ጎንደር፡ የአፄ ፋሲለደስ ቤተ መንግሥትን አደጋ ላይ የጣለው ምንድን ነው?

የአፄ ፋሲል ቤተ መንግሥት

ጎንደር በ16ኛው ክፍለ ዘመን በአፄ ፋሲለደስ እንደተቆረቆረች ይነገራል። ይሁን እንጂ ከአፄ ፋሲለደስ ንግሥና 300 ዓመታት ቀድማ በምንጮችና በተራሮች የተከበበች መንደር ነበረች ሲሉ የሚሞግቱም የታሪክ አዋቂዎች አሉ።

ጎንደር ለ200 ዓመታት የኢትዮጵያ መናገሻ ሆና አገልግላለች። ባሏት ተፈጥሯዊና ሰው ሰራሽ ቅርሶች፣ ታሪካዊ ቦታዎች እንዲሁም ኃይማኖታዊና ባህላዊ ትውፊቶች ትታወቃለች።

የበርካታ ቱሪስቶች መዳረሻ ከሆኑ አካባቢዎች መካከል በዓለም የቅርስ መዝገብ የሰፈረው የአፄ ፋሲለደስ ቤተ መንግሥት በግምባር ቀደምትነት ይጠቀሳል። ጎንደርን ከፋሲል ግንብ ነጥሎ ማየት ይከብዳል። ስለ ጎንደር የተዜሙ ሙዚቃዎች የሚነግሩንም ይህንኑ ነው።

ዛሬ ዛሬ ግን የአፄ ፋሲለደስ ቤተ መንግሥት ስም የሚነሳው በአስደናቂነቱ፣ በታሪካዊነቱና የኪነ ህንፃ ጥበቡ ብቻ ሳይሆን አደጋ የተጋረጠበት ቅርስ በመሆኑ ነው። በስፍራው ያገኘናቸው ጎብኚዎችም የፋሲል ግንብ ህልውና እንዳሳሰባቸው ገልፀውልናል።

የጥምቀት በዓል አከባበር በጎንደር

መቆየት ፋሲልን ሲጎበኝ የመጀመሪያው ነው።

"በጣም የሚገርም ጥበብ ነው ያየሁት። ታሪካዊ ቦታ ነው። ታሪካዊ በመሆኑ ደግሞ ለትውልድ የሚተላለፍ መሆን ነበረበት" ይላል።

መቆየት ቤተ መንግሥቱን ተሰነጣጥቆና ተሰባብሮ ሲያየው ስሜቱ እንደተነካ ገልጿል። "ለምን ጥገና አይደረግለትም?" ሲል የሁሉም የሆነውን ጥያቄ ይጠይቃል።

መንግሥትና የሚመለከተው የቅርስ ጥበቃ አካል ምን እየሠራ እንደሆነ ማወቅና መከታተል ያስፈልጋል ሲልም አስተያየቱን ሰጥቷል።

ከአዲስ አበባ ወደ ጎንደር የሄደው ሌላው ጎብኝ ሳሙኤል በለጠም "ቤተ መንግሥቱን ሳየው ድብልቅልቅ ያለ ስሜት ነው የተሰማኝ" ይላል። ጥበብ የተሞላበትን ኪነ ህንፃ ሲያይ በኢትዮጵያዊነቱ ኩራት ተሰምቶታል። በሌላ በኩል ደግሞ ቅርሱ ጥበቃና እንክብካቤ መነፈጉ አሳፍሮታል።

ሳሙኤል ይህን የተደበላለቀ ስሜት ውጦ ዝም አላለም። በጉዳዩ ላይ ከሥራ አስኪያጁ ጋር ተወያይተዋል።

"ለምን ዝም እንዳሉ አልገባኝም፤ ለምን ከተማ ላይ ብቻ ትኩረት ይደረጋል?" ሲል እንዲመለስለት የሚፈልገውን ጥያቄ ይሰነዝራል።

ከዚህ ቀደም ላሊበላን መጎብኘታቸውን የሚናገሩት ምትኩ እንዳለ የአፄ ፋሲለደስን ግንብ ሲጎበኙ የመጀመሪያቸው ነው።

በጉብኝታቸው ብዙ ጠብቀው ነበር። ይሁን እንጂ ያዩት ነገር አስደንግጧቸዋል። "ኢትዮጵያዊነትን እያጣን ነው" ሲሉ በአጭሩ ይገልፁታል። "ጥናት ተደርጎ በባለሙያ መጠገን አለበት፤ ሁሉም ኢትዮጵያዊ የራሱን አስተዋፅኦ ማድረግ አለበት" ይላሉ።

ከኢትዮጵያና ከሌሎች የአፍሪካ ሃገራት ስለተዘረፉ ቅርሶች ምን እናውቃለን?

በጎንደር አስጎብኚዎች ማህበር አስጎብኚ የሆነችው ቁምነገር ቢምረው የፋሲል ግንብ ያን ያህል እየተጎበኘ አይደለም የሚል አቋም አላት። እሷ ዘወትር ስታየው የተለየ ስሜት እንደሚሰማትና እንደምትኮራ ትናገራለች።

"ሳየው እኮራለሁ፤ ማንነቴን አገኘዋለሁ፤ ደስታ ይሰማኛል፤ በማያቸው ነገሮች እገረማለሁ፤ ትልቅ ታሪክ ያላቸው ሕዝቦች እንደነበሩና፤ እኔም የዚያ ታሪክ አባል እንደሆንኩ ይሰማኛል። "

ቢሆንም ግን እንደ ዓለም ቅርስነቱና ታሪካዊነቱ በመንግሥትም ሆነ በዩኔስኮ (የተባበሩት መንግሥታት የትምህርት፣ የሳይንስና የባህል ተቋም) ትኩረት ተሰጥቶት የሚያስፈልገው ጥገናም ሆነ እንክብካቤ እየተደረገለት አይደለም ትላለች።

አደጋምክንያት?

ቁምነገር እንደምትለው፣ በፋሲል ግንብ ቅጥር ግቢ ውስጥ በርካታ የሰርግ ሥነ ሥርዓቶች ይካሄዳሉ። ማህበረሰቡ ስለ ቅርስ በቂ ግንዛቤ ስለሌለው ብዙዎች ፎቶ ለመነሳት ግንቦቹ ላይ ይወጣሉ። ሰርጉን ምክንያት በማድረግም ይጨፍራሉ። ይህ ቅርሱን አደጋ ላይ የጣለው አንድ ምክንያት እንደሆነ ታስረዳለች።

ለቅርሱ ደህንነት ሲባል ማንኛውም የሰርግ እንቅስቃሴ መቆም አለበት ስትል አስተያየቷን ሰጥታለች።

"ቤቶቹ በማንኛውም ሰዓት ሊደረመሱ ይችላሉ"

የሥነ ሕንፃ ባለሙያ የሆኑት አቶ ማሞ ጌታሁን ተማሪ ሳሉ ጀምረው የአፄ ፋሲል ቤተ መንግሥትን (የፋሲል ግንብን) ለማየት ጉጉት እንደነበራቸው ያስታውሳሉ።

ሥራ ሲይዙ ባህልና ቅርሶችን የሚከታተል መሥሪያ ቤት ተመድበው በቀጥታ ወደ ቅርስ ጥገናና እንክብካቤ ሥራ ገቡ።

ከ1980ዎቹ ጀምሮ የፕሮጀክት ጥናቶችን አዘጋጅተዋል። በተጨማሪም ከሌሎች ዓለም አቀፍ ባለሙያዎች ጋር በመሆን በአፄ ፋሲል፣ በእቴጌ ምንትዋብ ቤተ መንግሥት፣ በደብረ ብርሃን ሥላሴ ቤተክርስቲያን፣ በአፄ ፋሲል መዋኛና ሌሎች በርካታ ቅርሶች ላይ ከሙሉ የጥገና ሥራ እስከ መለስተኛ እንክብካቤ ድረስ ሰርተዋል።

አቶ ጌታሁን ቅርሱ የሚገኝበትን ሁኔታ ለማየት ጥናት መሥራት ከጀመሩበት ጊዜ ጀምሮ ፋሲልን በተደጋጋሚ ጎብኝተውታል፤ የወዳጅ ያህል ያውቁታል።

በዚህ ልምዳቸው የከተማ መስፋፋትና ያለ በቂ ጥናት የሚሰሩ ጥገናዎች በቅርሱ ላይ ችግር ሲያስከትሉ ተመልክተዋል። ከመንግሥትና ከሚመለከታቸው አካላት የሚሰጠው ትኩረት ማነስ፣ የበጀት እጥረት፣ የእንክብካቤና ጥገና ጊዜ መዘግየትንም እንደ ምክንያት ይጠቅሳሉ።

የፋሲለደስ ግንብ የአሁን ይዞታ

የሥነ ህንፃ ባለሙያው እንደሚሉት፣ በቅርሱ ጣራያ ላይ ከሚታዩ ችግሮች በተጨማሪ ግድግዳዎች ተሰነጣጥቀዋል፤ በቅርፁ የመንሸራተትና የመዝመም እክሎችም ገጥመውታል። በአእዋፋትና በእፅዋት እንዲሁም በሌላ ንክኪ መብዛት የተነሳ ተሸርሽሯል፤ ካቦቹም ወዳድቀዋል።

የጎንደር ዓለም አቀፍ ቅርስ አስተዳደር አስተዳደሪ አቶ ጌታሁን ሥዩም በበኩላቸው "የፍቅር ቤተ መንግሥት ከተዘጋ ከ10 ዓመት በላይ ሆኖታል፤ የዮሐንስ ቤተ መንግሥትም እንዲሁ ተዘግቶ ነው ያለው፤ የታላቁ እያሱ ቤተ መንግሥትም ከፈረሰ በኋላ ጥገና አልተደረገለትም" ብለዋል።

የዳዊት ቤተ መንግሥትና የአፄ በካፋ ቤተ መንግሥትም እንዲሁ አደጋ ላይ እንደሚገኙ ሌሎቹም በርካታ ስንጥቆች እንዳሉባቸው ገልፀዋል። በአንድና በሁለት ሴንቲ ሜትር ይለካ የነበረው ስንጥቅ አሁን ወደ 5 ሴንቲ ሜትር ሰፍቷል።

በምስጥና በፈንገስ ምክንያት የእንጨት አካሎቻቸው እየተበሉና እየበሰበሱ ይገኛሉ። አስፈላጊው ጥገና ካልተደረገ የመውደቅ ወይም የመደርመስ አደጋ ማጋጠሙ ጥርጥር የለውም።

የመኪና ንዝረትና ግጭትም ቅርሶቹን ይፈታተኗቸዋል።

መፍትሔው ምንድን ነው?

ጎብኚዎች፣ አስጎብኚዎች እንዲሁም ባለሙያዎች ያስቀመጧቸው የመፍትሔ ሀሳቦች ተመሳሳይ ናቸው። ጉዳዩ የሚመለከታቸው የመንግሥት አካላት ቅርሱን የማዳንና የማቆየት ሥራ ሊሠሩ እንደሚገባ ይናገራሉ።

ቅድሚያ የሚሰጠውን መለየት፣ ለቅርሱ ኃላፊነት ወስዶ የሚሠራን ሰው መመደብ፣ መገምገምና ክትክክል ማድረግ ይገባል። በቂ በጀት መመደብም ከመንግሥት ይጠበቃል ይላሉ።

የቅርሶቹ የጉዳት መጠን በጥናት ታውቆ በቅርሱ አካባቢ የከባድ መኪኖችን እንቅስቃሴ መቆጣጠርም ያሰመሩበት ጉዳይ ነው።

ምን እየተራ ነው?

ለቅርሱ ጥበቃ ትኩረት ሰጥተው እንደሚሠሩ የሚናገሩት የጎንደር ዓለም አቀፍ ቅርስ አስተዳደር አስተዳዳሪ አቶ ጌታሁን ሥዩም ናቸው። በከተማ አስተዳደሩ አቅም የሚቻሉ የጥገና ሥራዎች ተከናውነዋል ይላሉ።

ከሁለት ዓመታት በፊት በነበረው ሀገራዊ ተቃውሞ ምክንያት የቱሪስት መቀዛቀዝ የታየ ቢሆንም አሁን ላይ በተሻለ ሁኔታ ጎብኚዎች ይመጣሉ። ይሁን እንጂ የቱሪስቶች የቆይታ ጊዜ አናሳ ነው።

"የግማሽ ቀን ጉዞ የሚያደርጉ ጎብኚዎች በዝተዋል፤ ይህም ከመሰረተ ልማት ጋር የተገናኘ ነው" ይላሉ።

ከኢትዯጵያ የተዘረፉ ቅርሶች በውሰት ሊመለሱ ነው

የቅርስ ጥናትና ጥበቃ ባለስልጣን በየዓመቱ ከ1 ሚሊዮን ብር ያላነሰ በጀት ይመድባል። ከሌሎች ድጋፍ አድራጊዎች ጋር በጋራ በመሆንም ቅርሱን ከአደጋ ለመጠበቅ እየተሠራ እንደሆነ አቶ ጌታሁን ገልፀዋል።

ቤተ መንግሥቱ ብቻ ሳይሆን በውስጡ ያሉት ተንቀሳቃሽ ቅርሶች ምን ያህል ጥበቃ እየተደረገላቸው ነው? ንጽህናቸውስ ይጠበቃል? የሚሉ ጥያቄዎችም ይነሳሉ። አቶ ጌታሁን፣ እነዚህና ሌሎችም በርካታ መዋቅራዊ ችግሮች ካልተፈቱ ቅርሱ "አደጋ ላይ ነው" የሚለው ቃል አይገልፀውም ይላሉ።

የአፄ ፋሲለደስ ቤተመንግ

የአፄ ፋሲል ቤተ መንግሥት በ1979 ዓ. ም. በዓለም ቅርስነት ተመዝግቧል። ቤተ መዛግብት፣ የአፄ ፋሲል መዋኛ፣ ቁስቋም ማርያም ራስ ግምብና ደረስጌ ማርያምን ያቀፈ ነው።

በአፄ ፋሲለደስ ግንብ ውስጥ ያሉት ቤተ መንግሥቶች ከ100 በላይ ክፍሎች አሏቸው። ባለ ሦስትና ባለ አራት ፎቅ ሲሆኑ፣ በአጠቃላይ 7 ሄክታር (70 ሺህ ስኩየር ሜትር) ይሸፍናሉ።

ግንቡ የተሠራው ከ300-400 ዓመታት በላይ በኖረ የድንጋይ ካብ ሲሆን በዋናነት ድንጋይ፣ ኖራና እንጨት ጥቅም ላይ ውለዋል። በሀገር ውስጥ ባለሙያዎች መሠራቱም ይነገርለታል።

በአፄ ፋሲለደስ ግንብ ውስጥ ያሉት ቤተ መንግሥቶችን ልዩ የሚያደርጋቸው እያንዳንዱ ነገሥታት የራሳቸውን አሻራና ታሪክ ለትውልድ ትተው ማለፋቸው ነው። ቤተ መንግሥቶቹ የሚከተሉት ናቸው፦

1. የአፄ ፋሲል ቤተ መንግሥት፡- ይህ ቀደምቱ ነው። ንጉሡ ቤተ መንግሥቱን ለማሳነፅ 10 ዓመታት ፈጅቶባቸዋል።

2. የአፄ ዮሐንስ ቤተ መንግሥት፡- አፄ ፋሲለደስ ለ36 ዓመታት ከነገሱ በኋላ ልጃቸው እሳቸውን ተክተው ወደ ስልጣን መጥተው ከ1667-1682 ዓ. ም. ሲነግሡ የተሠራ ነው።

3. የታላቁ አዲያም ሰገድ እያሱ ቤተመንግስት፦ የነገሡት ከ1682-1706 ዓ. ም. ነበር። ንጉሡ ጥሩ ፈረሰኛ ነበሩና በኮርቻ ቅርፅ የተሠራ ውብ ቤተ መንግሥት እንደተሰራ ታሪክ ያወሳራል።

4. የአፄ ዳዊት ቤተመንግስት፦ ለአምስት ዓመታት (ከ1716-1721 ዓ. ም.) ሲነግሡ ያሳነፁት ህንፃ ነው። ትልቅ የሙዚቃ ግንብ ያለው ሲሆን፣ ግንባር ቀደሙ የኪነ ጥበብ ማሳያ ህንፃ እንደሆነ ይነገራል። ጥቁር አንበሳ የሚባሉት አንበሶች መኖሪያ ይገኝ የነበረውም በዚህ ነበር።

5. የንጉሥ መሲሰገድ በካፋ ቤተ መንግሥት፦ ለዘጠኝ ዓመታት (ከ1721-1730) የነገሡ ሲሆን፣ የሳቸው ፍላጎት የነበረው ሕዝቡን ግብር የሚያበሉበት ትልቅ ሕንፃ መሥራት ነበር። ስለዚህም ከ250 በላይ ሰዎች መያዝ የሚችልና ፈረሶች የሚቆሙበት ቦታ ያለው ትልቅ የግብር አዳራሽ አሳነጹ።

6. የእቴጌ ምንትዋብ ቤተ መንግሥት፦ ከ1730-1755 ዓ. ም. የነገሡ ሲሆን፣ በጣና ገዳማት ላይም አሻራቸውን አሳርፈዋል።

ተያያዥ ርዕሶች

በዚህ ዘገባ ላይ ተጨማሪ መረጃ