እስራኤል ያሰናበተችው ኒጀራዊ ኑሮውን በኢትዮጵያ አየር መንገድ ተርሚናል ውስጥ አድርጓል

ኢሳ ሙሃመድ የእስራኤል ባንዲራ ይዞ

እስራኤል ወደ ሀገሩ እንዲመለስ የላከችው ኒጀራዊ ሀገሩ አልቀበልም ስላለችው፣ ከኅዳር ወር ጀምሮ በቦሌ አየር ማረፊያ ተርሚናል ውስጥ ተቀምጦ ይገኛል።

የ24 ዓመቱ ኢሳ ሙሃመድ ለቢቢሲ እንደተናገረው፣ "ይኸው እዚህ በአየር መንገዱ ውስጥ በመጥፎ ሁኔታ ላይ እገኛለሁ። ምንም ነገር የለም፤ ምንም" ብሏል።

የሙሐመድ ዕድለቢስነት የጀመረው ባለፈው ዓመት ሚያዚያ ወር ላይ እስራኤል ውስጥ ያለሕጋዊ ፈቃድ ሲኖር ከተያዘ ጊዜ ጀምሮ ነው።

ከ2011 ጀምሮ በእስራኤል ይኖር ነበር። የተሻለ ሕይወት አገኛለሁ በሚል ሀገሩን ለቅቆ የወጣው በ16 ዓመቱ እንደሆነ ይናገራል።

እርሱ እንደሚለው እግሩ እስራኤልን ከመርገጡ በፊት ለሕገወጥ አዘዋዋሪዎች በግብፅና በሊቢያ አድርገው ወደ እስራኤል እንዲወስዱት ከፍሎ ነበር።

አንድ ጊዜ እግሩ ቴል አቪቭን ከረገጠ በኋላ ያገኘውን ሥራ እየሠራ የዕለት ጉርሱን ያገኝ ነበር። በ2018 እስራኤል ውስጥ ያለሕጋዊ ወረቀት ነው የምትኖረው ተብሎ በቁጥጥር ሥር ሲውል በአንድ የከረሜላ ፋብሪካ ውስጥ ነበር የሚሠራው።

"ታከለ ኡማ አዲስ አበባን መምራት የለባቸውም" እስክንድር ነጋ

ለበርካታ ወራት በማቆያ ሥፍራ ከተቀመጠ በኋላ፣ ኅዳር ወር ላይ እስራኤል በአስቸኳይ የጉዞ ሰነድ አዘጋጅታ በኢትዮጵያ አየር መንገድ በአዲስ አበባ አድርጎ ወደ ሀገሩ ኒጀር እንዲገባ አሳፈረችው። ነገር ግን ሀገሩ ሲደርስ የኒጀር መንግሥት የጉዞ ሰነድህ የተጭበረበረ ነው በማለት አላስገባም አሉት።

"ኒጀር ውስጥ አልፈለጉኝም፣ ሊቀበሉኝ አልፈለጉም" ይላል መሐመድ።

በኒጀር ለሳምንታት ታግቶ ከቆየ በኋላ 'በል ወደ መጣህበት እስራኤል' በማለት ላኩት። እስራኤል ግን በጭራሽ በማለት በድጋሚ ወደመጣህበት ብላ ላከችው።

"እጅና እግሬን አስረው አልቀበልም ወዳለችኝ ሀገሬ ኒጀር በድጋሚ ላኩኝ" ይላል የ24 ዓመቱ ሙሀመድ።

በዚህ መሀል ኒጀር ለሁለተኛ ጊዜ አላቅህም ብላ አላስገባም በማለት ስትመልሰው አዲስ አበባ ቦሌ አየር ማረፊያ እያለ እስራኤል የሰጠችው የጉዞ ሰነድ ጊዜው አለፈበት፤ ተቃጠለ።

እስራኤል አፍሪካዊያን ስደተኞች እንዲወጡ አዘዘች

እስራኤል ካገር አልወጣም ያሉ ኤርትራውያን ስደተኞችን አሰረች

ይህ የሆነው ባለፈው ኅዳር ወር ነው። ከዛን ጊዜ ጀምሮ መሄጃ ያጣ መፃተኛ፣ የሰው ሀገር ሰው፣ ሆኖ በቦሌ አየር መንገድ ተርሚናል ውስጥ ይንከላወሳል።

ቢቢሲ የኒጀር የውጭ ጉዳይ ሚኒስትርን ሰነዱ ሀሰተኛ ነው ያለውን ለማጣራት ተደጋጋሚ ሙከራ ቢያደርግም ምላሽ ሊያገኝ አልቻለም።

ሙሀመድ አሁን በመንገደኞች መውጫ በኩል ወዲያ ወዲህ ሲንገላወድ ይውላል። መንገደኞች አልያም ሠራተኞች የሚሰጡትን ምግብ እንደሚመገብም ይናገራል።

Image copyright Getty Images

"የአየር መንገዱ ሠራተኞች ምግብ ይሰጡኛል። ሁሉም ቀን ለኔ ተመሳሳይ ነው፤ ግን ሳላመሰግናቸው አላልፍም" ይላል።

የሚተኛው ደግሞ በአየር መንገዱ ተርሚናል በሚገኘው የፀሎት ክፍል አንድ ጥግ ሻንጣውና አነስተኛ መስገጃውን በማንጠፍ ነው።

"አየር መንገድ ውስጥ መቆየት አልፈልግም ምክንያቱም አየር መንገዱ ሀገሬ አይደለም" ይላል።

የእስራኤል ኢሚግሬሽን ለቢቢሲ በጻፈው ደብዳቤ ሙሐመድ ከእስራኤል ለቅቆ እንዲወጣ የተደረገው በሀገሪቱ ውስጥ በሕገወጥ መልኩ ገብቶ በመገኘቱ እንደሆነ አረጋግጧል።

ከሀገሩ ለቅቆ እንዲወጣ የሰጠውም ሰነድ ሕጋዊ እንደሆነ እና ለውጪ ሀገር ዜጎች የሚሰጥ ሕጋዊ 'ሊሴ ፓሴ' ወረቀት እንደሆነም አብራርቷል።

ሙሐመድ ከኒጀር ከእስራኤልና ከኢትዮጵያ መንግሥት ኃላፊዎች ጋር የጠየቁትን ሁሉ በማድረግ መተባበሩን ይናገራል። ነገር ግን ጉዳዩ መቋጫ ሊገኝለት አልቻለም።

መባረር ወይም እስር የሚጠብቃቸው ስደተኞች በእስራኤል

ከእስራኤል የሚባረሩ ስደተኞች ለአደጋ እየተጋለጡ ነው

ስደተኞችን እጇን ዘርግታ በመቀበል መልካም ስም ያተረፈችው ኢትዮጵያ የሙሀመድ ጉዳይ አጣብቂኝ ውስጥ የጣላት ይመስላል።

ስማቸው እንዲገለፅ ያልፈለጉ አንድ የኢሚግሬሽን ጉዳዮች ኃላፊ እንደሚሉት በመሀመድ ጉዳይ እጃቸውን ማስገባት የሚችሉት በኢትዮጵያ ለመቆየት ጥገኝነት ከጠየቀ ብቻ ነው። ይህንን ለማድረግ ደግሞ መሀመድ ፈቃደኛ አይደለም።

"ይህ የራሱ ጉዳይ ነው። ስለ ክብሩ እንጨነቃለን፤ ሐሳቡን ቀይሮ የጥገኝነት ጥያቄውን ለማቅረብ ፈቃደኛ ከሆነ ደግመን እንጠይቀዋለን፤ ይህንን ብቻ ነው ልናደርግ የምንችለው" ብለዋል።

ሙሀመድ ግን ኢትዮጵያ ውስጥ መቆየት አይፈልግም። ወደ ሀገሩ ኒጀር መመለስ ወይም ደግሞ እስራኤል መሄድ ነው የልቡ መሻት።

በዚህ ዘገባ ላይ ተጨማሪ መረጃ