መምህር ስዩም ቦጋለ፡ የተማሪዎቻቸውን ገላና ልብስ የሚያጥቡት መምህር

መምህር ስዩም ቦጋለ የተማሪን ገላ ሲያጥቡ Image copyright Awi communication

ስድስት የውሃ መቅጃ ጀሪካንና ሁለት ሳፋ (ጥሽት) አላቸው፤ እስካሁን በግምት ከ650 በላይ ህጻናት ተማሪዎችን ገላ አጥበዋል፤ በአማካይ አንድን ተማሪ ለማጠብ 30 ደቂቃ ይፈጅባቸዋል።

በሳምንት ሁለት ቀናት ማለትም ረቡዕና አርብ የ60 ተማሪዎችን ልብስ ያጥባሉ፤ የተማሪዎቻቸው ንፅህና ተጠብቆና በትምህርታቸው ልቀው ማየት ህልማቸው ነው። ካላቸው አነስተኛ ደመወዝ አንድ ሶስተኛውን ለዚህ በጎ ስራቸው ለማዋል በጅተውታል።

ሀሁ አስቆጣሪው ጃማይካዊ

ቀኝ እጇን ለገበሬዎች የሰጠችው ኢትዮጵያዊቷ ሳይንቲስት

የሙያውን ፈተና ለመጋፈጥ ከከተማ ርቆ የሄደው ሐኪም

የአገሬው ሰው "ምን ሀጢያት ቢሰራ ነው፤ እንዲህ ያለ እዳው ጎንበስ ቀና የሚለው?" እያሉ ያጉመተምቱ ነበር- ታዲያ ነገሩ እስከሚገባቸው ነው። ከገባቸው በኋላማ "አንተ 'እንትፍ ...እንትፍ' ብለህ ከመረቅካቸውም ይበቃል" ሲሉ ያሞግሷቸዋል።

የሚያውቋቸው "ጋሸ" እያሉ ነው የሚጠሯቸው፤ ሲበዛ ያከብሯቸዋል። "የእርሳቸውን ነገር ለማውራትም ይከብዳል"ይላሉ። እንዲያው በአጭሩ "ለትውልድ ነው የተፈጠሩት" ሲሉ ይገልጿቸዋል።

ተማሪዎቻቸው ከአንድ ክፍል ወደ ሌላ ክፍል ቢሸጋገሩም እርሳቸው የሚያስተምሩበትን አንደኛ ክፍል ላለመልቀቅ ሲሉ " ምነው እንደ ሊቁ ያሬድ ሰባት ጊዜ በወደቅኩ" ብለው ይመኛሉ አሉ።

እኝህ ሰው ማን ናቸው?

መምህር ስዩም ቦጋለ የእንግሊዘኛ መምህር ሲሆኑ በ1998 ዓ.ም ከጎንደር ዩኒቨርሲቲ ተመርቀው በመምህርነት እያገለገሉ ይገኛሉ።

ከበፊት ጀምሮም በቤተሰብ ውስጥ የሚፈጠሩ ችግሮችን የማየትና ለዚያም መፍትሄ የማፈላለግ ፍላጎት እንደነበራቸው ይናገራሉ። በእርግጥ የእርሳቸው አስተዳደግም የተንደላቀቀ ባለመሆኑ ለችግር ብዙም ሩቅ አይደሉም።

እንዲህ ዓይነት የበጎ ስራን ማከናወን የጀመሩት አባታቸው በ13 ዓመት እድሜያቸው በሞት ከተለዩ በኋላ ከእርሳቸው በታች ያሉ እህትና ወንድማቸውን የማስተማር ኃላፊነት ከተረከቡበት ጊዜ አንስቶ ነው።

"እነርሱን በሚፈለገው እውቀትና የስነ ምግባር ደረጃ ለማብቃት የራሴን ሕይወት ከፍያለሁ፤ በዚህም የልፋቴን ዋጋም በእነርሱ ማየት ችያለሁ"ይላሉ። በአሁኑ ሰዓት ደካማ እናታቸውን እየረዱ ይኖራሉ።

የቤት ውስጥ የሚባል ማንኛውንም ስራ ያከናውናሉ፤ ምንም የሚቀራቸው የለም። ይሄው ልማድም ጎልብቶ ወደ ሙያቸው እንደመጣ ያስረዳሉ- መምህር ስዩም።

የሃምዛ ሃሚድ ገመድ አልባ የኤሌክትሪክ ማስተላለፊያ

በሚያስተምሩበት አካባቢ ወላጆች እድሜያቸው ለትምህርት የደረሱ ልጆቻቸውን ወደ ትምህርት ቤት እንዲልኩ ለመቀስቀስ ጋራና ሸንተረሩን ያቋርጣሉ፤ ሰለቸኝ ደከመኝ አይሉም። ሠርግ፣ ለቅሶ፣ እድር ላይ የአገሬውን ሰው መስለው ይሳተፋሉ፤ የአገሬው ሰው ቢሆኑም ቀለም ቀምሻለሁ ብለው ግን እራሳቸውን አያመፃድቁም።

ከዚያም የማትለያቸውን ማስታወሻ ደብተር አውጥተው የሚሰሟቸውን ቤተሰባዊ ችግሮች እየጠየቁ ይመዘግባሉ። "ሁሉም ሰው ችግራችንን ይጠይቀናል፤ ግን ከንፈር ከመምጠጥ ባለፈ መፍትሔ የሰጠን የለም" የሚል ተደጋጋሚ መልስ ነው የሚያገኙት ታዲያ።

አንድ ቀን አንዲት ተማሪ "ልብሴ ቀዳዳ በመሆኑ፤ የተቀደደ ልብስ ለብሼ ትምህርት ቤት መምጣት አልፈልግም" ስትል ትምህርት ቤት ላለመግባቷ መልስ የሰጠቻቸውን ያስታውሳሉ።

Image copyright Awi Communication

በወቅቱ የሰሙት ነገር ከእንቅልፋቸው ያባንናቸው ነበር፤ ይህን ስሜታቸውን ለማስታገስ ቢያንስ ሁለት ተማሪ መርዳት እንዳለባቸው ከራሳቸው ጋር ተነጋግረው ወሰኑ።

ልብስ አሰፍተው፣ የትምህርት ቁሳቁስ በሚችሉት አሟሉላት። እርሷም አላሳፈረቻቸውም ታዲያ። ከክፍሏ ቀዳሚ በመሆን ትምህርቷን እንዳጠናቀቀችና እርሳቸው እንደሚሉት ይህች ልጅ በምህንድስና ተመርቃ ስራ ላይ ትገኛለች።

የእርሷ ለስኬት መብቃት "ትውልድ እየቀጨጨና እየጠፋ ያለው በእኛ ምክንያት ነው" ሲሉ ጣታቸውን ወደ የቀለም አባቶች እንዲቀስሩ ምክንያት ሆናቸው፡፡ ችግሩ ያለው ከትውልዱ ሳይሆን ከቀራፂው መሆኑን አመኑ። ለዚሁ ጥያቄ ምላሽ ለማግኘት ረዳት የሌላቸውንና የአቅመ ደካማ ልጆችን ንፅህና መጠበቅ እንዲሁም የትምህርት ጥራት የበጎ ስራቸው ዋና ማጠንጠኛቸው ሆነ።

ይህ ብቻም አይደለም፤ ቀደም ብሎ የ7ኛ እና የ8 ኛ ክፍል የእንግሊዘኛ አስተማሪ በነበሩበት ጊዜ ተማሪዎቹ 'G' እና 'J' የእንግሊዝኛ ፊደል መለየት ሲያዳግታቸው ያያሉ። እነዚህ ተማሪዎች እዚህ የደረሱት በየት ተንሳፈው ቢመጡ ነው? ምን ዓይነት መምህር ቢያስተምራቸው ነው? የሚለው የዘወትር ጥያቄያቸው ነበር።

ስለሆነም እንዲህ ዓይነት ትውልድ እንዴት እናፈራለን? ሲሉ በአዊ ብሔረሰብ አስተዳደር፣ ፋግታ ለኮማ ወረዳ ትምህርት ፅ/ቤት አቤት አሉ። ለዚህም መፍትሔ ይሆን ዘንድ ከደረጃቸው ዝቅ ብለው አንደኛ ክፍል ማስተማር እንደሚፈልጉ ጥያቄ አቀረቡ።

ይሁን እንጂ እንዳሰቡት ቀላል አልሆነላቸውም። "አንደኛ ክፍልን ለማስተማር መሰልጠን ያለብዎትን ስልጠና አላገኙም" የሚል ጥያቄ ሞገታቸው። የሚያበቃኝን ስልጠና ስጡኝ ሲሉ በአቋማቸው ጸኑ፡፡

የኋላ ኋላ ተሳክቶላቸው አንደኛ ክፍልን ብቻ ማስተማር ጀመሩ። የእርሳቸው ስራ ከታች ተማሪዎችን አብቅቶ ለቀጣዩ መምህር ማቀበል ብቻ ሆነ።

በስራ ተወጥሮ ለሚውል አርሶ አደር፣ ውሃ በቀላሉ በማይገኝበት የገጠር አካባቢ፤ ምን አልባትም ውሃ ለመቅዳት በእግር ብዙ ርቀት መጓዝን በሚጠይቅ የኑሮ ሁኔታ አልያም ምርኩዝ ይዞም ቢሆን ውሃ ከወንዝ መቅዳት ለማይሆንለት ቤተሰብ የራስንም ሆነ የልጆችን ንጽህና መጠበቅ ዘበት ሊሆን ይችላል። ይህ ሌላኛው የሚያሳስባቸው ጉዳይ ነው- ለመምህሩ።

ከዚህ በኋላ ነበር ሳሙናዎችንና የማጠቢያ ሳፋ (ጥሽት) በመግዛት የተማሪዎችን ንፅህና ለመጠበቅ ሲሉ ልብሳቸውንና ገላቸውን ማጠብ የጀመሩት።

መምህር ስዩም በዘንድሮው ዓመት በሁለት ፈረቃ 130 ተማሪዎችን ያስተምራሉ። ማስተማር ብቻ ሳይሆን ንፅህናቸውን መጠበቅ፤ አይናቸው በትራኮማ በሽታ እንዳይጠቃ ፊታቸውን ማጠብ፤ በሳምንት ሁለት ጊዜ ልብሳቸውን ማጠብና ገላቸውን ማጠብ ለራሳቸው የሰጡት ኃላፊነት ነው።

ዘወትር ሀሙስ ጠዋት ሁሉንም ተማሪዎቻቸውን ተቀያሪ ልብስ በመያዝ ከትምህርት ሰዓታቸው ቀደም ብለው እንዲመጡ ይጠሯቸዋል። ምንም እንኳን በትምህርት ቤቱ በእጅ እየተወዘወዘ የሚፈስ ቧንቧ ቢኖርም ብዙ ስለሚያለፋቸው ከእርሱ ጋር መታገል አይፈልጉም። ከትምህርት ቤቱ 200 ሜትር ርቀት ላይ ኩልል እያለች የምትፈስ ንፁህ የመስኖ ውሃን መጠቀምን ይመርጣሉ።

ከዚያም ባሏቸው ጀሪካኖች ውሃ በመቅዳት ለዚሁ አገልግሎት ብለው በገዙት ማጠቢያ ሳፋ ለሴት ተማሪዎቹ ቅድሚያ በመስጠት ገላቸውን በየተራ ያጥቧቸዋል። ለዚህ ተግባራቸው የአሸዋ አንደኛ ደረጃ ትምህርት ቤት ርዕሰ መምህር የሆኑት አቶ ያረጋል ካሳሁን ምስክር ናቸው።

ርዕሰ መምህር አቶ ያረጋል በትምህርት ቤቱ መስራት ከጀመሩ አራት ዓመታትን አስቆጥረዋል። ምንም እንኳን መምህር ስዩም ይህንን ድርጊታቸውን ቀደም ብለው የጀመሩት ቢሆንም በቆዩባቸው አራት ዓመታት ጊዜ ውስጥ ስራቸውን በቅርብ ሆነው እንደሚከታተሉ ይናገራሉ።

"ከትምህርት ቤቱ ድጋፍ እንዳናደርግላቸው አቅም ባለመኖሩ፤ በዚህ ዓመት ለሳሙና መግዣ እንኳን ቢውል ብለን 1500 ብር ብቻ ድጋፍ አድርገንላቸዋል" ይላሉ።

የ29 ዓመቷ የህክምና ዶክተርና ኢንጅነር ዕልልታ ጉዞ

አቶ ያረጋል እንደሚሉት የመምህር ስዩም ድርጊት በሌሎች መምህራን ላይም መነሳሳትን ፈጥሯል፤ በዚህም ምክንያት ትምህርት ቤቱ በትምህርት አሰጣጥ በወረዳው ካሉ የተሻለ ሆኖ መገኘት ችሏል። በወረዳው በተካሄዱ የተለያዩ የትምህርት ቤቶች የቀለም ውድድርም ማሸነፍ ለመቻላቸው የእርሳቸውን አስተዋፅኦ ያነሳሉ።

"በእርሳቸው ክፍል የሚያቋርጥ ተማሪ የለም፤ ሁሉም የዓመቱን ትምህርት ያጠናቅቃሉ፤ ወላጆችም ልጆቻቸውን ወደ ትምህርት ቤት የመላክ ፍላጎት አላቸው" ሲሉ ያክላሉ።

ከተማሪዎቹ ወላጆች የሚያገኙት ግብረ መልስ ምን እንደሆነ የጠየቅናቸው ርዕሰ መምህሩ አስተያየቱ አዎንታዊ እንደሆነና 'እንደ አባት' ሙሉ እምነት እንደጣሉባቸው ያስረዳሉ።

መምህር ስዩም ይህን በጎ ተግባር ከጀመሩ ከ10 ዓመታት በላይ እንደሚሆናቸው የሚናገሩት አቶ ያረጋል ሁሉም የትምህርት ቤቱ ተማሪዎች በእርሳቸው የእንክብካቤ እጅ ስለሚያልፉ ከሁለተኛ ክፍል በላይ ያሉ ተማሪዎችም ሌላ ቅናት አያድርባቸውም።

"እንዲያውም መስከረም ሲመጣ ወደ 2ኛ ክፍል ያለፉ ተማሪዎች እርሳቸውን ጥለው ለመሄድ ይቸገራሉ፤ ህፃናትም ስለሆኑ ሁልጊዜ አንደኛ ክፍል ቢማሩ ደስታቸው ነው- ለእርሳቸው ሲሉ" በማለት የትምህርት ቤቱ ተማሪዎች ለእርሳቸው ያላቸውን አክብሮት ይገልፃሉ። በተለይ ተማሪዎችን በትምህርት ለማብቃት የሚከተሉትን ስነ ዘዴ ለማየት ከተለያዩ ትምህርት ቤቶች ጎብኝዎችም እንደሚመጡ ያስረዳሉ።

ፈቃዱ እጅጉ አዲስ አበባ በመንግስት ስራ ላይ የሚገኝ ሲሆን እርሳቸውን በቅርበት ያውቃቸዋል። ለእርሱ ባይደርሱም ታናናሾቹን ያስተማሯቸው መምህር ስዩም ናቸው። "ሙያውን ያከብራሉ፤ ደግነታቸው የበዛ ነው" ይላል። በአካባቢው ተወዳጅ የሆኑ ሰው እንደሆኑ ይመሰክራል።

የተቸገረን በመርዳት እንደሚታወቁ ይናገራል "አንድ ተማሪ ቸገረን ሲል ለምን ስዩምን አትጠይቁም" ይባል እንደነበር ያስታውሳል።

መምህር ስዩም በዚህ በጎ ስራቸው የተለያዩ ሽልማቶች የተበረከተላቸው ሲሆን በ2010 ዓ.ም በተካሄደው 6ኛው የበጎ ሰው ሽልማት በመምህርነት ዘርፍ እጩ ሆነው ተመርጠዋል፤ የዋንጫና የገንዘብ ሽልማትም ተበርክቶላቸዋል። በወረዳና በፌዴራል ደረጃ ሜዳሊያና የተለያዩ የምስክር ወረቀቶችን አግኝተዋል።

በዚህ ዘገባ ላይ ተጨማሪ መረጃ