"በራሷ ገቢ የምትተማመንና መቆም የምትችል ሀገር ማየት እሻለሁ"ወ/ሮ አዳነች አቤቤ

ወ/ሮ አዳነች አቤቤ የገቢዎች ሚንስትር
አጭር የምስል መግለጫ ወ/ሮ አዳነች አቤቤ የገቢዎች ሚንስትር

ጠቅላይ ሚንስትር ዐብይ አህመድ በጥቅምት ወር ከሾሟቸው ሀያ ሚኒስትሮች አስሩ ሴቶች ነበሩ። ይህም ሴቶች በከፍተኛ የፖለቲካ አመራር እንዲሳተፉ መሰረት የሚጥል ስለመሆኑ በርካቶች ይስማማሉ።

ቀደም ሲል በወንዶች ይመሩ የነበሩ እንደ መከላከያ ሚኒስቴር ያሉ ተቋማት በሴቶች እንዲመሩ የተደረገበት የካቢኔ ሹመት በብዙዎች ትልቅ እርምጃ ተብሎ ተሞካሽቷል።

ከሴት ካቢኔዎች መካከል የገቢዎች ሚንስትሯ ወ/ሮ አዳነች አቤቤ ይገኙበታል። ከሚንስትሯ ጋር አጭር ቆይታ አድረገናል።

"የመከላከያ ሚኒስቴርን በተሻለ መልኩ መምራት ይቻላል" ኢንጂነር አይሻ መሀመድ

ቢቢሲ፡ እስኪ ስለአስተዳደግዎ ይንገሩን?

ወ/ሮ አዳነች፡ተወልጄ ያደኩት አርሲ ዞን ውስጥ አሳኮ ወረዳ፣ ጨፌ ተብሎ በሚጠራ ቀበሌ ውስጥ ነው። የመጀመሪያ ደረጃ ትምህርቴን የተከታተልኩት ከአምስት ኪሎ ሜትር በላይ በእግሬ እየተመላለስኩ ነበር። ሁለተኛ ደረጃ ትምህርቴን ደግሞ የተከታተልኩት በመተሃራ ነው። የ12ኛ ክፍል ውጤቴ እንደጠበቅኩት አልነበረም። ከዚያ ወደ መምህራን ማሰልጠኛ ተቋም ገባሁ። ከአንድ ዓመት በኋላም የአንደኛ ደረጃ ትምህርት ቤት መምህርት ሆንኩ። መምህርት ሳለሁ የትምህርት ደረጃዬን ወደ ዲፕሎማ ከዚያም ወደ መጀመሪያ ዲግሪ ማሳደግ ችያለሁ።

የሴቶች መብት ታጋይዋ ወይዘሮ መዓዛ አሸናፊ ማን ናቸው?

ቢቢሲ፡ እንዴትወደልጣንመጡ?

ወ/ሮ አዳነች፡ ወደ ስልጣን የመጣሁት የሦስተኛ ክፍል ተማሪ ሳለሁ ነበር። በዛ እድሜዬ የክፍል አለቃ ነበርኩ። መምህርት ስሆን ደግሞ ''ዩኒት ሊደር'' ነበርኩ። ከዚያም የትምህርት ቤቱ ርዕሰ መምህርት ሆንኩ። የመጀመሪያ ዲግሪዬን በሕግ ከተመረቅኩ በኋላ በኦሮሚያ ፍትህ ቢሮ አቃቤ ሕግ በመሆን ማገልገል ጀመርኩ። እዚህ በነበርኩበት ወቅትም አንድ ቢሮ እመራ ነበረ።

1997 ዓ. ም. ላይ የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት አባል በመሆን ተመረጥኩ። የምክር ቤት አባል ሳለሁም በተለያዩ የኃላፊነት ቦታዎች ላይ አገለግል ነበር። ከዚያ በኋላ ለስድስት ዓመታት የኦሮሚያ ልማት ማህበርን ስመራ ቆይቻለሁ። ለአንድ ዓመት ተኩል የአዳማ ከተማ ከንቲባ ሆኜ ከሠራሁ በኋላ ነው እንግዲህ የገቢዎች ሚንስትር ሆኜ የተሾምኩት።

“አንቺሆዬ”፡ የኢትዮጵያዊያት ታሪክን መናገር

ቢቢሲ፡ ሴትነት እና ኃላፊነት እንዴት ይታያሉ?

ወ/ሮ አዳነች፡ ለማንም ቢሆን ነገሮች ቀላል አይሆኑም። ሴቶችን የሚገጥሟቸው አይነት ችግሮች እኔም ሲገጥሙኝ ቆይተዋል። ብዙ ውጣ ውረዶችን ማለፍ የተለመደ ነው። ከውጤትም፣ ከፈተናም ብዙ እንማራለን። ለምሳሌ በአንድ ነገር ውጤታማ ሳንሆን ስንቀር፤ ከዚህ ምን መማር እችላለሁ? ድክመቴ ምን ነበር? በማለት ራሳችንን መጠየቅ ይኖርብናል።

በአስተዳደር ብቃት ላይ ልዩነት የሚፈጥረው ጾታ ሳይሆን ችሎታ እና ዝግጁነት ነው። እንደውም ለኃላፊነቶቻቸው ትኩረት የሚሰጡት እና ለሕዝቡ ቀረቤታ ያላቸው ሴቶች ናቸው። በታችኛው የመንግሥት እርከን ላይ ብንመለከት በአመራርነት ላይ የሚገኙ ሴቶች በተሻለ መልኩ ለሕዝቡ ቅርብ ናቸው። ባለጉዳዮችን ቀርበው ያናግራሉ፣ የባለጉዳዮችን ጉዳይ በትኩረት ያዳምጣሉ፤ እንዴት ሆነ ብለውም ይጠይቃሉ።

ኢንጅነር አይሻ መሃመድ የሃገር መከላከያ ሚኒስትር ሆነው ተሾሙ

አጭር የምስል መግለጫ ወ/ሮ አዳነች አቤቤ የገቢዎች ሚንስትር

ቢቢሲ፡ ከአንደኛ ደረጃ ትምህርት ቤት መምህነት ተነስተው የሚንስትር መስሪያ ቤትን እየመሩ ይገኛሉ። የሴቶችን አቅም ለመገንባት ወይም ተሳትፎ ለመጨመር እና ወደስልጣን ለማምጣት የሚያደርጉት ጥረት አለ?

ወ/ሮ አዳች፡ ሴቶች እድሉን ተነፍገው እንጂ መሪ የመሆነ ተፈጥሯዊ አቅም ያንሳቸዋል የሚል እምነት የለኝም። አጉል ባህል እና የህብረተሰቡ አመለካከት የሴቶችን ተሳትፎ ዝቅ አድርጎታል። ሌት ተቀን እየተጉ የሚሠሩ ሴቶች እንኳ የኢኮኖሚ ጥገኛ ሆነው ይኖራሉ። ይህ የሚቆጨን ከሆነ ባገኘነው እድል ምን ሠራን ብለን ራሳችንን መጠየቅ ይኖርብናል።

የኦሮሚያ ፍትህ ቢሮ እያለሁ አዲስ የሚረቀቁ ሕጎች ምን ያህል የሴቶችን ጥቅም ያስከብራሉ? ምን ያህል ተጠቃሚ ያደርጋሉ? የሚሉ ጉዳዮች ላይ በአትኩሮት ስሰራ ቆይቻለሁ። የኦሮሚያ ልማት ማኅበር እያለሁም የምንቀርጻቸው ፕሮጀክቶች የሴቶችን ተጠቃሚነት የሚያረጋግጡ እንዲሆኑ ትኩረት እናደርግ ነበር። የአዳማ ከንቲባ ሆኜ ስመደብ በአመራርነት ደረጃ ላይ የነበሩት ሴቶች 18 በመቶ ነበሩ። ከአንድ ዓመት ተኩል ቆይታዬ በኋላ አሃዙ ወደ 32 በመቶ ከፍ ብሏል። ወደዚህ መሥሪያ ቤት ከመጣሁ በኋላ የሴቶችን ተሳትፎ ከፍ አድርጌያለሁ። •''የፍርድ ቤቶች ተዓማኒነት እና ገለልተኛነት ይመለሳል'' ወይዘሮ መዓዛ አሸናፊ

ቢቢሲ፡ አሁን እየመሩት በሚገኙበት የገቢዎች ሚንስትር መሪያ ቤት ውስጥ ምን አይነት ለውጥ ማምጣት ይሻሉ?

ወ/ሮ አዳነች፡ ዋናው ጉዳይ ሚንስትር መሥሪያ ቤቱ የተቋቋመበትን አላማ ማሳካት ነው። ሀገሪቱ የምታመነጨውን ገቢ መሰብሰብ። እዚህ እስካለሁ ድረስ በራሷ ገቢ የምትተማመንና መቆም የምትችል ሀገር ማየት እሻለሁ። ምንም እንኳ ይህ በአንድ ሚንስትር መሥሪያ ቤት የሚሳካ ባይሆንም መሰረታዊ ነገር ማኖር እፈልጋለሁ።

ቢቢሲ፡ እንደ አንድ ከፍተኛ አመራር ስለ ገሪቱ ጉዳይ የሚያሳስብዎ ነገር ምንድነው?

ወ/ሮ አዳነች፡ አሁን ለደረስንበት ደረጃ ብዙ መስዋዕትነት ተከፍሏል። ሕዝቡም ብዙ ለውጥ ማየት ይፈልጋል። ይሁን እንጂ ሕዝቡ ማየት የሚፈልገውን ለውጥ በቅርብ ግዜ ማምጣት ቀላል ላይሆን ይችላል።

የሆስፒታል፣ የመንገድ፣ የትምህር ቤት . . . የነዚህን ሁሉ ጥያቄ በአንድ ግዜ ምላሽ መስጠት አንችልም። ሁሉንም በአንድ ግዜ ማስደሰት አንችልም። ጥያቄዎች ምላሽ ሊያገኙ የሚችሉት በየደረጃው ነው። ይህ ባለበት ሁኔታ ትዕግስት አልበኝነት ይስተዋላል። እያስተዋልን ካልተጓዝን የምንጓጓለትን ለውጥ ሊያደናቅፍና ሊዘገይ ይችላል የሚል ስጋት አለኝ። ብዙ መሮጥ እየቻልን እንቅፋት በሚሆኑብን ጉዳዮች ላይ ጊዜ ማባከን ይስተዋልብናል። የኢትዮጵያ ሕዝብ መከፋፈል ሳይሆን አንድ ሕዝብ ሆነን መጓዝ ይጠበቅብናል።

በዚህ ዘገባ ላይ ተጨማሪ መረጃ