አእምሯችን ሲጎዳ ልባችን ይሰበር ይሆን?

የተሰበረ ልብ Image copyright Getty Images

በጣም አሳዛኝ ከሆነ አጋጣሚ በኋላ ልባችን ሊጎዳ ይችላል። ይህን የሚፈጥረው ደግሞ አእምሯችን እንደሆነ የዘርፉ ተመራማሪዎች ይናገራሉ።

የስዊዘርላንድ ተመራማሪዎች 'የተሰበረ ልብ ምልክቶች' (ብሮክን ኸርት ሲንድረም) የተባለው ያልተለመደ የልብ በሽታ ያለባቸውን ሰዎች ሲያጠኑ ቆይተዋል።

ይህ የልብ መድከም ድንገተኛ ሲሆን ብዙ ጊዜ ሰዎች በጥልቅ ሀዘን ሲወድቁና የሚያስጨንቅ ጊዜ ላይ ሲሆኑ ይከሰታል።

በሰው ክፋይ ሕይወት መዝራት - የኩላሊት ንቅለ ተከላ

በኢትዮጵያ ለካንሰር ተጋላጮች እነማን ናቸው?

ምንም እንኳን ጉዳዩ በትንሹ የተጠና ቢሆንም የአውሮፓው የልብ መፅሄት ለአእምሮ ለጭንቀት መልስ የሚሰጥበት መንገድ ጋር እንደሚገናኝ ይጠቁማል።

ትንፋሽ ማጣት እና ህመም

በሽታው ያለባቸውን ሰዎች ልብ በማመላከት በሌላ ስሙ 'ታኮትሱቦ ሲንድረም' ተብሎ የተሰየመው ይህ የልብ በሽታ በድንጋጤም ሊከሰት ይችላል።

በደም ትቦ መደፈን ምክንያት ከሚመጣው የልብ ድካም የተለየ ቢሆንም እንደ ትንፋሽ መቋረጥ እና የደረት ህምም አይነት ተመሳሳይ ምልክቶችን ያሳያል።

ብዙ ጊዜ አሳዛኝ ክስተቶች የበሽታው መንስኤ ሲሆኑ እንደ ሰርግ እና አዲስ ሥራ ማግኘትን የመሳሰሉ የደስታ ሁኔታዎችም የበሽታው መነሻ ሊሆኑ ይችላሉ።

ህመሙ ጊዜያዊ ሆኖ የልብ ጡንቻ ከቀናት፣ ከሳምንታት ወይም ከወራት በኋላ ወደ ጤነኛ ሁኔታው ሊመለስ ይችላል። ለአንዳዶች ግን ህመሙ ገዳይ የሚሆንበት አጋጣሚ አለ።

'ብሮክን ኸርት ሲንድረም' እንግሊዝ ውስጥ በዓመት 2500 ሰዎችን ያጠቃል ተብሎ ይታሰባል።

ትክክለኛ መንስኤው ባይታወቅም ተመራማሪዎች ከልክ ያለፈ እንደ 'አድሬናሊን' የመሳሰሉ የጭንቀት ሆርሞኖች በአካላችን ውስጥ መመረት ምክንያቱ ነው ይላሉ።

Image copyright Getty Images

ምስጢራዊነት

ዶ/ር ጀሌና ግሃደሪ እና አጋሮቹ በዙሪክ ዩኒቨርሲቲ ሆስፒታል በ 'ብሮክን ኸርት ሲንድሮም' የተጠቁ 15 ህሙማንን አእምሮ አጥንተዋል።

የህሙማኑ የአእምሮ ምስሎች ከ 39 ጤነኛ ሰዋች ጋር ሲነፃፀሩ ጉልህ ልዩነት አሳይተዋል።

"ወንዶች በጡት ካንሠር እንደሚያዙ አላውቅም ነበር"

ልብ የረሳው አውሮፕላን

በሽታው ባለባቸው ሰዎች ላይ፤ ንቁ ሆኖ ስሜቶችን በሚቆጣጠረው የአእምሮ ክፍል እና ምንም ሳያስብ እንደ ልብ ምት ያሉ አካላዊ እንቅስቃሴዎችን በሚቆጣጠረው ክፍል መካከል አነስተኛ ተግባብቶ የመስራት ችግር ይስተዋላል።

እነዚህ ሁለት የአእምሮ ክፍሎች አካላችን ለጭንቀት ምላሽ የሚሰጥበትን መንገድ ይቆጣጠራሉ ተብሎ ይታመናል።

"ስሜቶች የሚብሰለሰሉት አእምሮ ውስጥ ነው። ስለዚህ በሽታው አእምሮ ውስጥ ጀምሮ ወደ ልብ ይወርዳል" በማለት ዶ/ር ግሃድሪ ያስረዳሉ።

በሽታው እንዴት እንደሚጀምር እና እንዴት እንደሚበረታ እስካሁን በውል አይታወቅም። ለዚህም የበለጠ ጥናት መደረግ አለበት። ህመምተኞቹ በበሽታው ከመያዛቸው በፊት ወይም ልክ በበሽታው መያዝ ሲጀምሩ የሚያሳይ የአእምሮ ምስል አልተገኘም።

ስለዚህም ተመራማሪዎቹ የአእምሮ ክፍሎቹ አለመግባባት በሽታውን ይፍጠረው ወይም በሽታዉ አለመግባባቱን ይፍጠር ለማወቅ ተቸግረዋል።