የላሊበላ ቅርስ ጥገና ሥራውን የሚያከናውኑት ሴቶች

ፕሬዚዳንት ኤማኑኤል ማክሮ በላሊበላ ቅበላ ሥነ-ሥርዓት ላይ Image copyright OFFICE OF THE PRIME MINISTER

ፕሬዚዳንት ኤማኑኤል ማክሮ ከመጋቢት 3 ጀምሮ ለሁለት ቀን ይፋዊ ጉብኝት ለመጀመሪያ ጊዜ ወደ ኢትዮጵያ መምጣቸው ይታወሳል።

ይህ ጉብኝት ከምሥራቅ አፍሪካ ሃገራት ጉብኝታቸው የመጀመሪያቸው መድረሻ ሲሆን ቀጥለው ወደ ኬንያ አቅንተው ነበር።

የኢትዮጵያ ጉብኝታቸው ዋና ዓላማ በሁለትዮሽ ግንኙነት ላይ የሚያተኩርና አብሮ የመሥራት መንፈስን ለማጠናከር የታሰበ እንደሆነ ቢታወቅም፤ የኤማኑኤል ማክሮ ጉብኝት በላሊበላ መጀመሩና በላሊበላ ሹምሸሃ አየር መንገድ የመጀመሪያ ይፋዊ አቀባበል መደረጉ ለላሊበላ ብቻ ሳይሆን ለኢትዮጵያ ልዩ አድርጎታል።

ከጠቅላይ ሚኒስትር ዐብይ በቀረበላቸው ጥሪ መሠረት ጥያቄውን የተቀበሉት ማክሮ የላሊበላን ውቅር አብያተ ክርስቲያናት ጥገና በፈረንሳይ ድጋፍ በምን መልኩ ሊከናወን እንደታሰበ ከጥገናው ሥራ ጀርባ ያሉትን ባለሙያዎች አነጋግረናል።

ኢትዮጵያ እና ፈረንሳይ የተለያዩ ስምምነቶችን ተፈራረሙ

ፕሬዚዳንት ማክሮ አዲስ አበባ ገብተዋል

Image copyright CLAIRE BOSC-TIESSE
አጭር የምስል መግለጫ ቤተ ማሪያም ቤተ ክርስትያን እ.አ.አ በ2005

ከላሊበላ ጥገና በስተጀርባ

የፕሮጄክቱ መሪዎች ሴቶች ናቸው። እነርሱም ማሪ ሎር ዴራ እና ክሌር ቦሽ ቲዬሴ የሚባሉት የታሪክና አርኪዎሎጂ ተመራማሪ ምሁራን ናቸው።

ሁለቱም የፈረንሳይ ብሔራዊ ሳይንሳዊ ጥናት ማዕከል ሠራተኞች ቢሆኑም ከኢትዮጵያ ባህልና ቱሪዝም ሚኒስቴር ጋር በኢትዮጵያ አርኪዮሎጂና ታሪክ ላይ ሲሠሩ ሃያ ዓመታትን አስቆጥረዋል።

ከአሥር ዓመት በፊት ደግሞ 'ላሊበላ፡ የዋሻው አርኪዮሎጂና ታሪክ' [ላሊበላ፡ አርኪዮሎጂ ኤ ኢስቷር ደ ሲት ሩፔስትር] በተባለ ፕሮጄክት ላይ በመስራታቸው ነው የፈረንሳይና የኢትዮጵያ መንግሥታት የተስማሙበትን ላሊበላን በመጠገንና በማደስ ሥራ ላይ በዋነኝነት እንዲሳተፉ የተመረጡት።

ሴት መሆናቸው እስካሁን በነበራቸው የሥራ ቆይታቸው ላይ ከባድ ችግር ባይፈጥሩም "አልፎ አልፎ ግን እኛን ችላ የማለትና ወንዶቹን የማናገር ዝንባሌ አለ። አንዳንዴም ሴት መሆን ችግር የፈጠረባቸው አጋጣሚዎች አሉ" የምትለው ከፕሮጄክቱ ባለሙያዎች መካከል አንዷ የሆነችው ክሌር: በአጠቃላይ ግንየመጡበትን ዓላማም ሆነ ያላቸውን ብቃት በሚያብራሩበት ወቅት ነገሮች እንደሚስተካከሉና ያለችግር እንደሚቀጥሉ ትናገራለች።

ኢትዮጵያ እና ፈረንሳይ የተለያዩ ስምምነቶችን ተፈራረሙ

የላሊበላ ጥገና ለስንተኛ ጊዜ?

ክሌር ቦሽ ቲዬሴ ከዚህ በፊት በውቅር አብያተ ክርስቲያናቱ ላይ የተከናወነው ጥገና በአግባቡ አለመሠራቱ ብዙዎችን ቅር እንዳሰኘ ትናገራለች።

የጥገናና የእድሳት ሥራው በዩኔስኮ የዓለም የቅርስ ዝርዝር ውስጥ ለተካቱት ለሁሉም የላሊበላ ውቅር አብያተ ክርስቲያናት በማድረግ እንድ ዓይነት እርምጃዎችን መውሰድ እንደማይቻልም ታስረዳለች።

ለእያንዳንዱ ቅርስ "የተለያየ መፍትሔ ሊገኝ ስለሚችል የምንወስዳቸው እርምጃዎች በእርጋታ የትሰበባቸውና ጥንቃቄ የተሞላበት ሥራ መሥራት ይኖርብናል" የምትለው ክሌር በአሁን ሰዓት የተጀመረው ሥራ ስፍራውን የማጥናት ተግባር እንደሆነም አብራርታለች።

የጥናቱ ሥራ ጥንቃቄን ስለሚጠይቅ ቢያንስ ከአንድ ዓመት እስከ አንድ ዓመት ተኩል ሊፈጅ እንደሚችልም ትናገራለች።

በዚህም በእያንዳንዱ የላሊበላ ህንፃዎች ላይ ተገቢው ጥናት ከተደረገ በኋላ መወሰድ የሚገባው እርምጃ ምን እንደሚሆን ለማወቅ ስለሚያስችላቸው ደግሞ አንድ በአንድ መፍትሔዎቹን ሥራ ላይ ማዋል እንደሚጀምሩ አሳውቃናለች።

በኢትዮጵያውያን ተሰርቶ የአውሮፓውያንን ድጋፍ የሻተው ላሊበላ

ምን ዓይነት ብቃት ያላቸውን ሰዎች ያሳትፋል?

በዚህ ሥራ ውስጥ ከታሪክን ወይም ደግሞ ከእርኪዎሎጂ አዋቂዎችን በተጨማሪ የተለያዩ ሙያተኞች እንደሚሳተፉ ክሌር ትናገራለች። ለምሳሌ በምህንድስና ዘርፍ የተሰማሩ ባለሙያዎች ከላሊበላ አብያተ ክርስትያት አወቃቀር አንፃር የሚኖራቸውን እውቀት በመጠቀም ለማደስም ሆነ ለመጠገን የሚያስፈልገውን ድጋፍ ያደርጋሉ።

በቡድኑ ውስጥ ያሉ ሌሎች ባለሙያዎች ደግሞ ከዚህ ቀደም የተሠራውን ከለላ አጥንተው አብያተ ክርስትያናቱን በማይጎዳ መልኩ ማንሳትና ወደፊት የሚሠራው ደግሞ በምን ዓይነት መልኩ መገንባት እንዳለበት አስፈላጊውን ሥራ ያከናውናሉ።

በቡድኑ ውስጥ የተካተቱት የአርኪዎሎጂ ባለሙያዎችም ከጥንት አፈር፣ ከተቀበሩ ነገሮች ይዘታቸውን በማይቀይር መልኩ እድሳቱን ለማከናወን ይረዳሉ። በተጨማሪም የጥንታዊ ሥዕሎች እድሳት ባለሙያዎችም በሥራው ውስጥ ተካተዋል። የእነርሱም በአብያተ ክርስትያናቱ ውስጣዊ ክፍሎች ያሉትን መንፈሳዊ ሥዕሎች ሳይበላሹና ይዘታችው ሳይቀየር እንዲቆዩ በማድረግ ትልቅ ሚና ይጫወታሉ።

Image copyright MARIE LAURE-DERAT

የላሊበላ ነዎሪዎች ቅርስ

ክሌር እንደምትለው ከሁሉም በላይ ለሥራው በአግባቡ መከናወን ትልቅ ሚና የሚኖረው በአካባቢው ማህበረሰብ ውስጥ የመካተት ስሜት ሲፈጠር ነው። እንደባለሙያ ከሥራው፣ ከሂደቱና ከሚያጋጥሙት መሰናክሎች ባሻገር የማህበረሰቡ ቅርስ እንደመሆኑ መጠን "ሁሉንም ነገር በግልፅነት መንፈስ ለእነርሱ እያስረዳን ነው መሄድ የሚኖርብን" ብላለች።

በሥራው ላይ የተሰማሩት ኢትዮጵያውያንና ፈረንሳውያን ባለሙያዎች ለሥራው እንጂ የቅርሱ ትርጉም እንደ የነዋሪውን ያህል ሊሆንላቸው እንደማይችል የምትገምተው ክሌር፤ አብያተ ክርስትያናቱ ለሃገሪቷ ትልቅ ቅርስ እንደመሆናቸው ከነዋሪዎቹ ጋር ግን ጥልቅ ትስስር እንዳላቸው ትናገራለች።

ለዚህም ነው "ሥራው ማህበረሰቡን ያቀፈ፤ የምንሠራው ሁሉም ነገር ገብቶትና ለሥራው የባለቤትነት ስሜት ኖሮት ደስተኛ እንዲሆን እንፈልጋለን" የምትለው።

ፈረንሳይና የኢትዯጵያ ቅርሶች

በአርኪዮሎጂ ዙሪያ ፈረንሳይ እና ኢትዯጵያ ትብብራቸውን ከጀመሩ ረጅም ዓመታትን አስቆጥረዋል።

እ.አ.አ በ1950 ዎቹ አፄ ኃይለ ሥላሴ ፈረንሳይ የአርኪዮሎጂ ክፍል ለመመሥረት ኢትዮጵያን እንድታግዝ ጋብዘው የነበረው።

ከዚያን ጊዜ አንስቶ የፈረንሳይ ድጋፍ በተለይ በአርኪዮሎጂና ታሪክ ረገድ ኢትዮጵያን አልተለያትም። ለዚያም ነው የፕሬዚዳንት ኤማኑኤል ማክሮ የጠቅላይ ሚኒስትር ዐብይ አሕመድን ጥሪ ተቀብለው ወደ ኢትዮጵያ ሲመጡ የነበረውን ግንኙነት የሚያጠናክር የሆነው።

ክሌር በላሊበላ ቅርስ ላይ ስትሠራ ከአሥር ዓመት በላይ ማስቆጠሯ እንደ ትልቅ ክብር እንደምትቆጥረው ትናገራለች። የእርሷ ደስታ ደግሞ የሃገሯም ደስታ እንደሆነ የማትጠራጠረው ክሌር "በተመራማሪ ዕይታዬ ፈረንሳይ በዚህ ሥራ መሳተፏ ፈረንሳይ ለቅርሶች ትልቅ ቦታን ስለምትሰጥ፤ ለዓመታት ያዳበረችውን የቅርስ ምርምር፣ የጥናትና የጥገና እውቀት በሌላ ሃገር ሥራ ላይ ማዋል በመቻሏ ደስተኛ ትሆናለች ብዬ መገመት አያቅተኝም" ብላለች።

በዚህ ዘገባ ላይ ተጨማሪ መረጃ