በረከት ስምኦን ስለራሱ ይናገራል

የፎቶው ባለመብት, Bereket Simon
በረከት ስምኦን
ኤርትራዊው በረከት ስምኦን ወላጆቹ ያወጡለት ስም በተለያየ ምክንያት በተለያዩ ፀሐፊያን ሲብጠለጠል እንደነበር የተረዳው ዘግይቶ ነው። ሰዎችን እንደገደለ፣ ከኢትዮጵያ አምልጦ ፈረንሳይ፣ ፓሪስ እንደሚኖር ተፅፏል። ይህ ሁሉ ሲሆን ጉዳዩን ከቁብ ቆጥሮ አልተከታተለውም።
በኋላ ላይ ግን የተፃፈው ነገር እሱን ብቻ ሳይሆን ሁለት እህቶቹንም አካተተ። ያኔም በርካቶች ይፈሩት፣ ይደነግጡ ጀመር፤ በዚህ ወቅት ስጋት ገባው።
ከኤርትራዊያን የተወለደው በረከት ስምኦን ያደገው አዲስ አበባ ፖፖላሬ አካባቢ ሲሆን በልጅነቱ ክረምትን ያሳልፍ የነበረው ከቤተሰቦቹ ጋር በመሆን ኤርትራ ውስጥ ነበር።
ኑሮውን በፈረንሳይ ካደረገ 40 ዓመታትን ያስቆጠረው በረከት ስምኦን በስሙ ምክንያት ብዙ ችግሮች ገጥሞታል።
ከኢትዮጵያ ከመውጣቱ በፊት ስለነበረው ሕይወት ብዙ ያጫወተን በረከት ለዘመቻ (ዕድገት በሕብረት) ወደ ወለጋ ተልኮ ከነበረበት ጥሎ ወደ አዲስ አበባ እንደተመለሰና ኢህአፓን በአዲስ አበባ ውስጥ ወረቀት በመበተን መቀላቀሉን ያስታውሳል።
በረከት በወቅቱ የኢህአፓን የፕሮፓጋንዳ ጽሑፎች ቤት ለቤት ይበትን ነበር። ከዚያም አልፎ በየመንግሥት መሥሪያ ቤቶች 'መንግሥትን ክደዋል' ተብሎ ስም ዝርዝራቸው የተያዘ ግለሰቦችን ሰነድ ሰርቆ ያጠፋ እንደነበርም ያስታውሳል።
አንዳንዴ የጦር መሣሪያዎችን እንዲደብቅ ወይም እንዲያቀብል ይጠየቅና ይከውን እንደነበርም አልሸሸገም። በረከት እንደሚያስታውሰው በዙሪያው ከነበሩት ሰዎች መካከል የጠፉ፣ ሀገር ጥለው የወጡ፣ የታሰሩና የተገደሉ አሉ።
በረከት ከዕድገት በሕብረት ዘመቻ በመመለሱ አቋርጦት የነበረውን ትምህርቱን የመቀጠል ብርቱ ፍላጎት ነበረው። በዚህ ወቅት ነው ስሙ 'ኮብልሏል' ከሚል ዝርዝር ውስጥ መካተቱን ያወቀው።
ይኼኔ ይላል በረከት "ወረቀት የመስረቅ ልምድ ስለነበረኝ አራት ኪሎ ከሚገኝ መሥሪያ ቤት ገብቼ ስሜ የነበረበትን ደብዳቤ፤ አጣጥፌ በኪሴ ደብቄ ወጣሁ።"
ይህን በማድረጉ ከመንግሥት ትኩረት ለጊዜውም ቢሆን መሰወር ስለቻለ ወደ ሊሴ ገብረማሪያም ተመልሶ ትምህርቱን አጠናቀቀ። ከሊሴ ገብረማሪያም ከተመረቀ በኋላም ነፃ የትምህርት ዕድል አግኝቶ ወደ ፈረንሳይ ማቅናቱን ይናገራል።
"ወረቀቱን ከሠረቅኩበት መሥሪያ ቤት ሄጄ ከሃገር ለመውጣት እንድችል የሚያሰፈልገኝን ወረቀት እንዲፈርሙልኝ ጠየኳቸው... እነሱም ፈረሙልኝና ወጣሁ።"
የፎቶው ባለመብት, Bereket Simon
የበረከት ስምኦን መታወቂያ
በረከት ስምኦን ማን ነው?
በረከት ስምኦንን፤ የቀድሞውን የመንግሥት ኮሙኑኬሽን ጉዳዮች ሚኒስትርና በአሁኑ ወቅት በባህር ዳር በማረሚያ ቤት የሚገኙት ሞክሼው ጋር ይተዋወቁ እንደሆን ስንጠይቀው "ማን እንደሆነ አላውቅም። አግኝቼውም አላውቅም። እኔ ግን በረከት ስምኦን እባላለሁ" ሲል መልሶልናል።
ከዚህ ቀደም የኢትዮጵያ ማስታወቂያ ሚኒስትር የነበረው በረከት ስምኦን ስሙን የወረሰው ከእኔ እንደሆነ የሚገልጽ ጽሑፍ ወጥቶ እንደነበር ሰምቻለሁ የሚለው በረከት፣ በዚህም የተነሳ ሰዎች ከእሱ ጋር እንደሚያመሳስሉት ይናገራል።
"መጀመሪያ ምንም አልሰማሁም ነበር። በረከት ስምኦን ትክክለኛ ስሙም ይመስለኝ ነበር። ለመጀመሪያ ጊዜ የሰማሁት እህቶቼ አሥመራ እያሉ 'ወንድማችሁ ከኢትዮጵያ መንግሥት ጋር እየሠራ ነው' ብለዋቸው ትኩረቴ ተሳበ። ምን እንደሆነ ለማየት ብቻ አሥመራ ሄድኩኝ። ሲያዩኝ ሌላ ሰው እንደሆንኩኝ ሲገነዘቡ ምንም አላሉኝም።"
ከዚያ ቀጥሎ ግን በበይነ መረብ ብዙ ነገሮች ማንበብ እንደጀመረ ይናገራል። ከስም መመሳሰል ውጪ እርሱን ከበረከት ስምኦን ጋር ማገናኘታቸው ግራ እንደሚያጋባው ገልጾ "ታሪኩ ከእኔ ጋር ምንም የሚያገናኘው ነገር የለም" ይላል።
"ጸሐፊው እንዴት አድርጎ እኔ ላይ እንዳተኮረ ሊገባኝ አልቻለም" የሚለው አቶ በረከት "በተለይ ሁለቱንም እህቶቼን ጠቅሶ የጻፈ በመሆኑ ነው ቀጥታ ከእኔ ጋር ሊያያዝ የቻለው። እኔ ግን [የኮሙኑኬሽን ሚኒስትሩ] አልነበርኩም።"
"በአንድ ወቅት ቀልድም መስሎኝ ነበር" የሚለው በረከት ነገሩ እየተደጋገመ ሲመጣ ግን እያስጨነቀው መጣ። "አብረውኝ የተማሩት ጓደኞቼን በስልክ ሳገኛቸው... ያነበቧቸውን ነገሮች በሙሉ እኔ እንደሆንኩ አርገው ነበር ያመኑት" በማለት ያስረዳል።
የፎቶው ባለመብት, Bereket Simon
የአቶ በረከት ስምኦን የልደት ምሥክር ወረቀት
ኤርትራዊው በረከትና የተሳከረው ማንነት
በረከት ስምኦን ኢትዮጵያ በየተወሰነ ጊዜ ይመላለሳል። በአንድ ወቅት ከባለቤቱ ጋር ላሊበላ ባለ አንድ ሆቴል ቆይታ ለማድረግ ፈልገው ለእንግዳ ተቀባዩ ማንነታቸውን የሚገልፅ መረጃ እየሰጡ ሳለ የእሱን ስም ሲመዘግቡ መደናገጣቸው በፊታቸው ይነበብ ነበር ይላል።
በረከት ስምኦን እሱን እና እህቶቹን የጠቀሰው ጽሑፍ ስለማንነቱ የተወሰኑ መረጃዎችን በማስፈሩ ብዙ ሰዎች እንዲፈሩት፣ እንዲጠራጠሩት እንዳደረገ ይናገራል።
"ሰዎችን ገድሏል፣ ከኢትዮጵያ አምልጦ ፓሪስ ነው ያለው ተብሎ ነበር የተጻፈው። ጸሐፊው ከየት አምጥቶ ይህን ሁሉ እንደጻፈ አልገባኝም። እኔ የወጣሁት በሕጋዊ መንገድ ነው። ደግሞም ፓሪስ ኖሬ አላውቅም። ቤተሰባችን ውስጥ 10 ነን፤ ነገር ግን ሁለቱን እህቶቼን ብቻ መርጦ ለምን እንደጠቀሰ ግራ ገብቶኝ ነበር" ካለ በኋላ "እኔ እንደሚመስለኝ ሁለቱ እህቶቼ ታጋይ እንደነበሩ፣ በረከት ስምኦን የሚባልም [ወንድም] እንዳላቸውና... ፈረንሳይ መሆኔን ካወቀ በኋላ ነገሮቹን አገጣጥሞ ታሪክ የሠራ ይመስለኛል።"
አሥመራ የነበሩት እህቶቹ በዚህ ጽሑፍ ምክንያት 'ወንድማችሁ ከሃዲ ነው'፣ 'ወንድማችሁ ከኢትዮጵያ መንግሥት ጋር እየሠራ ነው' እና ሌላም ወቀሳ ይደርስባቸው እንደነበር ያስረዳል።
በረከት ምን ይሠራል?
"ምናልባት ሌላ በረከት ስምኦን ሊኖር ይችላል። እኔ ግን 'በረከት እያሱ' እንጂ ሌላ በረከት ስምኦን የሚባል ገጥሞኝ አያውቅም" የሚለው በረከት፣ በስሙ የተነሳ ከበርካታ ሰዎች ጋር የነበረው ግንኙነት እንደተበላሸ ይመሰክራል።
ይህንንም ሲያስረዳ "አንድ ጓደኛዬ ሰው ሞቶበት ላጽናናው ደውዬለት ጭራሽ እንደማያውቀኝ ሆነብኝ። እኔም ግራ ገባኝ። ከዚያ ሲያስረዳኝ ትክክለኛው በረከት ስምኦን መስዬው እንደሆነ አስረዳኝ። ከብዙ ጓደኞቼ ጋር ግን አቆራርጦኛል።"
ሰው ገድሏል በመባሉ የሸሹትን ሰዎች ሲያስብ "ያናድዳል" ይላል። አሁን ነገሩ እየከበደ ሊመጣ ይችላል እያለ የሚሰጋው በረከት "ክስ ልመሠርት ሁሉ አስባለሁ" ይላል።
በረከት በአሁኑ ወቅት በፈረንሳይ ናንት በምትባል ከተማ ውስጥ ኑሮውን ያደረገ ሲሆን የሦስት ልጆች አባትም ነው።
የእንስሳት ሐኪም የሆነውና የራሱን ክሊኒክ ከፍቶ እየሰራ የሚገኘው የ60 ዓመቱ በረከት "ጡረታ ልወጣ ትንሽ ነው የቀረኝ" በማለት ልጆቹ ለዩኒቨርሲቲ እንደደረሱለት አጫውቶናል።