'አስጸያፊ' ከመባል ኦስካር ወደማሸነፍ

የንጽህና መጠበቂያው ሞዴስ ሲሠራ
የምስሉ መግለጫ,

የንጽህና መጠበቂያው ሞዴስ ሲሠራ

የሴቶች ንፅህና መጠበቂያ (ሞዴስ) በምትሰራ አንዲት ወጣት ሴት ህይወት ላይ ያተኮረው ዘጋቢ ፊልም ኦስካር አሸንፏል።

ትላንት ባልተለመደ ሁኔታ ያለ አስተዋዋቂ የተካሄደው የኦስካር የሽልማት ሥነ ሥርዐት በርካታ ጥቁር ፊልም ሠሪዎች ጎልተው የወጡበት ነበር። 'ብላክ ፓንተር' በምርጥ ኦሪጅናል ስኮር፣ በፕሮዳክሽን ዲዛይንና በኮስቲውም ዲዛይን ሦስት ሽልማቶች አግኝቷል።

በተጨማሪም ዛንዚባር የተወለደው የሮክ ኤንድ ሮል ሙዚቀኛ ህይወትና ሥራ የሚዳስሰው ፊልም እንዲሁም፣ ለበርካታ ዓመታት ሽልማት ሳይገኝ የቆየው ስፓይክ ሊ ተሸልሟል።

ሌላው ተሸላሚ የጽህና መጠበቂያ ሞዴስ ላይ የሚያተኩረው ዘጋቢ ፊልም ነው። በሥራው ከተሳተፉት አንዷ ደግሞ ስኔህ ትባላለች።

ስኔህ የወር አበባ ያየችው በ15 አመቷ ነበር። ለመጀመሪያ ጊዜ የወር አበባዋ ሲመጣ ምን እየተፈጠረ እንደሆነ አላወቀችም ነበር።

"በጣም ደንግጬ ነበር። ከባድ በሽታ የያዘኝ መስሎኝ ማልቀስ ጀመርኩ" በማለት ትናገራለች።

"ለእናቴ ለመናገር ስለፈራሁ ለአክስቴ ነበር የነገርኳት። አክስቴ 'አሁን አድገሻል ማለት ነው። አታልቅሺ፤ ተፈጥሯዊ ነው።' በማለት አስረዳቺኝ። ለእናቴ የነገረቻት እሷ ናት"

ስኔህ አሁን 22 አመቷ ነው። በመንደሯ በሚገኝ የንፅህና መጠበቂያ (ሞዴስ) በሚያመርት አነስተኛ ድርጅት ውስጥ ትሠራች። ስለ ወር አበባ ለህብረተሰቡ ታስተምራለች።

የምስሉ መግለጫ,

ስኔህ ስለ ወር አበባ የተዛባ አመለካከት እንዳለ ትናገራለች

'ኢንድ ኦፍ ሴንቴንስ' (የአረፍተ ነገር መጨረሻ) የተባለው ዘጋቢ ፊልም ኦስካር ሲያሸንፍ፤ ስኔህ የኦስካር ዝግጅትን ለመታደም ወደ ሎስ አንጀለስ አቅንታለች።

ዘጋቢ ፊልሙ የተሠራው በሰሜን ሆሊውድ አንድ የተማሪዎች ቡድን ባሰባሰበው ገንዘብ ንፅህና መጠበቂያ (ሞዴስ) የሚሰራ ማሽን እና ኢራናዊ አሜሪካዊ ፊልም ሠሪ ራይካ ዜህታብቺን ወደ ስኔህ መንደር በመላክ ነው።

ፊልሙ የተቀረፀው በካቲክሄታ መንደር ባሉ የእርሻ ቦታዎች፣ ሜዳዎች እና የትምህርት ክፍሎች ነው። እንደ ሌሎቹ የሕንድ አካባቢዎች ሁሉ በካቲክሄራ መንደርም የወር አበባ የመነጋገሪያ ርዕስ አይደለም።

ሴቶች በወር አበባ ወቅት እንደቆሸሹ ስለሚታሰብ ከሀይማኖት ቦታዎች እና ሌሎች ማኅበራው ክንውኖችም ይታገዳሉ።

ስለ ወር አበባ ብዙ የተዛቡ አመለካከቶች ስላሉም ሰኔህ የወር አበባ ከማየቷ በፊት ስለ ወር አበባ ምንነት አለማወቋ አይገርምም።

"የወር አበባ የመነጋገሪያ ነጥብ አልነበረም፤ በሴቶች መካከልም መወያያ ርዕስ አልነበረም" ትላለች።

እንደ አውሮፓውያኑ በ2017 'አክሽን ኢንዲ' ውስጥ የሚሠራ ሱማን የተባለ ጎረቤቷ ንፅህና መጠበቂያ (ሞዴስ) የሚሠራ አነስተኛ ድርጅት ውስጥ ለመሥራት ፈቃደኛ እንደሆነች ጠየቃት።

የኮሌጅ ተመራቂ የሆነችው እና አንድ ቀን ለደልሂ ፖሊስ መሥራትን የምታልመው ሰኔህ ጥያቄውን በደስታ ተቀበለች። በመንደሩም "ሌላ ምንም አይነት የሥራ እድል" አልነበረም።

የምስሉ መግለጫ,

'ፍላይ' የተባለው ንጽህና መጠበቂያ ሞዴስ

"እናቴን ፍቃድ ስጠይቃት 'አባትሽን ጠይቂ አለችኝ'። በቤታችን ሁሉም ከባድ ውሳኔዎች በወንዶች ነው የሚወሰኑት"

ስኔህ ለአባቷ ስለ ሥራው ለመናገር በጣም አፍራ ስለነበረ የህፃናት መፀዳጃ እንደምትሰራ ነበር የነገረችው።

"ሥራውን ከጀመርኩ ሁለት ወር በኋላ ነው እናቴ ለአባቴ የሴቶች መፀዳጃ (ሞዴስ) እንደምሠራ የነገረችው" ትላለች ሰኔህ። እድለኛ ሆና አባቷ " ችግር የለውም፤ ሥራ ሥራ ነው" አለ።

ዛሬ አነስተኛ ድርጅታቸው ከ18 እስከ 31 ዓመት የሆኑ ሰባት ሴት ሠራተኞች አሉት። በሳምንት ስድስት ቀን ከጠዋቱ 3 ሰዓት እስከ 11 ሰዓት ይሠራሉ፤ በወር 2500 ሩፒ (35 ዶላር ገደማ) ይከፈላቸዋል።

በቀን 600 የሴቶች ንፅህና መጠበቂያ (ሞዴስ) ያመርታሉ። ንፅህና መጠበቂው 'ፍላይ' (መብረር) ይባላል።

ድርጅታቸው በመንደሩ ውስጥ ስለ ወር አበባ ያለውን የተሳሳተ አስተሳሰብ እየቀየረ ነው።

የስኔህ አባት ራጃንድራ ሲንግ ታንዋር በልጁ በጣም እንደኮራ ይናገራል። "ሥራዋ ህብረተሰቡን በተለይ ደግሞ ሴቶችን ከጠቀመ እኔ በጣም ደስተኛ ነኝ"

የምስሉ መግለጫ,

'አክሽን ኢንዲያ' የተባለው ተቋም በጤና ዙሪያ ይሠራል

ለሰኔህ እና የሥራ ባልደረቦቿ ለኦስካር እጩ መሆን በጣም ትልቅ ስኬት ነው። በኔትፍሊክስ ላይ የሚገኘው ፊልም እጩ የነበረው በምርጥ አጭር ዘጋቢ ፊልም ምድብ ነው።

"ከካቲክሄራ ውጪ ማንም ሰው ሄዶ አያውቅም፤ እኔ የመጀመሪያዋ ነኝ" ትላለች ስኔህ። "አሁን በመንደሬ ውስጥ ታዋቂ እና የምከበር ሰው ሆኛለው። ሰዎች እንደሚኮሩብኝ ይነግሩኛል"

"አሜሪካ እሄዳለው ብዬ አስቤ አላቅም። አሁን እራሱ የሆነውን ለመቀበል ጊዜ ያስፈልገኛል። ለኔ እጩ መሆን ራሱ ሽልማት ነው። የሆነው ነገር ህልም ነው፤ የማልመው ደግሞ አይኖቼን ገልጬ ነው" ትላለች።