በኮዬ ፈጬ ኮንዶሚኒየም የተቀሰቀሰው ውዝግብ

እስክንድር ነጋ፣ ጃዋር መሀመድ Image copyright Getty Images/ MAHEDER HAILESELASSIE TADESE

የጋራ መኖሪያ ቤቶች በዕጣ ተላልፎ መሰጠት ከፍተኛ ተቃውሞ የቀሰቀሰውን የአዲስ አበባና የኦሮሚያ የተቀናጀ ማስተር ፕላንን ማስቀጠል ነው የሚል ሀሳብ በከፍተኛ ሁኔታ እየተንፀባረቀ ሲሆን፤ ይህም ሁኔታ በተለያዩ የኦሮሚያ ክልል ከተሞች ተቃውሞን አስነስቷል። በትናንትናው ዕለት የተቀሰቀሰው ተቃውሞ በዛሬው ዕለትም እንደቀጠለ ነው።

የጋራ መኖሪያ ቤቶቹ የተገነቡት በኦሮሚያ ክልል አካባቢዎች ፤ ለአርሶ አደሮችም በቂ ካሳ ሳይከፈል ነው የሚሉ ሃሳቦች እየተነሱ ነው።

ከሻሸመኔ ቢቢሲ ያናገረው አንድ ተቃዋሚም ይህንኑ ሀሳብ ያጠናክራል።

የጋራ መኖርያ ቤቶቹ በዕጣ መተላለፋቸውን የኦሮሚያ ክልል ተቃወመ

"ኮንደሚኒየሞቹ የተሰሩት ከአዲስ አበባ ዙሪያ ወጥቶ ነው። እንዴት ነው የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር እንዲህ አይነት ውሳኔ የሚያስተላልፈው?። ቤቶቹ በኦሮሚያ ክልል ስር ተመልሰው የተፈናቀሉ አርሶ አደሮችን ሊቋቋሙባቸው ይገባል" ይላል።

ከሰሞኑ 51 ሺህ 229 የጋራ መኖሪያ ቤቶች በዕጣ የተላለፉ ሲሆን፤ ከአካካቢው ለተነሱ አርሶ አደሮችና ልጆቻቸው ያለ እጣ እንዲሰጣቸው በከተማው አስተዳደር ካቢኔና በቤቶች አስተዳደር ውሳኔ መሰረት እንዲተላለፍ መወሰኑን ምክትል ከንቲባ ታከለ ኡማ ገልፀዋል።

ዕጣ የወጣባቸው የጋራ መኖሪያ ቤቶች በኦሮሚያ ተቃውሞን ቀሰቀሱ

የጋራ መኖሪያ ቤቶቹ ሲገነቡ የተጎዱ ሰዎች እንዳሉ የተናገሩት ምክትል ከንቲባው "በተለይም የእርሻ መሬታቸውን ለነዚህ ተግባራት ሲሉ የለቀቁና ለኢኮኖሚና ማህበራዊ ቀውስ የተዳረጉ የአርሶ አደር ቤተሰቦችና ልጆቻቸው ህመማችሁ የእኛም መሆኑን እንድታውቁ" የሚል መልእክት አስተላልፈዋል።

ምክትል ከንቲባው ይህንን ቢሉም ውሳኔውን የተቃወሙት ብዙዎች ናቸው። በተለይም ለአመታት ተቸግረውና ካለቻቸው ቆጥበው ለከፈሉ ሰዎች እርምጃው ተቀባይነት ያለው አይመስልመ።

አንድ ስሟ እንዲገለፅ ያልፈለገች የአዲስ አበባ ኗሪ "ከደመወዛችን ላይ የቤት ኪራይ ከፍለን፤ ቆጥበን እንግዲህ ያልፍልናል፤ ነገ የቤት ባለቤት እሆናለን በሚል ተስፋ ነው። በጣም ከፍተኛ ተስፋ ነበረኝ፤ ቤቶቹንም አይቻቸዋለሁ። አሁን ይሄንን ስሰማ ደግሞ የባሰ ነው የተበሳጨሁት፤ እኛ እየቆጠብን ሰው አመፅ ስላስነሳ ያለ ዕቅድ እንደዚህ መደረግ የለበትም።መንግስት የራሱን ነገር ማድረግ አለበት" ብላለች

የኮንዶሚኒየሙ ለአዲስ አበባ ኗሪ መተላለፍ ፤ ኦሮሚያ ውስጥ ተቀስቅሶ ለረጅም ጊዜ ለዘለቀው ሕዝባዊ ተቃውሞ መነሻ ምክንያት እንደሆነ የሚነገርለትና ከ2006 ጀምሮ ተግባራዊ ይደረጋል ተብሎ የነበረው የአዲስ አበባና በዙሪያዋ ያሉ የኦሮሚያ ከተሞች የተቀናጀ ማስተር ፕላን ቅጥያ ነው ከሚሉት አንዱ ጃዋር መሀመድ ነው። የጋራ ቤቶቹ በዕጣ መተላለፍ ፍፁም ኢ ፍትሀዊ ነው ይላል።

ቤቶቹ ከዚህ ቀደም የነበረው የማስተር ፕላኑ አካል እንደሆነ የሚናገረው ጃዋር፤ ማስተር ፕላኑ ከህግ ውጪ በመሆኑ እንዲቆም ከተደረገ በኋላ ይህንን ለመተግበር መንቀሳቀስ ትክክል እንዳልሆነና፤ የህዝቡም ተቃውሞ ምንጭ ይሄ መሆኑን ይናገራል።

"አሁንም ቢሆን ፊንፊኔ የኦሮሚያ ዋና ከተማ ነች። ክልል አይደለችም። የሁለት ክልሎች ግጭትም አይደለም። ማንኛውም ከተማ ድንበር አለው።ለምሳሌ አዳማ ከተማ ድንበር አለው፤ ወለንጪት ሄዶ ቤት ሠርቶ ማስተላላፍ አይቻልም። አርሶ አደሮችን የማፈናቀል ሂደት ደግሞ ፊንፊኔን ከሌላ ክልል ጋር የማገናኘት የማስተር ፕላኑ እቅድ ነበር። ሕግን አፍርሶ የተገነባና አሁንም ሕግን አፍርሶ ለማስተላለፍ እየተደረገ ያለ ጥረት ነው።" ይላል።

የአዲስ አበባና የኦሮሚያ ድንበር ወሰንን ለማስመር ከዓመታት በፊት የተጀመረው ጥረት ባልተጠናቀቀበት ሁኔታ ኮንዶሚኒየሞቹ ኦሮሚያ ክልል ናቸው በሚል እጣው እንዴት ይቆማል የሚል መከራከሪያ የሚያነሱም ጥቂት አይደሉም።

ሃምሳ በመቶ የሚኒስትሮች ሹመት ለሴቶች

የሰብአዊ መብት አቀንቃኙና ጋዜጠኛ እስክንድር ነጋ በበኩሉ ተቃውሞው የጥቂቶች እንቅስቃሴ ነው ይላል። ትርጉም የሌለው ጥያቄም ነው ብሎ ያጣጥለዋል። ህዝቡን ለመከፋፈል እየተሰራ ያለ ሴራም ነው ብሎ ያምናል።

"አሁን ይሄንን ግርግር እየፈጠሩ ያሉ ጥቂቶች ናቸው። እዚህ ላይ መሰመር ያለበት እነዚህ ጥቂቶች ምንን ነው የሚወክሉት? የሚለው ወሳኝ ጥያቄ ነው። ፀረ ዲሞክራሲያዊ፤ ፀረ-አንድነት የሆኑ እንቅስቃሴዎች ናቸው። ሁላችንም የዲሞክራሲ ሃይሎችና ወዳጆች፣ የኢትዮጵያ አንድነት ወዳጆች አጥብቀን ልንታገለው ይገባል።" ይላል

የእስክንድርን ሃሳብ የሚጋሩት አቶ ኤፍሬም ማዴቦ የጋራ መኖሪያ ቤቶች በዕጣ መተላለፍ የለባቸውም የሚለው ተቃውሞ ትክክል አይደለም ሲሉ የግል አስተያየታቸውን ይሰጣሉ።

ፍትሃዊ አይደለም የሚሉበት ምክንያት ለአመታት ገንዘብ ሲያጠራቅሙ የነበሩና በጉጉት ሲጠብቅ የነበረን ህዝብ አይገባውም ማለት ኢዲሞክራሲያዊ ነው ብለው ማመናቸው ነው።

"በአዲስ አበባ አካባቢ የተገነቡ ቤቶች በተለይ ደሃው ወይም መካከለኛ ገቢ ያለው ማህበረሰብ ለብዙ አመታት ገንዘብ እየቆጠበ፤ በገንዘቡ እየተሰሩ ያሉ አፓርትመንቶች ናቸው። በነፃ የሚታደል አፓርትመንት አይደለም። እነዚህ ግለሰቦች ለአመታት ጠብቀው፤ደረሰኝ ፤ አልደረሰኝ እያሉ በጉጉት በሚጠብቁበት ጊዜ ይሄ የእጣው ሂደት መቆም አለበት የሚለውን አስተያየት በጭራሽ አልተቀበልኩትም፤ ፍትሃዊም አይደለም።"ብለዋል

ተያያዥ ርዕሶች