi University FB

በሚዛን ቴፒ ዩኒቨርስቲ ሚዛን ካምፓስ 330 ተማሪዎች ታመው ህክምና ማግኘታቸው ተሰማ።

ህመሙ በዩኒቨርስቲው መከሰቱን የሰሙት ማክሰኞ ዕለት ጥር 28/2011 ዓ.ም ከጠዋቱ 4፡30 ጀምሮ እንደሆነ የተናገሩት የሚዛን ቴፒ ዩኒቨርስቲ ማስተማሪያ ሆስፒታል ሜዲካል ዳይሬክተር ዶ/ር ቴዎድሮስ ወርቁ መጀመሪያ ላይ 15 ተማሪዎች ወደ ሆስፒታላቸው መምጣታቸውን ገልፀዋል።

የሚዛን ቴፒ ዩኒቨርስቲ ስጋት ነግሶበታል

ዶክተሩ እንደተናገሩት በዩኒቨርስቲው ክሊኒክ ያሉ መረጃዎች እንደሚያሳዩት ተማሪዎቹ የህመም ምልክት ማሳየት የጀመሩት ባለፈው ሳምንት አርብ ጥር 24 /2011 ዓ.ም ጀምሮ መሆኑን ነው።

"እንዲህ አይነት ወረርሽኝ ሲከሰት ኮሌራ ተከስቶ ይሆን የሚለው አስግቶን የነበረን ቢሆንም ምርመራው ተደርጎ አለመሆኑ ተረጋግጧል ብለዋል።" በምርመራው የተገኘው ኢኮላይ የተሰኘ ባክቴሪያ መሆኑንም ጨምረው ገልፀዋል።

ዶ/ሩ እንደተናገሩት የታመሙ ተማሪዎቹ ቁጥር ከፍተኛ ሲሆን በግቢው ክሊኒክ ውስጥ ጊዚያዊ የህክምና መስጫ አቋቁመው ህክምና እየተደረገላቸው መሆኑን ተናግረዋል።

ከተማሪዎቹ ከተወሰደው ናሙና የተገኘው ጥገኛ ተዋህስ ከሰው ልጅ ጋር ተስማምቶ የሚኖር ባክቴሪያ ቢሆንም በተለያየ ምክንያት ግን ጠቃሚ የነበረው ጎጂ ሊሆን ይችላል ይላሉ ዶ/ር ቴዎድሮስ።

ይሁን እንጂ በሽታው በአንድ ጊዜ ተማሪዎቹ ለተመሳሳይ ነገር ተጋልጠው የመጣ ሊሆን እንደሚችልም ይጠረጥራሉ። ህመሙ በውሃ ወይም በምግብ አማካይነት ሊከሰት ስለሚችል መንስኤውን ለማወቅ ከፌደራልም ሆነ ከክልል የሚመጡ ባለሙያዎች ምርመራ እንዲያደርጉ አስፈላጊውን ነገሮች ማመቻቸታቸውን አስረድተዋል።

በአሜሪካ ሀሰተኛ ዩኒቨርሲቲ የሚማሩ ተማሪዎች መታሰር በሕንድ ቁጣን ቀሰቀሰ

በአሁኑ ሰዓት በጊዜያዊ ማቆያውም ሆነ በሆስፒታሉ ተኝተው እየታከሙ ያሉት ተማሪዎች ቁጥር ከ20 እንደማይበልጥ የሚናገሩት ዶ/ር ቴዎድሮስ በሽታው በአካባቢው ማህበረሰብም ሆነ በቴፒ ካምፓስ ስለመለከሰቱ መረጃ እንደሌላቸው ተናግረዋል።

ጉዳዩን አስመልክተን ያነጋገርናቸው የዩኒቨርስቲው ፕሬዝዳንት ዶ/ር ፋሪስ ቴሊል የጤና ችግሩ በምን ምክንያት እንደተከሰተ እስካሁን እንዳልተረጋገጠ የተናገሩ ሲሆን ማክሰኞ ዕለት ግን ቁጥራቸው በርከት ያሉ ተማሪዎች የጤና መታወኩ እንዳጋጠማቸው ለቢቢሲ አረጋግጠዋል።

ሕክምና ያገኙት ተማሪዎች ቁጥር 330 ሲሆኑ አብዛኞቹ በዩኒቨርሲቲው የተማሪዎች ክሊኒክ የታከሙ ሲሆን ቀሪዎቹ ደግሞ በዩኒቨርሲቲው ማስተማሪያ ሆስፒታል ሕክምና አግኝተዋል። አብዛኞቹም ከህመማቸው በማገገማቸው በህክምና ላይ የነበሩት ተማሪዎች ቁጥር በከፍተኛ ሁኔታ እንደቀነሰ አስረድተዋል።

ዩኒቨርሲቲው አንገብጋቢ የውሃ ችግር ያለበት መሆኑንና ግቢ ውስጥ የሚጠቀሙት የጉድጓድ ውሃ በቂ ባለመሆኑም ከከተማ እያስመጡ እንደሚጠቀሙ የሚናገሩት ፕሬዚዳንቱ የጤና መታወኩ ከመከሰቱ አስቀድሞ ለተከታታይ 3 ቀናት በግቢው ውስጥ ውሃ ጠፍቶ እንደነበር አስታውሰዋል።

ተያያዥ ርዕሶች