ሳሙኤል ተፈራ፡ የ22 ዓመት ክብረ ወሰንን ያሻሻለው የ19 ዓመቱ ወጣት

ሳሙኤል ተፈራ Image copyright Getty Images

የ19 ዓመቱ አትሌት ሳሙኤል ተፈራ ቅዳሜ በበርኒንግሃም እንግሊዝ ተካሂዶ በነበረው የቤት ውስጥ የሩጫ ውድድር የዓለም ሪደርድ በማሻሻል አሽንፏል።

በ1500 ሜትር የቤት ውስጥ ውድድር በሞሮኳዊው አትሌት ሂሻም አልገሩሽ እአአ 1997 ተይዞ የነበረዉን 3፡31፡18 ክብረ ወሰን በ14 ማይክሮ ሰከንዶች በማሻሻል አትሌት ሳሙኤል ተፈራ አሸናፊ መሆን ችሏል።

''አሁንም ኢትዮጵያን ወክዬ መሮጥ እፈልጋለሁ'' አትሌት ፈይሳ ሌሊሳ

አትሌቱ የቤት ውስጥ ሩጫን ከዚህ በፊት አሸንፎ ስለማያውቅ የማሸነፍ ግምት አልተሰጠውም ነበር። ይልቁንም ባለፉት ሳምንታት ውድድሮቹን በድል ሲያጠናቅቅ የቆየው ዮሚፍ ቀጄልቻ ከፍተኛ የአሸናፊነት ግምት ተሰጥቶት ነበር። ዮሚፍ በዚህ ውድድር 3፡31፡58 በመግባት የግሉን ምርጥ ሰዓት ማስመዝገብ ችሏል።

"በጣም ደስተኛ ነኝ፤ ደስታዬ ይሄ ነው ለማለት ይከብደኛል። ወደዚህ ውድድር የገባሁት በግፊት እንጂ የራሴ ሃሳብ ኖሮኝ አይደለም። የፈጣሪ እርዳታ ነው።" በማለት ሳሙኤል ለቢቢሲ ተናግሯል።

ሳሙኤል በውድድሩ ላይ እንዴት እንደተሳተፈ ሲያስረዳ ''የዓለም ሪከርድን አሻሽላለሁ ብዬ አይደለም ወደ ስፍራው ያቀናሁት። ኔዘርላንድ እና ፈረንሳይ ለነበሩኝ ውድድሮች ላይ ለመሳተፍ ነው ወደ አውሮፓ ያቀናሁት። እኔ ሃሳቤ የነበረው የኔዘርላንድ እና ፈረንሳይ ውድድር ተሳትፌ ወደ ኢትዮጵያ መመለስ ነበር። ነገር ግን እንዳጋጣሚ ሆኖ ይህ ውድድርም አውሮፓ እያለሁኝ የሚካሄድ ስለነበረ በጣም በተጣበበ ሁኔታ ተወዳድሬ ነው ማሸነፍ የቻልኩት።'' ብሏል።

ሳሙኤል ያሻሻለው ሪከርድ እሱ ከመወለዱ በፊት የተያዘ ነበር። አትሌቱ ገና 19 ዓመት ወጣት ሲሆን ይህ ውድድር በማሸነፉ 3ሺህ ዶላር እንዲሁም ሪከርድ በመስበሩ 30ሺህ ዶላር ተሸላሚ ለመሆን በቅቷል።

"ማንም ታሸንፋለች ብሎ የገመተ አልነበረም"

ከዚህ ቀደም ምንም አይነት የዓለም ሪከርዶችን አሻሽሎ እንደማያውቅ የሚያስረዳው ሳሙኤል ለመጀመሪያ ጊዜ ያሻሻለው ሪከርድ ለሌላ ስኬት እንደሚያነሳሳው እና ወደፊትም ጠንክሮ እንዲሰራ ብርታት እንደሚሆነው ይናገራል።

በዚህ ውድድር በሁለተኛ ደረጃ ያጠናቀቀው ዮሚፍ፤ ከሳምንት በፊት በኒው ዮርክ የአንድ ማይል ሩጫ ተይዞ የነበረውን ክብረ ወሰን በአንድ ማይክሮ ሰክንድ ዘግይቶ በመግባቱ ሳያሻሽል ቀርቷል። በዚህም ምክንያት ይህን ውድድር ያሸንፋል ተብሎ ከፍተኛ ግምት ተሰጥቶት የነበረው ዮሚፍ ቀጄልቻ ነበር። የሳሙኤልም ሃሳብ ይሄ ነበር።

"ለአንድ ማይክሮ ሰከንድ ሳያሻሽል መቅረቱ በጣም አሳዝኖኝ ነበር። በዚህም ውድድር ዮሚፍ ያሸንፋል የሚል ግምት ነበረኝ። እኔም የዮሚፍ ጥሩ ተፎካካሪ እንደምሆን እራሴን አሳምኜ ነበር የገባሁት" ይላል ሳሙኤል።

ሳሙኤል ማን ነው?

  • ሥም ፡ ሳሙኤል ተፈራ ነሜ
  • የትውልድ ሥፍራ፡ ምዕራብ ሸዋ ሚዳ ቀኝ ወረዳ
  • በ2007 የ10 ኛ ክፍል ትምህርቱን በማቋረጥ ፊቱን ወደ አትሌቲክስ አዞረ
  • በ2008 የኦሮሚያ እንስሳትና ደን ጥበቃ ክለብን ተቀላቀለ
  • በ2009 የአለም ሻምፒዮና ቢሳተፍም ውጤታማ ሳይሆን ቀረ
  • በ2010 የአለም የቤት ዉስጥ ሩጫ በ1500 ሜትር የወርቅ ተሸላሚ ሆኗል

ተያያዥ ርዕሶች

በዚህ ዘገባ ላይ ተጨማሪ መረጃ