ታንዛኒያ ውስጥ በ8 እስር ቤቶች 1ሺህ 900 ኢትዮጵያዊያን ይገኛሉ

የስደት ጉዞ Image copyright Ymane

ከታንዛኒያ በቅርቡ 554 ኢትዮጵያዊያንን ወደ ሀገር ቤት የመመለስ ሥራ ዝግጅት መጠናቀቁን በታንዛኒያ የኢትዮጵያ ልዩ መልዕክተኛና ባለሙሉ ስልጣን አምባሳደር ዮናስ ዮሴፍ ለቢቢሲ ገለፁ።።

ከእነዚህ እስረኞች መካከል ከ300 በላይ የሚሆኑት የሚገኙት ከዋና ከተማው ዳሬሰላም 354 ኪሎ ሜትር ርቀው ታንጋ የሚባል አካባቢ ነው።

250ዎቹ ደግሞ ታንዛኒያ ዋና ከተማ አቅራቢያ ስለሚገኙ ለሁሉም የጉዞ ሰነድና ወጪያቸውን አሰናድቶ ለመሸኘት ከሦስት ሳምንት ያላነሰ ጊዜ እንደሚያስፈልጋቸው አምባሳደሩ ለቢቢሲ አስረድተዋል።

ኢትዮጵያዊያን ዛምቢያ ውስጥ በቁጥጥር ስር ዋሉ

የኢትዮጵያውያን ስደተኞች ኑሮ በደዳብ

ታንዛኒያ ውስጥ በስምንት እስር ቤቶች ውስጥ ከ1 ሺህ 900 በላይ ኢትዮጵያዊያን እንደሚገኙ አምባሳደር ዮናስ ዮሴፍ ለቢቢሲ አረጋግጠዋል።

ስደተኞቹ ወደ ደቡብ አፍሪካ የሚሻገሩ መሆናቸውን ገልፀው፤ ሁሉም የተሟላ የጉዞ ሰነድ እንደሌላቸው ተናግረዋል።

አምባሳደር ዮናስ ጨምረው ኤምባሲው ከታንዛኒያው ፕሬዝዳንትና ከውጭ ጉዳይ ሚኒስትሩ ጋር ውይይት ማድረጉንና ቀሪዎቹን እስረኞችንም ለመልቀቅ ፈቃደኞች መሆናቸውንም አሳውቀዋል።

ሶሪያውያን ስደተኞች በአዲስ አበባ ጎዳናዎች

ነገር ግን በእስረኞቹ አፈታት ዙሪያ ከኢትዮጵያ መንግሥት ከፍተኛ አመራሮች ጋር መነጋገር ይፈልጋሉ ሲሉ ገልፀዋል።

አምባሳደር ዮናስ እንደሚናገሩት በዚህ ዓመት በህዳር ወር መጨረሻ ላይ ከ230 በላይ ኢትዮጵያዊያን ወደ ሀገር ቤት ተመልሰዋል።

ጨምረውም ከሚለቀቁት ኢትዮጵያውያን ስደተኞች መካከል አንዳንዶቹ የእስር ጊዜያቸውን ያጠናቀቁ ሲሆኑ አብዛኞቹ ደግሞ ከታንዛኒያ መንግሥት ጋር በመነጋገር በምህረት ከእስር የሚወጡ ናቸው።

ስደተኞቹ በእድሜ አፍላ ወጣቶችና ወንዶች መሆናቸውንም አማባሳደር ዮናስ ዮሴፍ ጨምረው ገልፀዋል።

በዚህ ዘገባ ላይ ተጨማሪ መረጃ