ቻይና በቦይንግ 737 ማክስ 8 የሚደረጉ በረራዎችን አገደች

ቦይንግ 737 አውሮፕላን Image copyright Getty Images

ንብረትነቱ የኢትዮጵያ አየር መንገድ የሆነ ቦይንግ 737 አውሮፕላን ትላንት መከስከሱን ተከትሎ የቻይና አየር መንገዶች በቦይንግ 737 ማክስ 8 የሚደረጉ በረራዎችን እንዲያቆሙ የሃገሪቱ ኤቪዬሽን ተቆጣጣሪ መስሪያ ቤት አስታወቀ።

ማንኛውም የንግድ በረራ የሚያካሂዱ የቻይና አየር መንገዶች ከዛሬ ጠዋት 12 ሰአት ጀምሮ አውሮፕላኑን መጠቀም አይችሉም ተብሏል።

አውሮፕላኑ ከቦሌ አለም አቀፍ አውሮፕላን ማረፊያ የተነሳው ጠዋት 2፡38 ሲሆን ከ6 ደቂቃ በኋላ ከአብራሪዎቹ ጋር ይደረግ የነበረው ግንኙነት ተቋርጦ ከደቂቃዎች በኋላ መከስከሱ ተረጋግጧል።

ቦይንግ 737 ማክስ 8 ከተባለው አውሮፕላን ጋር በተያያዘ አደጋ ሲከሰት ባለፉት ስድስት ወራት ይህ ሁለተኛው ነው።

የዘርፉ ባለሙያዎች አደጋው በምን ምክንያት እንደተከሰት ለማወቅ ጊዜው በጣም ገና ነው ያሉ ሲሆን ባለፈው ጥቅምት ''የላየን'' አየር መንገድ ንብረት የሆነ ተመሳሳይ አውሮፕላን ተከስክሶ 189 ሰዎች ህይወታቸው ማለፉ ይታወሳል።

ዶ/ር አምባቸው ማን ናቸው?

የቻይናው ሲቪል ኤቪየሽን ባለስልጣን በሰጠው መግለጫ በአጭር ጊዜ ውስጥ አንድ የአውሮፕላን ሞዴል አደጋ ሲደርስበት በቸልታ ማለፍ ይከብደኛል ብሏል።

ቻይና ውስጥ ከ90 በላይ ቦይንግ 737 ማክስ 8 አውሮፕላኖች አገልግሎት የሚሰጡ ሲሆን ይህኛው ሞዴል ቦይንግ በቅርቡ በፈንጆቹ 2017 ዓ.ም. ነበር ለገበያ ያቀረበው።

የአውሮፕላኑ አምራች ኩባንያ ቦይንግ በበኩሉ በተፈጠረው አደጋ እጅግ ማዘኑን በመግለጽ የቴክኒክ ድጋፍ የሚሰጥና የአደጋውን መንስኤ ለማጣራት በሚደረገው ስራ ላይ እርዳታ የሚሰጥ ቡድን እንደሚልክ አስታውቋል።

የምርመራ ሂደቱም የሚመለከታቸው የኢትዮጵያ መስሪያ ቤቶች ከቦይንግ ባለሙያዎችና ከአሜሪካ የትራንስፖርት ደህንነት መስሪያ ቤት ጋር በመተባበር የሚካሄድ እንደሆነ ተገልጿል።

በኮዬ ፈጬ ኮንዶሚኒየም የተቀሰቀሰው ውዝግብ

የቻይና አየር መንገዶች የቦይንግ 737 ማክስ 8 አውሮፕላንን መጠቀም የሚችሉት የኤቪዬሽን መስሪያ ቤቱ ወደፊት በሚሰጠው መግለጫ መሰረት እንደሆነ አስታውቋል።

በትናንትናው ዕለት በቦይንግ 737 በረራ ቁጥር ET302 የ157 ሰዎችን ህይወት በቀጠፈው አሰቃቂ አደጋ ከሟቾቹ መካከል 8ቱ ቻይናዊያን መሆናቸው ታውቋል።