የኦነግ ጦር ወደተዘጋጀለት ስፍራ መግባት ጀመረ የሚሉ እና ሌሎች አጫጭር ዜናዎች

የኦነግ ታጣቂዎች

ኢትዮጵያ

በምዕራብ ኦሮሚያ የሚገኙ የኦሮሞ ነጻነት ግንባር ታጣቂዎች ትጥቅ ፈትተው ወደ ጦር ካምፖች ከመግባታቸው በፊት በጊዜያዊነት ወደ ተዘጋጀላቸው ስፍራ እየገቡ እንደሆነ አባ ገዳ በየነ ሰንበቶ ለቢቢሲ ተናገሩ።

መንግሥትን እና ኦነግን ለማስታረቅ በተቋቋመው የቴክኒክ ኮሚቴ ሰብሳቢ የሆኑት አባ ገዳ በየነ ሰንበቶ እንዳሉት ዛሬ አመሻሽ ጀምሮ ከመንዲ እና ከሌሎች ስፋራዎች የጦሩ አባላት በጊዜያዊነት ወደተዘጋጀላቸው ስፍራ መግባት ጀምረዋል።

''እስካሁን ወደዚህ የመጡትን የወታደሮች ብዛት አልቆጠርንም፤ ይሁን እንጂ በአጠቃላይ እስከ 10ሺህ ጦር እንጠብቃለን'' የሚሉት አባገዳ ሰንበቶ በቅርቡ ጦሩ ከጊዜያዊ መቆያው ወደተዘጋጀለት የጦር ካምፕ እንደሚገባ ጨምረው ተናግረዋል።

***

በቂሊንጦ ማረሚያ ቤት ላይ በደረሰው ቃጠሎ በተነሳው ረብሻ ምክንያት የሰብዓዊ መብት ጥሰት ፈፅመዋል በሚል የተጠረጠሩ የማረሚያ ቤት የፖሊስ አባላት ላይ ክስ መመስረቱን የአገር ውስጥ መገናኛ ብዙሃን ዘገቡ።

ተከሳሾች በፌደራል ማረሚያ ቤቶች የቂሊንጦ፣ የዝዋይ እና የሸዋ ሮቢት ማረሚያ ቤት በተለያየ የሃላፊነት ደረጃ ሲሰሩ የነበሩ መሆናቸውም ተገልጿል።

ግብጽ

ሦስት የግብጽ ፖሊሶች በአጥፍቶ አጠፊ ቦምብ ሳቢያ ህይወታቸውን አጡ።

ካይሮ ውስጥ ማንነቱ ያልታወቀ ግለሰብ ቦንብ ሊያፈነዳ ሲል ለማስቆም ሲሞክሩ ነበር ፖሊሶቹ የሞቱት።

ኬንያ

የአንድ ወር ልጁን የህክምና ወጪ መሸፈን ባመቻሉ ልጁን ከህክምና መስጫ ደብቆ ለማስወጣት የሞከረው ኬንያዊ አባት ሳይታሰር ቀርቷል። ግለሰቡ ለቀጣይ ሦስት ወራት ምንም አይነት ወንጀል እንዳይፈጽም ከመባሉ ባለፈ የኬንያ ፍርድ ቤት ከባድ ቅጣት ሳይጥልበት ቀርቷል።

ኡጋንዳ

የኡጋንዳው ፕሬዘዳንት ዩዌሪ ሙሴቪኒ የልጃቸውን ወታደራዊ ማዕረግ ወደ ሉተነንት ጀነራል ማሳደጋቸው እያነጋገረ ነው።

ልጁ ባለፉት ስድስት ዓመታት ሦስት ጊዜ ማዕረጉ እንዲሻሻል ተደርጓል። የተሰጠው ማዕረግ ወታደራዊ ብቃቱን አይመጥንም የሚል ትችት እየተሰነዘረ ነው።

ናይጄሪያ

የናይጄሪያ ፕሬዘዳንት ሙሀመዱ ቡሀሪ ሀገር አቀፉን ምርጫ ለማጫበርበር የሚሞክሩ አካላትን ፖሊስ መታገስ የለበትም ብለዋል። ንግግሩ ፖሊሶች ያሻቸውን እርምጃ እንዲወስዱ የሚያነሳሳ ነው ሲሉ የሀገሪቱ ተቀናቃኝ ፓርቲ አባላት ፕሬዘዳንቱን ኮንነዋል።

ህንድ

ህንድ ፓኪስታን ላይ ወታደራዊ እርምጃ ከወሰደች ፖኪስታን በምላሹ ጥቃት እንደምታደርስ እየዛተች ነው።

ባለፈው ሳምንት በህንድ ካሽሚር ግዛት ውስጥ ቦምብ ፈንድቶ 40 የህንድ የጸጥታ ሀይሎች መሞታቸው ይታወሳል። ህንድ ከጥቃቱ ጀርባ ያለችው ፓኪስታን ናት ብትልም ፓኪስታን ክሱን አጣጥላለች።

ሶሪያ

የተባበሩት መንግሥታት በሶሪያ በአይኤስ ቁጥጥር ስር ያለ ግዛት ውሰጥ የሚገኙ ሰዎች እጣ ፈንታ እንዳሳሰበው ገለጸ። በግዛቷ ወደ 200 የሚጠጉ ቤተሰቦች የሚገኙ ሲሆን አብዛኞቹ ሴቶችና ህጻናት ናቸው።

ፌስቡክ

ፌስቡክ መተግበሪያ በመጠቀም ተቀናቃኝ ድርጅቶቹን ይሰልላል የሚል ክስ ቀርቦበታል።

ግዙፉ የቴክኖሎጂ ተቋም የመረጃ ነጻነትን እየተጋፋ ነው ተብሏል። ከዚህ ቀደም 'ስናፕ ቻት' የተባለውን ተቀናቃኝ ለመግዛት ሞክሮ እንደነበር ይታወሳል።