«በስልክዎ ታካሚና አካሚ እናገናኛለን» ሥራ ፈጣሪው ወጣት መላኩ ኃይለማርያም

ሥራ ፈጣሪው ወጣት መላኩ ኃይለማርያም

በሜዲካል ላቦራቶሪ ሳይንስ እና በሂውማን ኒውትሪሽን የትምህርት ዘርፎች ዲፕሎማ እና ዲግሪ አለው፤ የሕክምና ባለሙያው መላኩ ኃይለማርያም።

«ከላቦራቶሪ ቴክኒሺያንነት፣ የሽያጭ ባለሙያ እስከ ማርኬቲን ማኔጀርነት ለ10 ዓመታት ያክል ስሠራ ቆይቻለሁ» ይላል።

ታድያ እነዚህ ያለፉት አሥር ዓመታት የሕክምና መስጫ ተቋማትንና የሚሠጡትን አገልግሎት በቅጡ እንዲረዳ አድርገውታል። «በተለይ ሆስፒታሎች፣ ክሊኒኮች እና ላቦራቶሪዎች እንዴት እንደሚሠሩ እና ያለባቸውን ክፍተት ለመርዳት ያገዙኝ ዓመታት ናቸው።» ይላል።

ሞባይል ለኢትዮጵያ እናቶችና ህፃናት ጤና

የሕክምና ዕቃዎችን አስመጥቶ በማከፋፈል ሥራ በርካታ ጊዜያትን ያሳለፈው መላኩ «ያላዳረስኩት ሆስፒታልና ክሊኒክ የለም» ሲል የስራ ልምዱን ይናገራል።

«በዚህ ሥራዬ ወቅትም በሕክምናው ዘርፍ ያሉ ክፍተቶችን ለማየት እሞክር ነበር፤ ይህ ነው ወደዚህ የሥራ ፈጠራ እንዳመራ የገፋፋኝ» ባይ ነው መላኩ።

'የመረጃ ኤግዚቢሽን'

'ኢትዮሜዶን.ኮም' ይሰኛል መላኩ የሰራው ድረ-ገፅና የተንቀሳቃሽ ስልክ መተግበሪያ (አፕሊኬሽን)።

የመላኩ ዓላማ አካሚና ታካሚን ማቀራረብ ነው፤ የሕክምና ዕቃ አስመጪዎችን ከገዢዎች ማገናኘት፤ ሰውን በጤና መረጃ ማርካት።

አዲስ አበባ ውስጥ የሕክምና ዕቃዎች እንዲሁም ተፈላጊ መድሃኒቶችን በቀላሉ ማግኘት ዘበት ነው። እግር እስኪቀጥን ተፈልጎ ላይገኝ ይችላል። አሁን አሁን ተፈላጊ የሕክምና ባለሙያን ከማግኘት ተጨማሪ ፕላኔት ማግኘት ይቀላል በማለት የሚቀልዱ አሉ።

የመላኩ ሃሳብ እነዚህን ችግሮች መቅረፍ ነው፤ ዋና ከተማዋ አዲስ አበባ ላይ ብቻም ሳይሆን ክፍለ ሃገራትንም ጭምር።

በርካቶች ከምጥ ይልቅ በቀዶ ህክምና መውለድን እየመረጡ ነው

«የሕክምና ዕቃዎችን በተመለከተ ከዚህ በፊት የተለመደው ኤግዚቢሽን ተዘጋጅቶ፤ አቅራቢዎችም ገዢዎችም በአካል ተገናኝተው መደራደር ነው። እኔ የሠራሁት ድረ-ገፅ ግን አቅራቢዎችና ገዢዎችን ሰዎች እጃቸው ላይ ባለ ተንቀሳቃሽ ስልክ የሚያገናኝ ነው።»

አያድርገውና ህመም ገጠመዎ እንበል። ለዚህ በሽታዎ የሚሹት ደግሞ 'ስፔሻሊስት' ሐኪም ነው። ይህ ሐኪም የት እንደሚገኝ አሊያም ለጤና ችግርዎን ትኩረት ሰጥቶ የሚያክም ሆስፒታል ወይም ክሊኒክ የቱ እንደሆነ ማወቅ ቢሹ ማድረግ ያለብዎና ትልቁ ነገር ተንቀሳቃሽ ስልክዎን መዘዝ አድርጎ በይነ-መረብን መቃኘት ነው።

በድረ-ገፁ 'ሄልዝኬር' በተሰኘው ምዕራፍ ሥር አሁን ላይ በርካታ ሆስፒታሎች፤ ልዩ ክሊኒኮች እና ላቦራቶሪዎች ይገኛሉ። ተጠቃሚዎች ባሻቸው ጊዜ የሚፈልጉትን ዓይነት የሕክምና አገልግሎት የሚሰጥ ጣቢያ የሚያገኙበት ገፅ ነው መላኩ የሠራው።

የተንቀሳቃሽ ስልክ መተግበሪያውን (አፕሊኬሽን) የሠራው መላኩ 'አፕሊኬሽኑ' ሊጠናቀቅ የቀረው ጥቂት ጊዜ እንደሆነ በመግለፅ በቅርቡ አንድሮይድ እና አይኦኤስ በተሰኙ የስልክ ዓይነቶች ላይ በቀላሉ እንደሚገኝ ያስረዳል።

ሴቶችን ከመንቀሳቀስ የሚያግደው መተግበሪያ ሊመረመር ነው

«ማንኛውም ሰው ካለበት ሆኖ የፈለገውን የሕክምና ዕቃ ማዘዝ ይችላል። ጨረታ ተብሎ እየወጣ ነገሮች እንዳይሆን እንዳይሆን ሲሆኑ አይቻለሁ። ድረ-ገፁ ላይ ግን ትክክለኛው መረጃ ነው የሚቀመጠው።»

አልፎም የመላኩ 'አፕሊኬሽን' የእያንዳንዱን የጤና መስጫ ተቋም ድረ-ገፅ ጋር (ካላቸው) ይይዛል። የሕክምና ዕቃ አስመጪዎችም ጭምር።

ፈተና. . .

መላኩ በበይነ መረብ እገዛ የሕክምና ዕቃ አቅራቢዎችን ከፈላጊዎች፤ ታካሚዎችን ከአካሚዎች ያገናኛል። ታድያ እኒህን ሰዎችን ማግኘትና ማገናኘት ቀላል እንዳልሆነ እሙን ነው። ለዚያውም ወጣ ገባ በሚል 'ኢንተርኔት' አገልግሎት።

መላኩ «ትልቁ ፈተና የሕክምና ተቋማትንና የሕክምና ዕቃ አስመጪዎችን መመዝገብ ነው። አገልግሎት ሰጪዎቹ ምርትና አገልግሎታቸውን በድረ-ገፃችን እንዲያስተዋውቁ ማድረግ ትልቅ ፈተና ነው።» ይላል።

ሆስፒታሎች እና የሕክምና ዕቃ አቅራቢዎች አሁንም እንደ ቴሌቪዥን ያሉ 'ባህላዊ' የማስታወቂያ ማስነገሪያ መንገዶችን እንደሚመርጡ መላኩ አይሸሽግም።

ቀዶ ህክምና በአፍሪካ ስጋት መሆኑ ከፍ ብሏል

«እርግጥ ነው አሁን ላይ የኢንተርኔት አገልግሎቱ የተሻለ ነው። ቢሆንም ድርጅቶች ኢንተርኔት ቢቋረጥስ እያሉ ይጠይቁናል። ለዚህ ነው ውል ከምንፈፅማቸው ድርጅቶች ጋር የዋስትና ስምምነት ልንደርስ የሆነው። ይህ ማለት ኢንተርኔት ቢቋረጥ ድርጅቶቹ ለድረ-ገፁ ከሚከፍሉት ክፍያ ታስቦ ይመለስላቸዋል» ሲልም ያስረዳል።

ምንም እንኳ የኢትዮጵያ ኢንተርኔት ጉዳይ እና የተቋማት ወደ ድረ-ገፅ እና አፕሊኬሽኖች ለመምጣት ማመንታት ችግር ቢሆንበትም የተጠቃሚዎች ከጊዜ ጊዜ እየጨመረ መምጣት ተስፋ እንደሚሰጠው መላኩ ይናገራል።

ምንም እንኳ የሕክምና አቅራቢ ድርጅቶች የሚከፍሉት የተወሰነ ክፍያ ቢኖርም፤ አገልግሎታቸውን ድረ-ገፁ ላይ ማስተዋወቅ የሚሹ የህክምና መስጫ ተቋማት ምንም ዓይነት ክፍያ እንደማይጠየቁ መላኩ ይናገራል። ምክንያቱን ሲገልጽ ደግሞ ድረ-ገፁ "በዋነኛነት ማሕበረሰቡን እንዲያገለግል ስለምንሻ ነው" ይላል።

የኢንተርኔት ወጣ ገባ ማለት እየፈተነውም ቢሆን፤ የሕክምና መስጫ አገልግሎት ተቋማት ድረ-ገፁን ለመቀላቀል እያመነቱም ቢሆን፤ መላኩ በድረ-ገፅና 'አፕሊኬሽን' ታካሚና አካሚን ለማገናኘት አዲስ ነገር ይዞ ብቅ ብሏል።