የአማራ ክልል ፖሊስ ኮሚሽን፡ "መንግሥት ትጥቅ ሊያስፈታ ነው የሚባለው ከእውነት የራቀ ነው"

ኮሚሽነር ዘላለም ልጃለም

በማዕከላዊ ጎንደርና በምዕራብ ጎንደር በተፈጠሩ ግጭቶች በሰው ሕይወትና በንብረትና ላይ ጉዳት ደርሷል፣ ዜጎች ተፈናቅለዋል፣ የትራንስፖርትና የንግድ እንቅስቃሴ ተስተጓጉሏል።

የክልሉ መንግሥትም በተለያየ ጊዜ የሚፈጠሩ ግጭቶችን ለማስቆም ጥረት እያደረገ እንደሚገኝ በተለያየ ጊዜ ባወጣው መግለጫ አስታውቋል።

ግጭቱን ለመፍታት የፌደራልና የክልሉ የፀጥታ ኃይል ካለፈው ሳምንት ጀምሮ በአዲስ መልክ የአካባቢውን ሰላምና ደህንንት ለማረጋገጥ የሚያስችል ስምሪት ውስጥ መግባታቸው ተነግሯል።

በስምሪቱ የተለያዩ ለውጦች እየታዩ እንደሆነ የአማራ ፖሊስ ኮሚሽን ኮሚሽነር ዘላለም ልጃለም ዛሬ የካቲት 18 ቀን 2011 ዓ. ም. በሰጡት መግለጫ አስረድተዋል።

"ስምሪቱ ከጀመረ በኋላ አንፃራዊ የሆነ ሰላም በአካባቢው ላይ ተፈጥሯል" የሚሉት ኮሚሽነሩ፤ ከስምሪቱ በኋላ የሰው ሕይወት መጥፋትና ንብረት መውደም ቆሟል ብለዋል።

የትራንስፖርትና የንግድ እንቅስቃሴን የሚያውኩ ሁኔታዎች ላይ መሻሻሎች ታይተው በየትኛውም አካባቢ የትራንስፖርት እንቅስቃሴ ሰላማዊ በሆነ መልኩ እየተካሄደ መሆኑን ጨምረው ተናግረዋል።

ባለፈው ሳምንት አልፎ አልፎ በግለሰብ ደረጃ የተፈፀሙ ወንጀሎች የተከሰቱ ቢሆንም፣ በተለይ ከዚህ ቀደም በቡድንና በተደራጀ መልኩ ሲፈፀሙ የነበሩ ወንጀሎችን መከላከል ተችሏል ብለዋል ኮሚሽነሩ።

ልዩ ስምሪቱ ከጀመረ በኋላ መሰረታዊ የሚባል የፀጥታ መሻሻል ቢታይም ወደነበረበት ሰላም የመመለስ ሥራ እየሰራን ነው ብለዋል።

በዚህ ሂደት ከመቼውም ጊዜ በላይ የፌደራልና የክልል የፀጥታ ኃይል ተቀናጅቶ እየሠራ መሆኑን ኮሚሽነሩ አስታውቀው ህብረተሰቡም የተፈናቀሉ ሰዎችን በመርዳት፣ የሕዝብ ለሕዝብ ግንኙነትን በማጠናከር፣ ወንጀለኞችን አጋልጦ በመስጠት፣ ለፀጥታ ሥራውና ለአካባቢው ደህንነት ሲባል በተከለከሉ አካባቢዎች ትጥቅ ይዞ አለመንቀሳቀስን ተግባራዊ በማድረግ ከፍተኛ አስተዋፅኦ እያደረጉ ይገኛሉ ሲሉ አስረድተዋል።

የታገቱ ሰዎችን በሚመለከት ለተነሳላቸው ጥያቄም "ሙሉ በሙሉ ተለቀዋል፤ ወንጀለኞችንም በቁጥጥር ስር ለማዋል እየተሠራ ነው" ብለዋል።

ኮሚሽነሩ እንደገለፁት፤ ከዚህ ቀደም የታየውን ህፃናትን ወደ ወንጀል ድርጊት መግፋትና የአርሶ አደር የእህል ክምር እንዲቃጠል የማድረግ ሁኔታንም መቆጣጠር ተችሏል።

ከጎንደር መተማና ሁመራ መስመር ሰላማዊ የሆነ የትራንስፖርት አገልግሎት ተጀምሯል። ክልሉ አዲስ ስምሪት ከጀመረ በኋላ ግጭት የፈጠሩ 11 ግለሰቦች በቁጥጥር ስር ውለዋል።

ኮሚሽነሩ ከዚህ ቀደም ወንጀል የፈፀሙ፣ ለሰዎች ሞት ምክንያት የሆኑ፣ ንብረት ያወደሙና ዜጎች እንዲፈናቀሉ ያደረጉ በአግባቡ ተለይተው ሕጋዊ እርምጃ ለመውሰድ እየተሠራ እንደሆነም ገልፀዋል።

"በአማራም ሆነ በቅማንት የሞተው አንድ ሕዝብ ነው፤ እርስ በእርስ የተሳሰረ ሕዝብ ነው። ይህንንም ግጭት ህብረተሰቡ እያወገዘው ነው። በመሆኑም በየትኛውም በኩል ብጥብጥና ሁከት የፈጠሩ ወንጀለኞችን ለማጋለጥ ህብረተሰቡ ትብብሩን አሳይቷል" ሲሉ በሁለቱ ሕዝቦች መካከል ያለውን ትስስር ገልፀዋል።

ሕገ ወጥ የጦር መሳሪያን በሚመለከት ኮሚሽነሩ በመግለጫቸው፤ "ጎንደር ከተማ ውስጥ ማንኛውም ሰው ትጥቅ ይዞ እንዳይንቀሳቀስ ከተከለከለ በኋላ ተኩስ የለም። ህገ ወጥ እንቅስቃሴ የለም። ለዚህም ህብረተሰቡ ተሳትፎ እያደረገ ነው" ብለዋል።

ነገር ግን አሁንም ሥራውን ሊያደናቅፉ የሚችሉ ችግሮች ይስተዋላሉ ያሉት ኮሚሽነሩ፤ መንግሥት የጎንደርን ሕዝብ ትጥቅ ሊያስፈታ ነው የሚል ፕሮፖጋንዳ በፍፁም የማይደረግና የመንግሥት አቋም አይደለም ብለዋል።

በተመሳሳይ በፌደራልና በክልሉ የፀጥታ መዋቅር እንዲሁም በክልል ከፍተኛ የፀጥታ አመራሮች መካከል አለመግባባት እንዳለ የሚገለፁ ሃሳቦችን ተራ አሉቧልታ፣ ከእውነት የራቁና ሆን ተብለው የክልሉን የተደራጀ አቅም ለማዳከም የሚጠነሰስ ሴራ በመሆኑ ህብረተሰቡ ከሀሰተኛ መረጃዎች ራሱን እንዲጠብቅ አሳስበዋል።