'አምብሮ' ከኢትዮጵያ እግር ኳስ ፌደሬሽን ጋር ተፈራረመ የሚሉና ሌሎች አጫጭር ዜናዎች

የአምብሮና የኢትዮጵያ እግር ኳስ ፌደሬሽን መለያ

የፎቶው ባለመብት, soccerethiopia

ኢትዮጵያ

አምብሮ የተሰኘው የእግርኳስ ትጥቆች አምራች ኩባንያ ከኢትዮጵያ እግርኳስ ፌዴሬሽን ጋር የትጥቅ አቅርቦት ውል ተፈራረመ።

ፌዴሬሽኑ ያለፉትን 2 ዓመታት ከጣልያኑ ኤርያ ጋር ሲሰራ የቆየ ሲሆን ቀሪ ውሉን በማቋረጥ ነው መቀመጫውን በእንግሊዝ ያደረገው ግዙፉ የትጥቅ አምራች ኩባንያ- አምብሮ ጋር የ4 ዓመታት ውል የተፈራረመው።

አምብሮ ከዚሀ ቀደም የብራዚል እና እንግሊዝ ብሔራዊ ቡድኖች እንዲሁም ማንቼስተር ዩናይትድን ከመሳሰሉ ታላላቅ ቡድኖች ጋር የሰራ ሲሆን በአሁኑ ሰዓት ኤቨርተን፣ ዌስትሃም፣ ፒኤስቪ እና የመሳሰሉ ክለቦች ጋር እየሰራ ይገኛል።

***

ኢትዮጵያና ጂቡቲ የነዳጅ ማስተላለፊያ ቱቦ ለመገንባት ተስማሙ።

ማስተላለፊያ ቱቦው ከጂቡቲ ዋና ጣቢያ ወደ ኢትዮጵያ የሚያጓጉዝ ሲሆን ከሁለት ዓመታት በፊት የቻይና ኢንቨስትመንት ካምፓኒ ግንባታውን ለማካሄድ ከጂቡቲ ጋር የመግባቢያ ሰነድ ተፈራርመው ነበር።

ካሜሩን

በካሜሩን በታጣቂዎች ተጠልፈው የነበሩ 166 ተማሪዎችና መምህራን መለቀቃቸው ተሰማ።

የተጠለፉበት ምክንያት እስካሁን ግልፅ ያልተደረገ ሲሆን ከ3 ዓመታት ወዲህ ግን በአገሪቱ ባለው የርስ በርስ ግጭት ተመሳሳይ አደጋዎች እያጋጠሙ እንደሆነ ተነግሯል።

ተማሪዎቹ ኩመቦ ከሚገኘው የካቶሊክ ትምህርት ቤት ተጠልፈው የተወሰዱ ሲሆን የትምህርት ቤቱ ኃላፊዎች እንዲለቀቁ ሲደራደሩ ቆይተዋል።

ናይሪያ

የናይጄሪያ ፕሬዚደንት ሙሃመዱ ቡሃሪ ምርጫውን ለማራዘምና ለማስተጓጎል ለሚንቀሳቀሱ ሁሉ የአገሪቱ የፀጥታ ኃይል ርህራሄ እንዳያሳዩ ትዕዛዝ መስጠታቸውን አስታወቁ።

ፕሬዚደንቱ አክለውም "የምርጫ ሳጥኖችን፣እንዲሁም ሌሎች የምርጫ ቁሳቁሶችንለመስረቅ፣ለማውደም የምትጥሩ ሕይወታችሁን ትከፍሉበታላችሁ" ሲሉ አስጠንቅቀዋል።

ይህን ያሉት የካቢኔ አባላቶቻቸውን በጠሩት የአስቸኳይ ስብሰባ ወቅት ነው።

ዚምባብዌ

የዚምባብዌ ፍርድ ቤት ተቃዋሚው ፖለቲከኛ ቴንዳይ ቢቲ 7 ቀናትን በእስርቤት እንዲያሳልፉ አሊያም 200 የአሜሪካ ዶላር እንዲከፍሉ በየነ።

ፖለቲከኛው ውሳኔው የተላለፈባቸው የምርጫ ህግን በመጣስ " የባለፈው ዓመት ምርጫ አሸናፊ ኔልሰን ቻሚሳ እንጂ ፕሬዚደንት ኤመርሰን ምናንጋግዋ አልነበሩም በማለት ይፋዊ ንግግር በማድረጋቸው ነው።

ሞዛምቢክ

የሞዛምቢክ የቀድሞ ፕሬዚደንት አርማንዶ ልጅ 2 ቢሊየን ዶላር የመንግስት ገንዘብ በማጭበርበር በቁጥጥር ስር ዋለ።

ገንዘቡ አባቱ በስልጣን ላይ በነበሩ ጊዜ የተለያዩ ፕሮጀክቶችን ለማካሄድ ከመንግስት በብድር የተወሰደ ነው ተብሏል።

የፕሬዚደንቱ ልጅ በአራት ቀናት ውስጥ በተመሳሳይ ወንጀል ተጠርጥረው ከተያዙ ግለሰቦች መካከል 9ኛው ነው።

ሳዑዲ አረቢያ

ሳዑዲ አረቢያ የፓኪስታንን ኢኮኖሚ ለመደገፍ የ20 ቢሊዮን ዶላር ገንዘብ ድጋፍ ተፈራረመች።

ስምምነቱ በነዳጅ፣ በማዕድንና በኃይል አቅርቦት ዙርያ የሚያተኩር ሲሆን ያጋጠማትን የኢኮኖሚ ቀውስ ይፈታላታልም ተብሏል።

የፓኪስታን ብሔራዊ ባንክ በካዝናዬ የቀረኝ 8 ቢሊዮን ዶላር ብቻ ነው ሲል ማስታወቁ አይዘነጋም።

ህንድ

በህንድ ካሽሚር በታጣቂዎችና በመንግስት ወታደሮች መካከል በተደረገ የተኩስ ልውውጥ አራት ወታደሮች መገደላቸው ተሰማ።

ግጭቱ ባለፈው በአጥፍቶ ጠፊ ቦምብ ፍንዳታ 40 ፖሊሶች የሞቱበት ፑልዋማ ግዛት የተፈጠረ ሲሆን ይህንንም ተከትሎ በህንድና በፓኪስታን ውጥረት ነግሷል።

እንግሊዝ

ሰባት የብሪታኒያ የሰራተኞች ፓርቲ የፓርላማ አባላት መልቀቂያ ማስገባታቸው ተሰማ።

የፓርላማ አባላቱ መልቀቂያ ያስገቡት ፓርቲው ጀርሚ ኮርቢን በተባለው መሪያቸው አመራር ሰጭነት ለሀገሪቱ የሚጠበቅበትን ኃላፊነት እየተወጣ እንዳልሆነ ተቃውሟቸውን ለመግለጽ ነው ተብሏል።