ሁለት እምነቶችን በአንድ ጣራ ለአስርታት ያሳደሩ ጥንዶች

ሶፍያ እና ወንድሙ

የኮምቦልቻዎቹ ጥንዶች ሶፍያ ሰይድ እና ወንድሙ ነጋ የተገናኙት በአስራ ዘጠኝ ሰማንያዎቹ መጨረሻ ነው። ሁለቱም ገራገር ተማሪዎች ሳሉ።

"መንገድ ላይ ከጓደኞቼ ጋር የእግር ጉዞ እያደረገን እያለ ነው ያየኋት። እንዳየኋት ወደድኳት" ይላል ወንድሙ ሁለት አስርት ዓመታት የተሻገረውን የአብሮነት ጥንስስ ሲተርክ።

መተያየት ወደትውውቅ፥ እርሱም ወደ ፍቅር ግንኙነት ሲያድግ ጊዜ አልፈጀበትም። ለጥቆም ትዳር መጣ። ልጆች ተከታተሉ። ሶፍያ የእስልምና እምነቷን እንደያዘች፥ ወንድሙም ከክርስትና የኃይማኖት ጎዳና ፈቀቅ ሳይል።

"መጀመሪያ ስንገናኝ የኃይማኖታችን መለያየት ብዙም ችግር ሆኖ አልታየኝም" ትላለች ሶፍያ። "ልጅነትም ስለነበረ ስለዚህ ጉዳይ አጥብቄም አላሰብኩበትም።"

"ከመቶ ምናምን ፓርቲ ሴት የምናገኘው አንድ ወይም ቢበዛ ሁለት ሊሆን ይችላል" ወይዘሪት ብርቱካን ሚደቅሳ

ከዚህም ባሻገር ግን የኃይማኖት ልዩነት በትዳር ለመጣመር ደንቃራ ላለመሆኑ በዙሪያቸው ሲያዩት የኖሩት እውነታ መተማመን ፈጥሮባቸውም ይሆናል።

ኮምቦልቻ በምትገኝበት የደቡብ ወሎ ዞን ከሁለት የተለያዩ ኃይማኖቶች የመጡ ጥንዶች መሥርተዋቸው ለረጅም ዘመናት የዘለቁ ትዳሮችን ማግኘት እንግዳ አይደለም።

ወላጅ፥ አያት፥ ቅድመ አያቶቻቸውን ሲቆጥሩ የተለያዩ ኃይማኖቶች መነሻዎች ያሏቸውም ጥቂቶች አይደሉም።

ብዙ ጊዜ ግን በጋብቻ ማግስት ባል የሚስትን እምነት ወይንም በግልባጩ ሚስት የባልን ኃይማኖት ተቀብለው አዲስ የሚመሠረተው ቤተሰብ ተመሳሳይ እምነት ሲኖረው ይስተዋላል።

ሶፍያ እና ወንድሙም በትዳራቸው የማለዳ ወራት የኋላ ኋላ አንዳቸው ወደሌላኛቸው ኃይማኖት እንደሚያመሩ ቃል ተገባብተው ነበር።

ይሁንና ከሃያ አመታት በኋላ እርሷ ከመስጂድ እርሱ ከቤተ ክርስትያን ደጆች ሳይነጣጠሉ አሉ። "አምላክ ባለው ጊዜ ይሆናል" ይህንን አስመልክቶ ሁለቱም የሚሰጡት ማብራሪያ ነው።

ከወዳጆች፥ ከጎረቤቶች እንዲሁ ከዘመዶች ግን የ'ለምን አንድ አትሆኑም?' ጥያቄዎች ደጋግመው መምጣታቸው አልቀረም።

ዶ/ር አምባቸው ማን ናቸው?

በተለይ ከወላጆቻቸው። የወላጆቻቸውም ጥያቄ ከአካባቢው ሰዎች ግፊት የመነጨ ሳይሆን እንደማይቀር ይገምታሉ።

"ከሰዎች የምትሰማው ይከብዳል፤ እኛ ግን እየኖርን ነው" ትላለች ሶፍያ።

ሦስቱ ልጆቻቸው ናትናዔል፥ ኤፍሬም እና ፍላጎት ወደ እናታቸው እምነት አዘንብለዋል።

ይሄንን አስመልክቶ አባት ወንድሙ "ትልልቆቹ ፆም ይፆማሉ፤ ሶላትም ይሰግዳሉ፤ ትንሿም ቁርዓን ትቀራለች። እምነታቸውን አከብራለሁ፤ በዓላቸው እንዲደምቅ እጥራለሁ። ለምን የእኔን እምነት አልተከተልክም'፤ ለምን አብረኸኝ ቤተክርስትያን አልሄድክም ብዬ አንድም ልጅ አስጨንቄ አላውቅም፤ እግዚአብሄር ያለው ስለሆነ የሚሆነው። ማንም የምንም ኃይማኖት ተከታይ ይሁን ብቻ ዋናው ነገር መልካም ሰው እንዲሆን ወላጆቹን የሚያከብር እንዲሆን [ማድረግ ነው]" ሲል ይናገራል።

የአስራ ዘጠኝ ዓመቱ ናትናዔል (በእናቱ በኩል ያሉት የሴት አያቱ አቡበከር ሲሉ ይጠሩታል) በኮምቦልቻ ፖሊቴክኒክ ኮሌጅ የምግብ አስተዳደር ተማሪ ነው።

የኮንዶሚኒየሙ እሰጣገባ

የወላጆቹን ታሪክ የማያውቁ የትምህርት ቤት ጓደኞቹ ከስሙ ብቻ በመነሳት ክርስትያን አድርገው እንደሚያስቡት ሲነግረን እየሳቀ ነበር። የእስልምና እምነት ተከታይ መሆኑ ሲያውቁ ደግሞ አግራሞት ያሸንፋቸዋል።

ወላጆቹ በእምነትም ሆነ በሌላ ጉዳይ እምብዛም ጫና አንደማያሳድሩበት የሚናገረው ናትናዔል በመካከላቸው ቅራኔ ብዙም ሲፈጠር አይቶ አንደማያውቅም ጨምሮ ይገልፃል።

የኃይማኖት መለያየት "ትልቅ ክፍተት ቢመስልም እኛ ጋ እንደክፍተት አይደለም" ሲል ያስረዳል።

ናትናዔል ከወንድም እና እህቱ ጋር በክርስትና ኃይማኖት የሚከበሩ በዓላት በሚኖሩበት ጊዜ ወደ አባታቸው ወንድሙ ወላጆች ቤት ሄዶ ያከብራል። "ጥምቀት ሲሆን ደግሞ እዚህ ጓደኞቼ ጋር እንሄዳለን።

"ወንድሙ ትዳራቸውን የአካባቢው ኃይማኖታዊ መከባበር ትዕምርት አድርጎ ይመለከተዋል።

በደቡብ እና በሰሜን ወሎ የክርስትና እና እስልምና ኃይማኖት ተከታዮች ትዳር መመሥረታቸው እንደነውር ያለመቆጠሩን እውነታ በኩራት ያወድሰዋል።

"ይህ ማለት እምነት ያለማወቅ አይደለም። ወሎ የመቻቻል አገር ነው" ይላል።

ተያያዥ ርዕሶች