"ማብረርን ወደላቀ ደረጃ የማድረስ ህልም ነበረው"የረዳት አብራሪው አህመድ ኑር ጓደኛ

ረዳት አብራሪ አህመድ ኑር Image copyright FEKRUDIN

በቅርቡ የተከሰከሰው ቦይንግ 737 ማክስ 8 ረዳት አብራሪ የነበረው አህመድ ኑር ፓይለት ከመሆኑ በፊት በልደታ ህንፃ ኮሌጅ በአርክቴክቸር የትምህርት ክፍለ ዘርፍ እንደተመረቀ የሚናገረው በተቋሙ ሲማር በነበረበት ወቅት የዩኒቨርስቲ ጓደኛው የነበረው ፈክሩዲን ጀማል ነው።

ከጓደኝነት በተጨማሪ በዩኒቨርስቲ ቆይታቸው ለሶስት አመታት ያህል በአንድ ዶርም ውስጥ አድረዋል።

አህመድ ኑርን ለመግለፅ ቃላት ያጠረው ፈክሩዲን "አህመድ ኑርን ለመግለፅ ይከብዳል። በጣም የተረጋጋ ሰው ነበር። ምንም ነገር ሲያደርግ በጣም ተረጋግቶ ነው። ትዕግስተኛ ነው" ይላል።

"የሞተው የኔ ያሬድ ነው ብዬ አላሰብኩም" የካፕቴን ያሬድ የ11 አመት ጓደኛ

ፈክሩዲን እንደሚናገረው የአርክቴክቸር ትምህርት ፈታኝ ቢሆንም "አህመድ ኑር በተረጋጋ መንፈስ ነገሮችን ስለሚያከናውን ትምህርቱ እንደፈተነው መገመት ይከብዳል።" ይላል።

ለጓደኞቹ ፈጥኖ ደራሽ ነበር የሚለው የሰባት አመት በላይ ጓደኛው ፈክሩዲን "ማብረርን እንደ ጥናት ሳይሆን ወደላቀ ደረጃ የማድረስም ህልም ነበረው" ብሏል።

አብዛኛውን ጊዜም ስለበረራ ለጓደኞቹ ሲያስረዳ በአይነ ህሊናቸው እንዲታያቸው አድርጎ በጥልቀት እንደሚተነትንም ይገልፃል።

ለ60 ዓመታት የዘለቀው የኢትዮጵያ አየር መንገድና የቦይንግ ግንኙነት

"በሕይወቱ አቋራጭ ነገር ሲጠቀም አይቼው አላውቅም" ሁልጊዜም በአንድ ጉዳይ ላይ የጠለቀ እውቀት እንዲኖረው ስለሚፈልግም ጊዜውን እንደሚሰጥ ይናገራል።

Image copyright FEKRUDIN

ልደታ ተማሪ በነበረበትም ወቅት ለማብረር ከፍተኛ ፍቅር እንደነበረው የሚናገረው ፈክሩዲን በህይወቱ ቅድሚያ የሚሰጣቸውን ጉዳዮች አትኩሮት ሰጥቶም እንደሚከታተል ይገልፃል።

በማያጠናበት ወቅት እግር ኳስ ይጫወት የነበረ ሲሆን፤ ለቀድሞ የአማርኛ ሙዚቃዎች ለየት ያለ ፍቅር ነበረው።

" እኩል እድሜ ላይ ብንሆንም እኛ የማናውቀውን ሙዚቃ ይዘፍንና ይሄ ልጅ ግን መቸ ነው የተወለደው ያስብለን ነበር።" በማለት ፈክሩዲን ይናገራል።

ድሬዳዋ ተወልዶ ያደገው የ26 አመቱ አህመድረ ኑር ወደ አዲስ አበባ የመጣውም በዩኒቨርስቲ ድልደላ በምህንድስና የትምህርት ዘርፍ አዲስ አበባ ዩኒቨርስቲ ተመድቦ ነው።

ኢትዮጵያ አየር መንገድ ዛሬም ስኬታማ ነው

ተማሪ ሳሉ አዘውትሮ ቤተሰቦቹን ሊጎበኝ ድሬዳዋ ይመላለስ እንደነበር ያስታውሳል።

ከትምህርት ቤት ተመርቆ ከወጣ በኋላና የበረራ ትምህርቱን ከጀመረም ሆነ ማብረር ከጀመረ በኋላ በተቻለ መጠን ይገናኙ እንደነበር የሚናገረው ፈክሩዲን "ገና ጎጆ መውጣቱም ስለነበር፤ አብዛኛውን ጊዜ ወደኛ ቤትም ይመጣል። ከትምህርት አለም ወደስራ መግባቱም ስለነበር ብቻውን ነበር የሚኖረው።" ብሏል።

Image copyright FEKRUDIN

ለመጨረሻ ጊዜ የተገናኙት ከበረራው አንድ ቀን ቀደም ብሎ ቅዳሜ እለት ሲሆን የህንፃ አጨራረስ ቀለምና ጂፕሰም ላይ የሚሰራ ሌላ ጓደኛውን ከነ ፈክሩዲን ጋር ለማገናኘት ነበር።

"ቆይና ነገ ትሄዳለህ ብንለውም ነገ ወደ ኬንያ እበራለሁ ብሎን ወደ አመሻሹ 12 ሰአት ላይ ወደ ሰሚት ሊሄድ ተለያየን።" ይላል።

ከዚያም በኋላ ዜናውን የሰማው ኢትዮጵያ አየር መንገድ ከሚሰራ ትልቅ ወንድሙ ጋር እሁድ እረፋፈዱ ላይ ቁጭ ብለው ቴሌቪዥን በመመልከት ላይ በነበሩበት ወቅት ነው።

ወንድሙ የአደጋውን ዜና በኢንተርኔት ሲያይ በጣም ደነገጠ መጀመሪያ ያየውም ካፕቴን ያሬድን ነው።

"ካፕቴን ያሬድን አቀዋለሁ፤ ልጅ ነው። አብሬው ሁሉ በርሬ አውቃለሁ፤ ደስ የሚል ሰው ነው ብሎ ነገረኝ" ፈክሩዲን ቀጥሎም በረራው የት ነበር ብሎ ሲጠይቀው ወንድሙም ኬንያ ብሎ መለሰለት "በጣም ብደነግጥም በረራው ጠዋት እንዳልሆነ ራሴን አሳመንኩኝ፤ እሱ አለበት የሚለውንም ላለማመን ምክንያት ለራሴ ፈለግኩኝ። በቀን የተለያዩ በረራዎች ስላሉ በሌላኛው ይሆናል አልኩኝ" የሚለው ፈክሩዲን በዛው ሳያቆምም ለማጣራት ብዙ ጥረቶችን ማድረግ ጀመረ።

በመቀጠልም ጓደኞቹ ደዋውለው የበረራ ሰዓቱ ጥዋት መሆኑን ተረዱ። በዛም መንገድ ነው አስደንጋጭ ዜናውን የሰማው።

"ያው አምላክ ያመጣውን ነገር ምን ማድረግ ይቻላል፤ ለጓደኞቹ ብዙ ነገር ነው። በጣም እንደ አባት፣ ጓደኛ ፣ ወንድም የሚያዩት ነበሩ።" በማለት በሃዘን ገልጿል።

በዚህ ዘገባ ላይ ተጨማሪ መረጃ