ኢህአዴግ ከግንባር ወደ ውህድ ፓርቲ ያመራል?

ኢህአዴግ Image copyright EPRDF

በቅርቡ ጠቅላይ ሚንስትር ዐብይ አህመድ ከሐረሪ፣ ቤኒሻንጉል ጉሙዝ፣ ጋምቤላ፣ አፋርና ሶማሌ ክልል ከተውጣጡ የማኅበረሰብ ተወካዮች ጋር ውይይት ባደረጉበት ወቅት አንድ ጠንካራ አገራዊ ፓርቲ መመሥረት እንደሚያስፈልግ ተናግረዋል።

ሁሉም ኢትዮጵያዊ እኩል የሚነጋገርበት፣ የሚወስንበት፣ ድምፁ የሚሰማበት ሥርዓት ለመፍጠር ጥረት እየተደረገ እንደሚገኝም ጠቅላይ ሚንስትሩ በንግግራቸው ገልፀው ነበር።

ይህንኑ ተከትሎ ሐሳቡ 'የምር ነው ወይስ የጠቅላይ ሚኒስትሩ የአፍ ወለምታ?' ሲሉ በርካቶች መነጋጋሪያ አድርገውት ቆይተዋል። የኢህአዴግ የሕዝብና የውጭ ግንኙነት ዘርፍ ኃላፊ አቶ ሳዳት ነሻን ኢህአዴግ አንድ ፓርቲ እሆናለሁ ማለቱ እውነት መሆኑን ለቢቢሲ አረጋግጠዋል።

"ኢህአዴግ ተዳክሟል ብላችሁ እንዳትሳሳቱ" ጠቅላይ ሚኒስትር ዐብይ አህመድ

"ኢህአዴግ በአራት ብሔራዊ ድርጅቶች ተመሥርቶ እንደ አንድ አገራዊ ፓርቲ እያገለገለ ነው" የሚሉት አቶ ሳዳት ፓርቲዎቹ ተመሳሳይ ፕሮግራም ስላላቸው፣ በልማት፣ በዲሞክራሲና ሰላምን በማስፈን በጋራ ሲሠሩ በመቆየታቸው ወደ አንድ አገራዊ ፓርቲ ላለመሸጋገር የሚያግዳቸው የለም ብለዋል።

አቶ ሳዳት እንደሚሉት ኢህአዴግ አራቱ ፓርቲዎች ብቻ ሳይሆን ሌሎች አጋር ድርጅቶችም ድርጅቱ የበለጠ ተጠናክሮ እንዲቀጥል በማሰብ ይህንኑ የእንዋሃድ ጥያቄ በተደጋጋሚ ሲያቀርቡ ቆይተዋል።

ኢህአዴግ ከግንባር ወደ ፓርቲ መሸጋገር አለበት የሚል ጥያቄ ወደ ጉባዔም መጥቶ በተለይ በ11ኛው ድርጅታዊ ጉባዔ ላይ አፅንኦት ተሰጥቶት አቅጣጫ ተቀምጧል።

ኢህአዴግ ውስጥ ያሉ ፓርቲዎች የሐሳብ ልዩነቶች ስለመኖራቸው ጉምጉምታው ብዙ ነው። ታዲያ በዚህ ጊዜ ውህደቱ እውን ሊሆን ይችላል ወይ? በሚል ለቀረበላቸው ጥያቄ "ኢህአዴግ ውስጥ የተለመደ አሠራርና ልምድ አለ፤ ድርጅቱ የትግል ፓርቲ ነው፤ ስለሆነም ኢህአዴግን የመሠረቱት ፓርቲዎች የተለያዩ ክርክሮችና ሐሳቦችን ያቀርባሉ፤ ነገር ግን ኢህአዴግ ይህን እንደ ልዩነት አያየውም" ብለዋል።

እርሳቸው እንደሚሉት ከልዩነትም ይልቅ በውይይቶቹ ለሃገርና ለዲሞክራሲ ሥርዓት ግምባታ ገዥ የሆነ ምክንያታዊ ሐሳቦች ይመጣሉ ብሎ ያምናል-ኢህአዴግ።

"በረከትና ታደሰ በሙስና መጠርጠራቸው አስደንቆኛል" አቶ ጌታቸው ረዳ

አራቱ ፓርቲዎች በሐሳብ ስለመለያየታቸው ቢወራም ኢህአዴግ እንደዚያ ዓይነት ግምገማ እንደሌለውና ድርጅቱ በሥራ አስፈፃሚም ሆነ በምክር ቤት አጀንዳዎች ላይ ልዩነት ፈጥረው የወጡበት ጊዜ እንደሌለ በመግለጽ አቶ ሳዳት ሐሳባቸውን በምክንያት ያስደግፋሉ።

በመሆኑም ወደ አንድ ድርጅታዊ ፓርቲ ለመምጣት የሚያግድ ነገር አለ ተብሎ እስካሁን አልተገመገመም ብለዋል።

ሁሉም አባል ፓርቲዎች ወደ አንድ ፓርቲ ለመሸጋገር ከዚህ በፊት ባደረጉት ስምምነት መሠረት እየሄደ እንዳለም ገልፀው የድርጅቱ አባላትንም ሕዝብንም በውይይት ለማሳተፍ ተሞክሯል። ይህም የሁሉንም ድርጅቶች ፍላጎትን ያማከለ እንደሆነ ይገልፃሉ።

ሳቡ መቼ ተነሳ? በማን?

እርሳቸው እንደሚሉት ሐሳቡ በአንድ ጀምበር የተጠነሰሰ ሳይሆን ለረዥም ጊዜ በድርጀቱ ሲብላላ ቆይቷል። የዘጠነኛውና የአስረኛው ጉባኤን ጨምሮ በተደጋጋሚ በተለያዩ መድረኮች ላይ ሲነሳ የቆየ ሐሳብም ነው።

ነገር ግን ከግንባር ወደ ፓርቲ መሻገር ያስፈልጋል በሚል አፅንኦት ተሰጥቶ የተነሳው በ11ኛው መደበኛ ጉባኤ ላይ ነው።

ታዲያ እስካሁን ለምን ዘገየ ተብለው የተጠየቁት አቶ ሳዳት ጥያቄውን በሳይንሳዊ መንገድ በጥናት ለመመለስ ታስቦ እንደሆነ ተናግረዋል። ይኸው ጥናት በዚህ ዓመት መጨረሻ ፍጸሜውን አግኝቶ ለውይይት እንደሚቀርብም ይጠበቃል።

"ሁሉም የፓርቲ አባላት ሐሳቡን አንስተዋል፤ አሁን ባለው ሁኔታ ግን አራቱም ድርጅቶች ብቻ ሳይሆኑ ሌሎች አጋር ድርጅቶችም እኛም መካተት አለብን የሚል ጥያቄን ሲያርቡ ቆይተዋል" ብለዋል ኃላፊው።

"የሽግግር መንግሥት ተግባራዊ መደረግ አለበት"

ይህ የውህደት ጉዳይ በዚህ ወቅት ለመነሳቱ ምን ገፊ ምክንያቶች ይኖሩ ይሆን? አቶ ሳዳት ለጉዳዩ ወቅታዊ ምክንያት የሚጠቀስ ባይኖርም በርካታ ፓርቲዎች መኖራቸው አስፈላጊ እንዳልሆነና ሰብሰብ ማለት እንደሚያሻ አስምረውበታል። ይህ ወደ አንድ ፓርቲ የመሰባሰቡ ነገር በተፎካካሪዎች ብቻ ሳይሆን በኢህአዴግም ያስፈልጋል ብለዋል።

ከዚህም ባሻገር ይላሉ አቶ ሳዳት ኢህአዴግ ጠንካራ ፓርቲ ሆኖ የአገሪቱ መሪ መሆን የሚችል ሰው የማፍራት አቅም ለማዳበር ታልሞ እንደሆነ ውህደቱ ያስፈለገበትን ምክንያት በዝርዝር ያስቀምጣሉ።

ይሁን እንጂ አገሪቱ በለውጥ ጎዳና ላይ ከመሆኗ ጋር ተዛምዶ በተለይም ኢትዮጵያዊነት በድርጅቱ ሊቀመንበር ጎልቶ በሚቀነቀንበት ወቅት የውሕደት ሐሳቡ ወደፊት መምጣቱ ለአንዳንዶች በብሔር አደረጃጀትና በፌዴራሊዝም ላይ ለውጥ የሚያጣ ሆኖ ታይቷቸዋል።

ፓርቲዎቹ በብሔር የተደራጁና ስማቸውም ብሔርን የሚወክሉ በመሆናቸው ኢህአዴግ ይዋሃዳል ሲባል ፓርቲዎቹ የነበራቸውን አጠቃላይ የብሔር ምንነትን ያጣሉ የሚል ስጋት መፍጠሩም አልቀረም።

እርሳቸው ግን "ሁሉም የጋራ አስተዋፅኦ የሚያደርጉበት እንዲሆን የታሰበ እንጂ ኢህአዴግ በፌደራል ሥርዓቱ ላይ የሚፈጥረው ለውጥ የለም፤ ግምባሩን ወደ አንድ ፓርቲ ማምጣት ማለት ወደ አሃዳዊ ሥርዓት ይመጣል ከሚለው ሃሳብ ጋር አይገናንኝም" ሲሉ ሞግተዋል።

የህወሓት ማዕከላዊ ኮሚቴ አባል የሆኑት ዶ/ር ፍሰሐ ሐፍተ ጽዮን በበኩላቸው "ወደ ውህደት ከመኬዱ በፊት ብዙ የቤት ሥራዎች መሠራት ይኖርበታል" ሲሉ አቋማቸውን ይገልፃሉ።

ቢያንስ በዋና ዋና የፓርቲው ምሰሶዎች በሆኑት፤ የህገ መንግሥት፣ የልማት ሁኔታዎች ላይ ተመሳሳይ አሊያም እጅግ ተቀራራቢ አረዳድ መኖር አለበት፤ እነዚህ ሳይሟሉ ወደ ውህደት ለመሄድ የሚደረገው ጥረት ስኬታማ ይሆናል የሚል እምነት እንደሌላቸው ይናገራሉ። ህገ መንግሥታዊ ሥርዓቱን በሚመለከትም በሁሉም ፓርቲዎች ስምምነት እንደሌለ የአደባባይ ምስጢር ነው በማለት ያስረዳሉ።

መጠየቅ ካለብን የምንጠየቀው በጋራ ነው፡ አባይ ፀሐዬ

"የኢህአዴግ አባል ድርጅቶችና አባላት ተቀራራቢ ወይም አንድ ዓይነት አቋም እንደሌላቸው ግልፅ ነው፤ ራሳቸውም በተለያየ ጊዜ የሚናገሩት ይህንኑ ነው" የሚሉት ዶ/ር ፍሰሐ ግምባሩም እንደ ግንባር ተቀራራቢ አቋም ሳይኖረው አንዳንዶቹ የግንባሩ ፓርቲዎች ከፍተኛ የሆነ የጎራ መደበላለቅ እያለ 'እንዋሃድ' ስለመባሉ ያላቸው ሃሳብ አወንታዊ እንዳልሆነ ለቢቢሲ አስታውቀዋል።

በውህደቱ የማይስማማ ፓርቲ ቢኖርስ?

ለመሆኑ አንድ ፓርቲ በውህደቱ ባይስማማስ? ምን ሊፈጠር ይችላል? አቶ ሳዳት ይህን ይላሉ፤

"ፓርቲ ለመሆን ውህደት ለመፍጠር የአባል ድርጅት ፍላጎት ይጠይቃል። መሠረታዊ ፍላጎት አለ ብለን እናስባለን። ጥናቱም ያረጋገጠው እሱን ነው። ይህ ከሌለ ግን ወደ ፓርቲም ሳንሸጋገር ከግንባርም መውጣት የሚፈልግ መውጣት ይችላል።"

ነገር ግን አሁን ባለው ሁኔታ በገዢው ግንባር ውስጥ ያለው የሃሳብ ልዩነት ከውህደቱ በፊት እንዲጠብ ካልተደረገ የኢህአዴግ ዋነኛ አስኳል ሆኖ ለሦስት አስርት ዓመታት ለሚጠጋ ጊዜ የዘለቀው ህወሓት በሚመሰረተው ውህድ ፓርቲ ውስጥ የመዝለቁ ነገር አጠያያቂ እንደሆነ ብዙዎች ይናገራሉ።

ተያያዥ ርዕሶች

በዚህ ዘገባ ላይ ተጨማሪ መረጃ