አብዱል ፋታህ አልሲሲ እስከ 80 ዓመታቸው ግብጽን ሊገዙ ይችላሉ

አብዱል ፋታህ አል-ሲሲ Image copyright Getty Images

የግብጽ ምክር ቤት አልሲሲን ለሚቀጥሉት 12 ዓመታት በርዕሰ ብሔርነት እንዲቀጥሉ የሚያስችላቸውን ረቂቅ በፍጹም አብላጫ ድምጽ ደገፈ። ይህ የሕገ መንግሥት ለውጥን የሚያስከትለው ረቂቅ ውሳኔ ከ596 የግብጽ ሸንጎ እንደራሴዎች 485 የሚሆኑት ደግፈውታል።

አብዱል ፋታህ አል-ሲሲ እንደ ጎርጎሮሲያዊያኑ በ2022 ሁለተኛ ምዕራፍ የሥልጣን ዘመናቸው እንደሚያበቃ ይጠበቅ ነበር። ሕግ አውጪው ሸንጎ ግን ለጊዜው ሁለት ዓመት ጨምሮላቸዋል። ከዚያ በኋላ ባሉ ዓመታትም በሥልጣን እንዲቆዩ ለሚያስችለው ረቂቅም ድጋፉን ሰጥቷል።

''የተፈጥሮ ሃብታችንን ለመጠቀም የማንንም ይሁንታ አንጠብቅም''

በርካታ የግብጽ ሰብአዊ መብት ተሟጋች ቡድኖች ውሳኔውን ክፉኛ ኮንነውታል።

ይህ ረቂቅ ሕግ በድጋሚ ለፓርላማ ከቀረበ በኋላ ጸድቆ ይሁንታን ካገኘ ሕዝበ ውሳኔ እንደሚደረግበት ይጠበቃል።

ረቂቅ ሕጉ ምን አዲስ ነገር አለው?

በ2014 በሕዝበ ውሳኔ ጸድቆ የነበረው የግብጽ ሕገ መንግሥት 'አንቀጽ-140' ተመራጩ ርዕሰ ብሔር ከሁለት የአራት ዓመት የአገዛዝ ምዕራፍ በላይ በሥልጣን እንዳይቆይ ያስገድዳል።

ነገር ግን አሁን በቀረበው ረቂቅ ርዕሰ ብሔሩ ከዚያም በላይ በሥልጣን እንዲቆይ ያስችለዋል። በዚህም መሠረት የ64 ዓመቱ አልሲሲ እንደ ፈረንጆቹ እስከ 2034 መንበራቸው አይነቃነቅም። በዚያን ጊዜ ዕድሜያቸው ወደ ሰማንያ ይጠጋል ማለት ነው።

ግብጻዊቷ ዘፋኝ አባይ ላይ ቀልደሻል ተብላ እስር ተፈረደባት

በረቂቅ ሕጉ መሠረት የአልሲሲ የሥልጣን ዕድሜ ዘለግ ባለ ዓመታት መለጠጡ ብቻ ሳይሆን ዳኞችና አቃቤ ሕጉን የመሾም ልዩ ሥልጣንንም ያጎናጽፋል። ረቂቁ ከአል-ሲሲ ባሻገር ለመከላከያ ሠራዊትም ተጨማሪ ኃላፊነቶችን ይሰጣል።

አዲሱ ረቂቅ አዲስ የታችኛው ምክር ቤት እንዲቋቋም፣ የፓርላማው መቀመጫ 25 እጅ ለሴቶች እንዲሰጥ፣ ተገቢ ውክልና ለኮፕቲክ ክሪስቲያን አማኞች እንዲቀርብ ያደርጋል።

ሕዝቡ ምን አለ?

በምክር ቤቱ የአልሲሲ ደጋፊዎች እንደሚሉት የሥልጣን ዕድሜ መራዘሙ ሲሲ የጀመሯቸውን የምጣኔ ሀብት ማሻሻያዎችን ከዳር እንዲያደርሱ ያስችላቸዋል።

ተቃዋሚዎች በበኩላቸው ረቂቁ ለዲሞክራሲ አደጋ ነው ይላሉ። አስራ አንድ የሚሆኑ የሰብአዊ መብት ተቋማት በጋራ በሰጡት መግለጫ ረቂቁን 'አምባገነንነትን በወርቅ የመለበጥ ሙከራ' ሲሉ ተችተውታል።

ሴቶችን ከመንቀሳቀስ የሚያግደው መተግበሪያ ሊመረመር ነው

ጥቂት ቢሆኑም የሕግ አውጪው ሸንጎ አባላትም ድምጻቸውን አሰምተዋል።

"ሁሉንም ሥልጣኖች በአንድ ሰው መዳፍ እያስጨበጥን ነው። ይህ እየሆነ ያለውም ሕዝባችን ዳቦ፣ ነጻነትና ማኅበራዊ ፍትህን እንድናቀርብለት እየጠበቀን ባለበት ጊዜ መሆኑ ያሳዝናል" ብለዋል አሕመድ ታንታዊ የተባሉ የሕዝብ እንደራሴ።

አልሲሲ እንደ ጎርጎሮሲያዊያኑ በ2013 በመፈንቅለ መንግሥት ሥልጣን ከያዙ በኋላ የተቃውሞ ድምጾችን ሁሉ በመደምሰስ የድጋሚ ምርጫን 97 በመቶ ድጋፍ አግኝቼ አሸንፊያለሁ ብለው ካወጁ ጥቂት ዓመታት ተቆጥረዋል።

ተያያዥ ርዕሶች