አዲሱ የአማራ ክልል ርዕሰ መስተዳድር ዶ/ር አምባቸው ማን ናቸው?

አዲሱ የአማራ ክልል ርዕሰ መስተዳድር ዶ/ር አምባቸው መኮንን Image copyright FBC

ዛሬ በክልሉ ምክር ቤት ፊት ቀርበው ቃለ መሃላ የፈጸሙት አዲሱ ተሿሚ ዶ/ር አምባቸው መኮንን የተጣለባቸውን ኃላፊነት "ከባድ፥ የሚያስጨንቅና በውስብስብ ፈተናዎች የተሞላ..." ሲሉ ነበር የገለጹት።

ደቡብ ጎንደር ጋይንት ያደጉት ዶ/ር አምባቸው ለመሆኑ የትምህርትና የአስተዳደር ዝግጅታቸው ምን ይመስላል?

ዶ/ር አምባቸው መኮነን ሲሳይ አሁን የ48 ዓመት ጎልማሳ ናቸው።

የጋራ መኖርያ ቤቶቹ በዕጣ መተላለፋቸውን የኦሮሚያ ክልል ተቃወመ

በልጅነታቸው የፊዚክስና የሒሳብ ትምህርትን አብልጠው ይወዱም ነበር። ሕልማቸውም መምህር መኾን ነበር።

የ2ኛ ደረጃ ትምህርታቸውን በወቅቱ በነበረው ጦርነት ምክንያት ለማቋረጥ ተገደዋል። ከዚያም ትግሉን ከተቀላቀሉ ከ5 ዓመት በኋላ ያቋረጡትን ትምህርት በርቀት አጠናቀዋል።

የመጀመርያ ዲግሪን የተከታተሉት በኢትዮጵያ ሲቪል ሰርቪስ ዩኒቨርስቲ ነው። የድኅረ ምረቃ ትምህርታቸውን ደግሞ ደቡብ ኮሪያ ከሚገኘው ኬዲአይ የፐብሊክ ፖሊሲና አስተዳደር ትምህርት ቤት ተከታትለዋል።

የአማራ ክልል ርእሰ መስተዳድር አቶ ገዱ አንዳርጋቸው መልቀቂያ አቀረቡ

በቅድመ ምረቃም ኾነ በድኅረ ምረቃ ያጠኑት የትምህርት ዘርፍ ምጣኔ ሐብትን ነው።

ከኮሪያ ተመልሰው ለ11 ዓመታት በተለያዩ የሥራ ኃላፊነቶች ካገለገሉ በኋላ ለሦስተኛ ዲግሪ ወደ እንግሊዝ አቅንተዋል።

ሦስተኛ ዲግሪያቸውንም እንዲሁ በምጣኔ ሐብት ዙርያ ከእንግሊዙ ኬንት ዩኒቨርስቲ ነው ያገኙት።

የጥናት ወረቀታቸው ርእስ "የምጣኔ ሐብት ዕድገት፣ ንግድና ኢንቨስትመንት ከሰሀራ በታች ባሉ አገሮች" የሚል ነበር።

በበጀት እጥረት ምክንያት ሦስተኛ ዲግሪያቸውን ለማቋረጥ ጫና እንደነበረባቸው፣ ጓደኞቻቸው ገንዘብ በማዋጣት ጭምር ያግዟቸው እንደነበር ከዚህ ቀደም ካፒታል ለተሰኘ ጋዜጣ በሰጡት ቃለ ምልልስ ተናግረዋል።

የዩኒቨርሲቲ ተማሪዎች ንቅናቄ ትናንት እና ዛሬ

ዶ/ር አምባቸው ከትጥቅ ትግሉ በኋላ ከወረዳ ጀምሮ አስተዳደራዊ አገልግሎት ሰጥተዋል። በዋናነት ከሚጠቀሱት መሀል በአማራ ክልል የሥራ አመራር ኢንስቲቲዩት ዳይሬክተር፣ የብአዴን ማዕከላዊ ኮሚቴ ጽሕፈት ቤት ኃላፊ፣ ለአማራ መልሶ መቋቋምና ልማት ድርጅት ዋና ዳይሬክተር፣ የአማራ ክልል ንግድና ኢንዱስትሪ ቢሮ ኃላፊ እንዲሁም የኢንዱስትሪ እና ከተማ ልማት ቢሮ ኃላፊነቶች ይገኙበታል።

በፌዴራል ደረጃ ደግሞ የኮንስትራክሽን ሚኒስቴር ሚኒስትር ኾነው ለአንድ ዓመት ያህል አገልግለዋል። ከዚያ በኋላም የከተማ ልማት እና ቤቶች ሚኒስቴር መሥሪያ ቤትን በሚኒስትርነት ለአንድ ዓመት ተኩል ያህል ጊዜ መርተዋል።

ከግንቦት 2010 ዓ.ም ጀምሮ የኢንዱስትሪ ሚኒስቴር ሚኒስትር ሆነው ከአንድ ዓመት ላነሰ ጊዜ ያገለገሉ ሲሆን፣ ከሕዳር 2011 ዓ.ም ጀምሮ ይህንን የክልል ፕሬዝዳንትነት ሹመት እስካገኙበት ድረስም በጠቅላይ ሚኒስትር ጽሕፈት ቤት የመሠረተ ልማት አማካሪ ሚኒስትር ኾነው በማገልገል ላይ ነበሩ።

ዶ/ር አምባቸው ከለውጡ በኋላ ለርዕሰ ብሔርነት ታጭተው እንደነበርና ሕዝቡም ሆነ ፓርቲያቸው በፖለቲካው ተሳትፎ እንዲቀጥሉ በመፈለጋቸው ሐሳባቸውን መቀየራቸው ይነገራል።

*መረጃዎቹ በከፊል የተገኙት ከካፒታል ጋዜጣና ከአማራ መገናኛ ብዙኃን ኤጀንሲ ነው

ተያያዥ ርዕሶች