የናይጄሪያን ምርጫ ፕሬዝዳንት ቡሀሪ እየመሩ ነው

ናይጄሪያውያን የምርጫውን ውጤት በጉጉት እየተጠባበቁ ነው

የፎቶው ባለመብት, Reuters

የምስሉ መግለጫ,

ናይጄሪያውያን የምርጫውን ውጤት በጉጉት እየተጠባበቁ ነው

በናይጄሪያ ሀገራዊ ምርጫ እስካሁን ቆጠራ በተጠናቀቀባቸዉ የምርጫ ክልሎች ፕሬዝዳንት ሙሀመዱ ቡሃሪ ሰባቱን አሸንፈዋል።

ተፎካካሪያቸዉ አቲኩ አቡበከር ደግሞ ዋና ከተማዋ አቡጃን ጨምሮ ሌሎች ሁለት ግዛቶችን በበላይነት አሸንፈዋል።

በተካሄደዉ አጠቃላይ ሀገራዊ ምርጫ 36 የምርጫ ክልሎች ወይም ግዛቶች ይገኛሉ። የሌሎች የምርጫ ክልሎች ዉጤት ባይጠናቀቅም የአቡበከር ፓርቲ ፒዲፒ ከወዲሁ የድምጽ ቆጠራ ሂደቱ ትክክል አለመሆኑን እየገለጸ ነዉ።

ተጨባጭ መረጃ ባይሰጥም "መንግሥትና የምርጫ ኤጀንሲዉ ምርጫዉን ለማጭበርበር እየሰሩ ነዉ" ብለዋል።

የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት፣ አሜሪካ እና የአፍሪካ ህብረት በምርጫው መዘግየትና በምርጫ ቁሳቁሶች ችግር ዙሪያ ያላቸዉን ቅሬታ ገልጸዋል። ገለልተኛ ታዛቢዎች ግን እስካሁን ያሉት ነገር የለም።

ሁለቱ ተፎካካሪዎች አንዱ ሌላዉን ምርጫዉን ለማጭበርበር ከገለልተኛዉ የምርጫ ኮሚሽን ጋር እየሰራ ነው በማለት እየተካሰሱ ነው።

ምርጫዉ በአብዛኛዉ አካባቢ በሰላማዊ ሁኔታ መጠናቀቁ ታውቋል። ነገር ግን በሰሜን ናይጀሪያ ከቦኮ ሃራም በተሰነዘረ ጥቃት የምርጫ ኮሮጆዎችን ለመንጠቅ ሙከራዎች እንደነበሩ ተገልጿል።

በምርጫዉ 73 እጩዎች ቢቀርቡም በዋናነት ግን ቡሃሪና አቡበከር ተቆጣጥረውታል። ሁለቱም ተፎካካሪዎች በሰባዎቹ የእድሜ ክልል የሚገኙ ናቸው። ግማሽ የሚሆኑት ወይም ደግሞ 84 ሚሊዮን የሚሆኑት መራጮቻቸዉ ደግሞ ከ35 ዓመት በታች ናቸዉ።

ፕሬዝዳንት ቡሃሪ ቃል የገባሁትን ለመፈጸም ጊዜ ያስፈልገኛል በማለት መራጮቻቸውን ተማጽነዋል። በአንጻሩ ደግሞ አቡበከር ፕሬዝዳንት ቡሃሪ ሊሰሩበት የሚገባቸዉን ጊዜ አቃጥለውታል የናይጀሪያን ችግር አስተካክላለሁ ምረጡኝ እያሉ ነዉ።

ማንም ይመረጥ ማን ግን የአፍሪካ ባለግዙፍ ምጣኔ ሃብት ናይጀሪያ የሚገጥሟትን ዘርፈ ብዙ ችግሮች በተለይም የኃይል እጥርት፣ ሙስና፣ የሰላምና ጸጥታ ስጋት እና የምጣኔ ሃብት ማሽቆልቆልን የሚታደጋግ መሪ ትሻለች።