አረጋውያንን በነጻ የሚያሳፍረው ባለታክሲ

ማርቆስ ዘሪሁን Image copyright ማርቆስ ዘሪሁን

ማርቆስ ዘሪሁን ብዙ በረከት ከተቸረው ባለታክሲዎች አንዱ ሳይሆን አይቀርም። በአዲስ አበባ ከተማ የላዳ ታክሲ አገልግሎት በመስጠት ነው የሚተዳደረው። ታዲያ በላዳው የጀርባ መስታወት ላይ ዕድሜያቸው ለገፉና ለአቅመ ደካሞች የነጻ አገልግሎት እሰጣለሁ የሚል ጽሑፍ ከስልክ ቁጥር ጋር አስቀምጧል።

አቅመ ደካሞችን በመንገድ ላይ እያዩ ማለፍ ይከብደኛል የሚለው ማርቆስ በተለይ ነፍሰጡሮችን ዝም ብሎ ለማለፍ ልቡ ስለማያስችለው ገንዘብ ሳይጠይቅ በነፃ ወደሚፈልጉበት ቦታ ይወስዳቸዋል።

ይህ ተግባሩ በብዙ ሰዎች ዘንድ እውቅና ያሰጠው ማርቆስ በአካባቢው ባይኖር ብዙ ሰዎች በስልክ ደውለው ይጠሩታል። እሱም የተለመደ መተባበሩን ያከናውናል።

''ሥራ ላይ ካልሆንኩኝ በፍጥነት ሄጄ እተባበራቸዋለሁ። '' ይላል

አምስት ነጥቦች ስለቀጣዩ የሕዝብ እና ቤት ቆጠራ

በሰው ክፋይ ሕይወት መዝራት - የኩላሊት ንቅለ ተከላ

''ታክሲው ባዶ ሆኖ መሄድም ቢሆም አልወድም። ''

እንደዚህ ዓይነት ሰዎችን የመተባበር ሥራ ላይ ስታተኩር ዋናው ሥራህ ጋር አይጋጭብህም ወይ? ስንል ለማርቆስ ጥያቄ አቅርበንለት ነበር።

''ሲጀመር እኔ ምንም አላስበውም፤ ከሥራዬም ጋር እስካሁን የተጋጨብኝ ነገር የለም። እንደውም መጀመሪያ ያንን ሥራ አስቀድሜ ከጀመርኩ ቀኔ ደስ የሚል ሆኖ ነው የሚውለው'' በማለት ይመልሳል።

በጠዋት ከቤት ሲወጣ ለትራንስፖርት አገልግሎት የተሰለፉ ዕድሜያቸው የገፋ ሰዎችን ሲመለከት ሁለትም ይሁን ሦስት ፌርማታ ድረስ የሚፈልጉበት ቦታ ያደርሳቸዋል። አንዳንዴ አምስትም ስድስትም ሊወስድ እንደሚችል ይናገራል።

አንዳንድ ጊዜም ደንበኛ ጭኖ እየሄደ እንኳን አቅመ ደካሞችን ሲመለከት አስፈቅዶ ሰዎቹን እንደሚጭናቸው ይናገራል።

ደንበኞችህ፣ ጓደኞችህና ሌሎች በአቅራቢያህ ያሉ ሰዎች ምን ይሉሃል? ለሚለው ጥያቄ መልስ ሲሰጥ፣ ''ደንበኞች በጣም ደስ ይላቸዋል። አንዳንዶቹ እኔ በምሄድበት መንገድ ከሆነ ምንም ችግር የለውም ይላሉ። ሌሎቹ ደግሞ የሚሄዱበት መንገድ ካልሆነ ደስተኞች አይሆኑም'' ብሏል።

''ሁሉም ሰው አንድ ዓይነት አስተሳሰብ ሊኖረው አይችልም። ጓደኞቼ ደግሞ ''በርታ፣ ጠንክር እኛ ያላሰብነውን ነገር ነው እያደረግክ ነው ያለኸው ይሉኛል።''

የላዳ ታክሲ አገልግሎት መስጠት ከጀመረ ሁለት ዓመት የሆነው ማርቆስ፤ በሹፌርነት ተቀጥሮ በሚሠራበት ወቅትም ይህንኑ ተግባር ያከናውን እንደነበር ይናገራል።

Image copyright ማርቆስ ዘሪሁን
አጭር የምስል መግለጫ ''ታክሲው ባዶ ሆኖ መሄድም ቢሆም አልወድም። ''

''ወደ ተለያዩ ቦታዎች ስላክ ብዙ ጊዜ ብቻዬን ስለሆነ የምሄደው በመንገዴ ያገኘኋቸውን ሁሉ እየጫንኩ አልፍ ነበር። ተቀጣሪ እንደመሆኔ የመኪናው ባለቤቶች ደስተኞች አይሆኑም። እኔ ግን ዝም ብዬ የተቸገሩ ሰዎችን ሳገኝ እተባበር ነበር።''

'' እንደውም የራሴ መኪና ቢኖረኝ እኮ እንደልቤ እሠራ ነበር እያልኩ እመኝ ነበር፤ አሁን ይኸው የተመኘሁትን ነገር እያደረግኩ ነው።''

ማርቆስ ይህንን በጎ ተግባር ሲፈጽም ሁሉም ነገር አልጋ በአልጋ እንዳልሆነ ይናገራል።

ለ10 ዓመታት እጆቹን ያልታጠበው የቴሌቪዥን አቅራቢ

ሜድ ኢን ቻይና- የሀገር ባህል አልባሳቶቻችን

አንዳንድ ሰዎች ተቸግረናል እዚህ ቦታ ቶሎ ድረስልን ብለው ደውለውለት እሱ በቦታው ደርሶ ሲደውልላቸው አውቀን ነው፤ እውነተኛ መሆንህን ለማረጋገጥ ፈልገን ነው የሚል ምላሽ እንደሚሰጡት ይናገራል።

''ረጅም መንገድ ተጉዤና ያንን ሁሉ ጊዜዬን አባክኜ እንዲሁም ነዳጄን ጨርሼ በቦታው ስደርስ 'ታማኝነትህን ለማረጋገጥ ነው' የሚሉ ሰዎች ናቸው ትንሽ ያስቸገሩኝ።''

ከዚህ በተረፈ ግን እስካሁን ምንም ችግር እንዳላጋጠመው የሚናገረው ማርቆስ ወደፊትም ቢሆን ይህንን በጎ ተግባሩን እንደሚቀጥልበት ጽኑ እምነቱ ነው።