ዓለም ሁሉ የሚያወራለት ክሪይፕቶከረንሲ ምንድነው?

ቢትኮይን

የፎቶው ባለመብት, Reuters

የጥንታዊው የሰው የዛፍ ፍሬ ለቅሞ እና እንስሳት አድኖ ህይወትን አስቀጥሎ ከዚህ ደርሷል።

በጊዜ ሂደት እና በቴክኖሎጂ እድገትም የአኗኗር ዘያችን በፍጥነት እየተቀየረ መጥቷል። ለዚህም ማሳያ የሚሆነን ደግሞ 'ዲጂታል ገንዘቦችን' ለምርት እና አገልግሎት መገበያያነት ማዋል መቻላቸው ሊጠቀስ ይችላል።

21ኛው ክፍለዘመን ካስተዋወቀን የቴክኖሎጂ ምጡቅ ቃላት መካከል ብዙ እየተባለለት ያለው 'ክሪይፕቶከረንሲ' አንዱ ነው።

ኦክስፎርድ መዝገበ ቃላት 'ክሪይፕቶከረንሲን' እንዲህ ሲል ይገልጸዋል፤ የገንዘብ ልውውጦችን ደህንነት የሚያረጋግጥ፣ የተጨማሪ አሃዶችን መፈጠርን የሚቆጣጠር እና ገንዘብ መተላለፉን የሚያረጋግጥ ጠንካራ ክራፕቶግራፊ የሚጠቀም መገበያያ እንዲሆን ተደርጎ የተቀረጸ ዲጂታል ገንዘብ።

ከላይ የተጠቀሰውን መስፈርት የሚያሟሉ በርካታ አይነት ክሪፕቶካረንሲዎች አሉ። በስፋት ከሚታወቁት መካከል ቢትኮይን፣ ኤቴሪያም፣ ሪፕል እና ቢትኮይን ካሽ የሚባሉት ከበርካታ ክሪፕቶካረንሲዎች መካከል ሊጠቀሱ ይችላሉ።

በቅድሚያ የ'ዲጂታል ከረንሲውን' ተቀላቅሏል ሚባልለት እና በስፋት በሚታወቀው ቢትኮይን ላይ ትኩረታችንን እናድርግ።

ቢትኮይን ምንድነው?

ቢትኮይን ማለት በቀላል ቋንቋ፤ ዲጂታል+ገንዘብ+መገበያያ በማለት ማጠቃለል ይቻላል።

ይህ መገበያያ በኪሳችን ተሸክመን እንደምንዞረው የብር ኖት ወይም ሳንቲም ሳይሆን 'ኦንላይን' የሚቀመጥ ዲጂታል ገንዘብ ነው።

ሌላው የቢትኮይንና የተቀሩት የክሪይፕቶከረንሲዎች ልዩ ባህሪ በመንግሥታት እና በባንኮች አለመታተማቸው እንዲሁም ቁጥጥር አለመደረጉ ነው። ቢትኮይን የሚፈጠረው 'ማይኒንግ' በሚባል ሂደት ነው። በመላው ዓለም በኔትወርክ በተሳሰሩ ኮምፒውተሮች ቁጥጥር ይደረግበታል።

ቢትኮይንን የፈጠረው ግለሰብ/ቡድን በዓለም ላይ 21 ሚሊዮን ቢትኮይኖች ብቻ እንዲፈጠሩ ገደብ እንዳስቀመጠ/ጡ ይታመናል። የብሎክቼይን መረጃዎች እንደሚያሳዩት እስካሁን 17 ሚሊዮን ያህል ቢትኮይኖች ማይን ተደርገዋል።

የቢትኮይን ዋጋ መዋዠቅ?

ከአንድ ዓመት በፊት እአአ የካቲት 15/2018 የአንድ ቢትኮይን ዋጋ 10,031 የአሜሪካ ዶላር ነበር። ከአንድ ዓመት በኋላ ማለትም የካቲት 15/2019 የአንድ ቢትኮይን ዋጋ ወደ 3,561 የአሜሪካ ዶላር ዝቅ ብሏል።

ቢትኮይን ከተፈጠረ 10 ዓመታት ተቆጠረዋል። ባለፉት አስር ዓመታትም የቢትኮይን ዋጋ እጅጉን እየጨመረ መጥቷል። የካቲት 2010 ዓ.ም የአንድ ቢትኮይን ዋጋ ከ10ሺህ ዶላር በላይ ደርሶ ነበር። ከሁለት ዓመት ከነበረው ዋጋ ጋር ሲነጻጸርም ከ27 እጥፍ በላይ ጨምሯል። አሁን ላይ ደግሞ ከአንድ ዓመት በፊት ከነበረው ዋጋ ጋር ሲነጻጸር ወደ 3 እጥፍ በሚጠጋ ዋጋ ቀንሷል።

ከሁለት ዓመታት በፊት ዋጋ በፍጥነት ሲጨምር ለዋጋው መጨመር ምክንያቱ በትክክል ይህ ነው ማለት አልተቻለም። አንዳንድ የምጣኔ ሃብት ባለሙያዎች ግን ኢንቨስተሮች ''እድሉን እንዳያልፋቸው'' ከሚገባው በላይ ፈሰስ እያደረጉበት ነው የሚል ምክንያት ያቀርባሉ። ሌሎች ደግሞ የቢትኮይን ተቀባይነት እየጨመረ በመምጣቱ ዋጋው እንደጨመረ ያስቀምጣሉ።

በቢትኮይን ግብይት መፈጸም ይቻላል?

አዎ። ለሚያቀርቡት ምርት እና አገልግሎት ቢትኮይንን በክፍያ መልክ የሚቀበሉ በርካቶች ድርጅቶች አሉ። ማይክሮሶፍት፣ የፈጣን ምግብ አቅራቢዎቹ ኬኤፍሲ እና ሰብዌይ፣ የጉዞ ወኪሉ ኤክስፔዲያን ከመሳሰሉ ባለብዙ ሚሊዮን ገንዘብ ኩባንያዎችን አንስቶ እስከ ሆቴሎች እና ካፊቴሪያዎች ቢትኮይንን በክፍያ መልክ ይቀበላሉ።

በቢትኮይን አማካኝነት ክፍያ ሲፈጸም የገዢውን ማንነት ይፋ አለማድረግ ያስችላል። ይህም በርካቶች በኢንተርኔት አማካኝነት ማንነታቸውን ሳይገልጡ አገልግሎቶችን እንዲያገኙ ስለሚያስችላቸው በቢትኮይን አማካኝነት የሚደረጉ የንግድ ልውውጦች ቁጥር እጅጉን ጨምሯል።

ቢትኮይን እንደስጋት?

አሸረትስ በተባለ የፋይናንስ ተቆጣጣሪ ኩባንያ ውስጥ ባለሙያ የሆኑት ብራደሊይ ራይስ በቢትኮይን ላይ ምንም አይነት ቁጥጥር እንደማይደረግበት ያስታውሳሉ።

ቢትኮይንን በመጠቀም የገዢው ማንነት ይፋ ሳይደረግ በየትኛውም ሰዓት እና በየትኛውም ስፍራ የቢትኮይን ዝውውር ማድረግ ይቻላል። የግዢው ማንነት ይፋ ሳይደረግ ግብይት መፈጸም ይቻላል።

በዚህም ሕገ-ወጥ ቡድኖች የጦር መሳሪያዎች እና እጾችን ሊገዙ እና ሊሽጡ ይቻላሉ፣ ሕገ-ወጥ የገንዘብ ዝውውር እና አሸባሪዎችን ለመደገፍ ያስችላል በማለት ቢትኮይንን ጨምሮ ሌሎች ክሪይፕቶከረንሲዎች ላይ ያላቸውን ስጋት የሚያነሱ በርካቶች ናቸው።

በሌላ በኩል በርካታ የፋይናንስ ባለሙያዎች ቢትኮይን ላይ ምንም አይነት ቁጥጥር አለመደረጉ ተፈላጊነቱን እንደጨመረው ያወሳሉ።

የፎቶው ባለመብት, Getty Images

በቢትኮይን የሃገራት ምልከታ

እአአ 2009 ላይ ከበርካቶች ጋር የተዋወቀው ቢትኮይን፤ ሕጋዊ ነው? ወይስ አይደለም? በሚሉ ጥያቄዎች ታጅቦ ቆይቷል። 'ሕጋዊ ነው? ወይስ አይደለም?' ለሚለው ጥያቄ ምላሽ የምናገኘው ግን የት የሚለው ሲካተትበት ብቻ ነው።

አሜሪካ፣ ካናዳ፣ የአውሮፓ ህብረት እና አውስትራሊያን የመሳሰሉ የዓለማችን ግዙፍ ኢኮኖሚዎች ለቢትኮይን አዎንታዊ ምልከታ አላቸው። ከላይ በተጠቀሱት ስጋቶች ምክንያት ቬትናም፣ ቦሊቪያ፣ ኮሎምቢያ እና ኢኳዶር በቢትኮይን መገበያየትን ከከለከሉ ሃገራት መካከል ይገኙበታል።

ቢትኮይን 10 ዓመታት ቢያስቆጥርም አሁንም ቢሆን በርካታ የዓለማችን ሃገራት ክሪፕቶከረንሲዎችን በተመለከተ ግልጽ ሕግ የላቸውም። ክሪይፕቶከረንሲዎችን መቆጣጠር የማይቻል በመሆኑም ለመንግሥታት ፈተና ሆኖ ቆይቷል።