በሸዋ ሮቢት ከተማ የእናትና ልጅን ግድያ ተከትሎ ቁጣ ተቀሰቀሰ

የህዝብ ቁጣ

የፎቶው ባለመብት, Shewa robit kentiba office FB

ዛሬ በሰሜን ሸዋ ዞን ሸዋ ሮቢት ከተማ የእናትና ልጅን ግድያን ተከትሎ የህዝብ ቁጣ ተቀሰቀሰ።

ትናንት የካቲት 12/2011 ዓ.ም ከቀኑ 11፡30 አካባቢ የግድያው ጥቆማ እንደደረሳቸውና የግድያው ምክንያት የፍቅር ግንኙነት እንደሆነ የሚያመለክት መነሻ መረጃ እንዳላቸው የሸዋ ሮቢት ከተማ አስተዳደር ፖሊስ ፅ/ቤት ኃላፊ ኢንስፔክተር ሞገስ ባዬ ለቢቢሲ ተናግረዋል።

ኢንፔክተር ሞገስ እንዳሉት ግድያው በሸዋ ሮቢት ከተማ ልዩ ቦታው 01 ቀበሌ የተፈፀመ ሲሆን አንዲት እናት ከ5 ዓመት ሴት ልጇ ጋር ተገድለው ተገኝተዋል። ተጠርጣሪው በህግ ቁጥጥር ስር የዋለ ሲሆን ከሟች መኖሪያ ቤትም የተዘረፈ ንብረት እንደተያዘ ኢንፔክተሩ ጨምረው ገልፀዋል።

ይሁን እንጂ በርካታ ሰዎች አደባባይ በመውጣት "እርምጃ መወሰድ አለበት፤ በአስቸኳይ ፍርድ ሊሰጥ ይገባል" እያሉ ተቃውሟቸውን እየገለፁ እንደነበር ኢንስፔክተሩ ያስረዳሉ።

ያነጋገርነው መሀመድ አሊ የተባለ የአካባቢው ነዋሪ "ተጠርጣሪውን ከፖሊስ ጣቢያ እናወጣለን፤ እርምጃም እንውስድበታለን" በሚል የህዝብ ቁጣ እንደተቀሰቀሰ ይናገራል።

ሟቾቹ ታፍነው እንደተገደሉ እንደሰማ የሚናገረው መሀመድ ቁጣው ከጠዋቱ 3 ሰዓት ገደማ እንደተቀሰቀሰና ወደ ፀጥታ ኃይሎች ድንጋይ በመወርወር ተቃውሟቸውን እየገለፁ እንደነበርና ከሰዓት በኋላም እንዳልበረደ ገልፆ መንገዶች ዝግ በመሆናቸውም መኪኖች እስከ አመሻሽ ድረስ መንቀሳቀስ አልቻሉም ነበር ብሏል።

ስሟ እንዲገለፅ ያልፈለገች ሌላኛዋ የአይን እማኝ "ሟቿ ህፃን ተማሪ ስለነበረች ለቅሶ በመሆኑ ትምህርት ቤት ልጆች እንዳትልኩ ብለውን፤ ስንወጣ ነው ህዝቡ አደባባይ በመውጣት 'ይገደልልን፤ ፍትህ ይሰጠን' የሚል ቁጣና ጩኸት የሰማነው" ትላለች።

ይህች የአይን እማኝ እንደምትለው እናትና ልጅ በመታፈን ግድያው የተፈፀመባቸው ሲሆን ሌላ የሁለት ዓመት ልጇም ታፍኖ ሻንጣ ውስጥ እንደተገኘም ትናገራለች። "ሟች ትናንት ቀኑን ሙሉ ሳትታይ መዋሏ ያስደነገጣቸው የአካባቢው ነዋሪዎች ማታ ላይ ቤቷን ሲከፍቱ እናትና ልጅ ሞተው ተገኙ" ስትል የነበረውን ሁኔታ ትገልፃለች።

ቁጣውን ተከትሎ እስካሁን በንብረትና በሰው ላይ የደረሰ ጉዳት አለመኖሩን የሚናገሩት ኢንስፔክተሩ በአገር ሽማግሌዎችና በኃይማኖት አባቶች ቁጣው እየበረደ እንደመጣ ነግረውናል።

ኢንስፔክተሩ የግድያውን ምክንያት የሚያጣራ የምርመራ ቡድን የተቋቋመ ሲሆን አጣርተን ሙሉ መግለጫ እንሰጣለን ብለዋል።