አር ኬሊ በገንዘብ ዋስ ከእስር ተለቀቀ

አር ኬሊ በቀረቡበትን ክሶች ባጠቃላይ ጥፋተኛ አይደለሁም ብሏል

የፎቶው ባለመብት, EPA

የምስሉ መግለጫ,

አር ኬሊ በቀረቡበትን ክሶች ባጠቃላይ ጥፋተኛ አይደለሁም ብሏል

በወሲባዊ ጥቃት ክስ ታስሮ የነበረው የአር ኤንድ ቢ ሙዚቀኛው አር ኬሌ ከቺካጎ እስር ቤት በ100 ሺህ ዶላር የገንዘብ ዋስ ተለቀቀ። ባለፈው ሳምንት የቀረቡበትን አስር የወሲባዊ ጥቃት ክሶች ባጠቃላይ "ጥፋተኛ አይደለሁም" ብሎ ነበር።

የ52 ዓመቱ ሙዚቀኛ ባለፈው ሳምንት ወደ እስር ቤት ከጠበቃው ጋር ሲሄድ ለመገናኛ ብዙሀን የተናገረው ነገር አልነበረም። ለፖሊስ እጁን ከሰጠ በኋላ የሳምንቱን ማገባደጃ ቀናት በእስር ቤት ውስጥ አሳልፏል።

አር ኬሊ ፍርድ ቤት የቀረበው 'ሰርቫይቪንግ አር ኬሊ' የተሰኘው ተከታታይ ዘጋቢ ፊልም ለእይታ ከበቃ ከሳምንታት በኋላ ነበር። ዘጋቢ ፊልሙ የአር ኬሊን የቀድሞ ሚስት ጨምሮ በአር ኬሊ ወሲባዊ ጥቃት የደረባቸው ሴቶች ሰቆቃቸውን ይፋ ያደረጉበት ነበር።

አር ኬሊ የተከሰሰው እንደ አውሮፓውያኑ ከ1998 ጀምሮ አድርሷል በተባለው ወሲባዊ ጥቃት ነው። ጥቃት ካደረሰባቸው ሴቶች አንዷን ያገኛት 16ኛ ዓመቷን በአንድ ሬስቶራንት ውስጥ ስታከብር ነበር። ሌላኛዋ የ16 ዓመት ታዳጊ ደግሞ ፊርማውን ስትጠይቀው ነበር ያገኛት።

ጥቃት አድርሶባቸዋል ከተባሉት ሴቶች ሦስቱ ጥቃቱን ሲያደርስባቸው ለአቅመ ሄዋን አልደረሱም ነበር ተብሏል።

ድምጻዊው ለበርካታ አስርት ዓመታት የወሲባዊ ትንኮሳ ክሶች ይቀርቡበት የነበረ ቢሆንም በመደበኛ ሁኔታ ሕግ ፊት ቀርቦ አያውቅም። እሱም ክሶቹን ውድቅ ሲያደርግ ቆይቷል።

የ'ኮክ ካውንቲ ሼሪፍ' ቃል አቀባይ ሶፊያ አንሳሪ እንደተናገሩት፤ አር ኬሊ ትላንት የካቲት 18 ቀን 2011 ዓ. ም. ምሽት ላይ 100 ሺህ ዶላር ገንዘብ ዋስ ሰጥቶ ከእስር ተለቋል። ይህም በዳኛ እንዲያሲዝ ከተወሰነበት አንድ ሚሊየን ዶላር አስር በመቶው ነው።

ፍርድ ቤቱ አር ኬሊ ከአስራ ስምንት ዓመት በታች ከሆነ ሰው ጋር እንዳይገናኝና ፖስፖርቱን እንዲያስረክብ አዟል። አር ኬሊ የፊታችን መጋቢት ዳግመኛ ፍርድ ቤት ይቀርባል።