ኦዲፒ 'በፌዴራሊዝም አልደራደርም' ሲል ምን ማለቱ ነው?

ኢንጂነር ይልቃል ጌትነትና አቶ ኤፍሬም ማዴቦ
የሰሞኑ የኦዲፓ መግለጫ እንደዋዛ አልታለፈም፤ ለሰፊ የማኅበራዊ ውይይት በር ከፍተ እንጂ። 'በፌዴራሊዝሙ አንደራደርም' የሚለው ሐሳብ በተለይም በአሓዳዊ ፖለቲካ አቀንቃኞች ላይ ቀዝቃዛ ውኃን የቸለሰ ይመስላል።
ኾኖም መግለጫው ለተከፈተ ዘመቻ ምላሽ እንደሆነ በኦዲፒ ተገልጿል፤ ዘመቻው በማን፣ መቼና የት እንደተከፈተ ለይቶ ባይጠቅስም።
ይህ በፌዴራሊዝም ላይ ተከፈተ የተባለው የሐሰት ዘመቻ ሁለት ግብ እንደነበረው የኦዲፒ መግለጫ ጨምሮ ያወሳል።
'የፌዴራል ሥርዓቱ ከዛሬ ነገ መፍረሱ ነው በሚል ብሔር ብሔረሰቦች በጥርጣሬ እንዲመለከቱት ማድረግ ሲሆን ሌላው ደግሞ' ተጨማሪ መብት እንደሚያገኝ እየጠበቀ ያለውን የኦሮሞን ሕዝብ' እንኳንስ ተጨማሪ መብት ይቅርና 'ከዚህ ቀደም ያገኘኸውንም ልታጣ ነው' በሚል ማደናገር ነው ሲል የዘመቻውን ግብ ያትታል።
ለመኾኑ መግለጫዉ ባለፉት ቀናት በሕዝብ ዘንድ ሰፊ መነጋገሪያ ለምን ኾነ? በዚህ ወቅት ይህን መግለጫ ማውጣትስ ለምን አስፈለገ? በተገዳዳሪ ፓርቲዎች ዘንድ መግለጫው ምን ስሜት ፈጠረ? ቢቢሲ የአርበኞች ግንቦት 7 እና የኢሀን አመራሮችን አነጋግሯል።
'ሕዝቡ በምኞት ቀውስ ውስጥ ነው'
ኢንጂነር ይልቃል ጌትነት መግለጫው አነጋጋሪ የሆነው በርካታ ሕዝብ ዶ/ር ዐቢይ አገሩን አንድ አደርጋለሁ የሚሉትን ነገር እንደ ትግል አጀንዳ የምር በመቁጠሩ ይህን ተከትሎ የመጣ "የምኞትና የፍላጎት ቀውስ" ነው ይላሉ።
ዶ/ር ዐቢይ የሚናገሩትን ብቻ በማየት ብዙ ሰው ለውጡ ሥር ነቀል ነው ብሎ አምኖ ነበር። ነገር ግን አሁን የኦዲፒ ትክክለኛ አቋም በተለየም በፌዴራሊዝም ዙርያ የቱ ጋር እንደሆነ ሲታወቅ በሕዝቡ ዘንድ የምኞት ቀውስን እንዳስከተለ ይገምታሉ።
''እንደ ሕዝብ ከደረቅ ሐቅ ይልቅ ምኞታችንን የማመን ደዌ ተጸናውቶናል'' ይላሉ።
"ኢትዮጵያ የሁላችንንም አቋም የምንተገብርባት የሙከራ ቦታ አይደለችም"
መግለጫው በዚህ ደረጃ ለምን አነጋገረ? ምን አዲስ ነገርስ ኖሮት ነው?
እንደ ኢንጅነር ይልቃል አመለካከት በኦዲፒ ዉስጥ አዲስ ነገር አልተፈጠረም። መግለጫውም ቢኾን አዲስ ነገር የለውም።
በኢህአዴግ ዉስጥ እያለም ኦዲፒ የዉስጥ ትግል ሲያደርግ ይህንን ሐሳብ እያራመደ ነው የመጣዉ። ሲጀመርም ኦዲፒ ከህወሓት የሞግዚት አስተዳደር ከመውጣት ውጭ ወትሮም የተለየ ፍላጎት አልነበረዉም።
"እንዲያዉም እውነቱን ንገረኝ ካልከኝ ይሄ ሕገ መንግሥት እንዲሻሻል ከማይፈልጉ ድርጅቶች መካከል ከህወሓትም በላይ ግንባር ቀደሙ ኦዲፒ ነዉ" ይላሉ ኢንጂነር ጌትነት።
የአርበኞች ግንቦት 7 ለአንድነት እና ዴሞክራሲ ንቅናቄ የፖለቲካ ዘርፍ ኃላፊ አቶ ኤፍሬም ማዴቦ በበኩላቸው ፖለቲካዊ ትንቢት መስጠት እንደማይፈልጉ ገልጸው ኾኖም ግን ማንም ቢሆን ለድርድር ዝግ መሆን እንደሌለበት ያስገነዝባሉ።
"አንደራደርም ሲሉ አሁን ያለው የቋንቋ ፌዴራሊዝም ይቀጥል ነው? ወይስ ኢትዮጵያን ከዚህ ፌዴራሊዝም ውጭ ማስተዳደር አይቻልም ማለት ነው? ይህን የማስረዳት የኦዲፒ ዕዳ ነው" ይላሉ።
አቶ ኤፍሬም አክለዉም ኢትዮጵያ ዉስጥ የተለያዩ የፖለቲካ ፓርቲዎች የየራሳችን አቋም አለን። እና ኢትዮጵያ የሁላችንንም አቋም የምንተገብርባት የሙከራ ቦታ አይደለችም። ስለዚህ አንድን ሐሳብ አንስቶ አንደራደርም የሚለዉ ነገር ለእኔ ትክክለኛ ሐሳብ ነዉ ብዬ አላምንም ብለዋል።
የመግለጫው መቼት?
ሌላው ውይይትን ያጫረው መግለጫው የወጣበት ጊዜና በአገሪቱ የተለያዩ አካባቢዎች ያለው ነባራዊ ሁኔታ ነው።
ከዚህ አንጻር በዚህ ወቅት ይህ መግለጫ ለመውጣቱ ገፊ ምክንያቶች ሲሉ የሚጠቅሷቸው ሦስት መላምቶች አሏቸው፤ ኢንጂነር ይልቃል።
''ጠቅላይ ሚኒስትሩ የጅማዉን ጨምሮ በተለያዩ ጉባኤዎች ከጠላት ጋር እያበራችሁ ኦሮሞ አገር መምራት አይችልም እያስባለችሁን ነው በማለት ከኦነግ በላይ ለኦሮሞ ተቆርቋሪ እንደሆኑ ለማሳየትና አሁን ያለውን መንግሥት የኦሮሞ መንግሥት መሆኑን ለመግለጽ ጥረት አድርገዋል'' ይላሉ።
ምናልባት በንንግራቸው አሀዳዊ የሚመስሉት ጠቅላይ ሚኒስትሩ ከፌዴራሊዝም እያፈገፈጉ ናቸው በሚል ከኦነግ ደጋፊዎች ሊያርቃቸው ይችላል። አንደኛው የመግለጫው አንድምታ ይህንን ድጋፍ መልሶ ማጠናከሪያ ይመስላል።
ሁለተኛዉ ህወሓት በ44ኛ የምሥረታ በዓሉ የብሔር ብሔረሰቦች መብትና ሕገ መንግሥቱን የምትደግፉ ሰዎች ከጎኔ ኾኑ፣ ፌዴራሊዝሙን እናድን ብሎ ያወጣው ጥሪ የፈጠረው ግፊት ነው ይላሉ ኢንጂነሩ።
''ሦስተኛው ምክንያት ከግንቦት 7 ሰዎች ጋር ያለውን መቀራረብ በማየት የኦሮሞ አክቲቪስቶች ሥልጣን አስወሰዳችሁብን ሲሏቸዉ ስለነበር ለዚያ ምላሸ ለመስጠት ይመስላል።''
መግለጫው አርበኞች ግንቦት 7 ላይ ያነጣጠረ ነው?
መግለጫው አርበኞች ግንቦት 7 ላይ ያነጣጠረ ይሆን? በሚል የተጠየቁት አቶ ኤፍሬም ማዴቦ መግለጫው የእሳቸዉን ፓርቲ እንደማይመለከት፤ አርበኞች ግንቦት 7ም የፌዴራሊዝም ጸር ሳሆን ደጋፊ መሆኑን አውስተዋል።
"ኦዲፒ እኛ ላይ የሚያነጣጥርበት ምንም ምክንያት የለም። ይልቅ እኛና ኦዲፒ የምናነጣጥረው ወደ ጋራ ጠላት ነው" ሲሉ በመግለጫው አለመደናገጣቸውንም ጭምር ገልጸዋል።
በአንድም ሆነ በሌላ ቅርጹ ፌዴራሊዝምንና ያልተማከለ አስተዳደርን የማይደግፍ ጉልህ ፓርቲ በአገሪቱ በሌለበት ሁኔታ ኦዲፒ ይህን መግለጫ ሲያወጣ ማንን ታሳቢ አድርጎ እንደሆነ አለመገለጹ አንዱ መነጋገሪያ ነው።
ከዚህም በላይ ኦዲፒ አልደራደርበትም የሚለው ፌዴራሊዝም አሁን ያለውን የቋንቋ ፌዴራሊዝም ነው ወይስ ሌላ ማንኛውንም አማራጭ የፌዴራሊዝም ቅርጽ የሚለውም ሌላው ያልተመለሰ ጥያቄ ነው።
አሁን ያለው ፌደራሊዝምን ቅርጽ መቀየር ያስፈልጋል ብለው የሚያምኑት ኢንጂነር ይልቃልም የኦዲፒ መግለጫ ግን የቋንቋ ፌዴራሊዝምን ባለው ሁኔታ ለማስቀጠል ያለመ ስለመሆኑ አይጠራጠሩም።
"ደጋግመን ስለወደቅን በሕዝቡ ዘንድ እውነታውን ከመውሰድ ይልቅ ምኞታችንን የማመን አዝማሚያ አለ። ጥሬ ሐቁ ግን ኦዴፒ በፌዴራል ሥርዓቱ አንደራደርም ሲል ይህን ቋንቋን መሠረት ያደረገ ፌዴራሊዝም አሁን ባለው ቅርጽ እንዲቀጥል አደርጋለሁ ማለት እንጂ ሌላ ሊሆን አይችልም" ይላሉ።
ምክንያቱን ሲያስረዱም "ኦዲፒ አሁን ባለው የፌዴራሊዝም ቅርጽ መቀጠልን የሚሻውና ይህ ነገር ያለቀለት አድርጎ የሚያየው ወደ 'ኦቶኖሚ'፣ ወደ ኮንፌዴራሽን መሄድ ብሎም ወደ መገንጠለም ለመሄድ ሁለተኛ አጀንዳ ይዞ ስለሚንቀሳቀስ ይህን ፌደራሊዝም ማስቀጠል ይፈልጋል" ይላሉ ኢንጅነር ይልቃል።
"የዜግነት ፖለቲካና ፌዴራሊዝም አይጣሉም"
ብዙውን ጊዜ የአሐዳዊነት ጠበቃና ከፌዴራሊዝሙ በተጻራሪ እንደቆመ ፓርቲ ተደርጎ የሚታሰበው ግንቦት 7 ከቋንቋ ፌዴራሊዝም እንጂ ካልተማከለ የአስተዳደር አወቃቀር ጋር ጥል የለኝም ይላል። ብዙዎች ግን ፓርቲውን በዚያ መንገድ ለማየት ይቸገራሉ ወይም አይፈልጉም።
ቃል አቀባዩ አቶ ኤፍሬም እንደዚያ የሚያስቡን "የሐሳብ ድሀዎች" ናቸው ይላሉ።
"የዜግነት ፖለቲካ በአሐዳዊ ሥርዓት ውስጥ ሊገለጽ ይችላል፤ ፌዴራል በሆነ ሥርዓት ውስጥም ሊገለጽ ይችላል። የዜግነት ፖለቲካ በፌዴራል ሥርዓት ውስጥ አይኖርም ብሎ ማሰብ ግን ስህተት ነው።"
አበክረን ከተናገርናቸው ነገሮች ውስጥ ኢትዮጵያን ከአሁን በኋላ ካልተማከለ ሥርዓት ውጭ መምራት እንደማይቻል ነው። ነገር ግን ብዙ ዓይነት ያልተማከሉ ሥርዓቶች አሉ። ከነዚያ ውስጥ እኛ ለኢትዮጵያ የሚበጃት ፌዴራሊዝም ነው ብለን እናምናለን። "በፌዴራሊዝም አያምኑም የሚሉን ሰዎች የመጨረሻ ቃላችን አሁንም ሙሉ በሙሉ እናምናለን ነው" ብለዋል፤ አቶ ኤፍሬም።
"ኢትዮጵያን ከቋንቋ ይልቅ ወደ ኅብረ ብሔራዊ ፌዴራሊዝም ብንለውጣት ጥሩ ነው ብለን በጥቅሉ እናምናለን፤ እንዴት ይሄ ተግባራዊ ይሆናል የሚለው ግን ከእኛም በላይ ነው፤ በእኛ ድርጅት ብቻ የሚፈጸም ነው ብዬም አላምንም" ይላሉ።
በቅርቡ አቶ አንዳርጋቸው ጽጌ በደብረማርቆስ ፌዴራሊዝሙ መፍረስ እንዳለበት የሚያሳስብ አስተያየት መስጠታቸውን በተመለከተ ከቢቢሲ የተጠየቁት አቶ ኤፍሬም ሁኔታውን አስተባብለዋል።
"እኔና አንዳርጋቸው አንድ ድርጅት ውስጥ ነን፤ በፌዴራሊዝም ላይ የተለያየ አቋም ሊኖረን አይችልም። [እሱ] ፌዴራሊዝሙ ይፍረስ አላለም። አሁን ያለው የዘርና የቋንቋ አደረጃጀት ይፍረስ ነው ያለው" ብለዋል።
'አንደራደርምን' ምን አመጣው?
የኦዲፒ መግለጫ የቆሰቆሳቸው ሐሳቦች በፌዴራሊዝም ጉዳይ ላይ ብቻ የሚያጠነጥኑ አይመስልም። ከመግለጫው ይዘት ይልቅ "ለድርድር ዝግ ነኝ" ማለቱ ይበልጥ ያሰጋቸው ጥቂት አይደሉም።
ለየትኛውም አማራጭ ሐሳብ በሩ ክፍት መሆኑ የሚታሰበው የዐቢይ አስተዳደር "አንደራደርም" የሚል ጠጣር ቃል፣ ያውም ጠቅላይ ሚኒስትሩ ከሚመሩት መሪ- ፓርቲ መስማት ብዙዎችን ሳይጎረብጣቸው አልቀረም።