የማዕከላዊ ጎንደር ዞን ተፈናቃዮች ቁጥር እየጨመረ ነው

የማዕከላዊ ጎንደር ዞን ተፈናቃዮች

በማዕከላዊ ጎንደር ዞን በተፈጠረ ግጭት የሰው ሕይወት ጠፍቷል፤ ንብረት ወድሟል፤ በርካታ ሰዎችም ያፈሩትን ንብረትና የኖሩበትን ቀዬ ጥለው ወጥተዋል፡፡

ተፈናቃዮቹም በተለያዩ ጊዜያዊ መጠለያ ጣቢያዎች ይገኛሉ፡፡

ቢቢሲ አማርኛም በርካታ ተፈናቃዮች የሚገኙበትንና ከጎንደር በ38 ኪሎ ሜትር ርቀት ላይ በሚገኘው የአይምባ መጠለያ ጣቢያ ተገኝቶ ነበር፡፡

"እስካሁን ሙሉ የሰውነት ክፍል ማግኘት እንደተቸገርን ለቤተሰብ እያስረዳን ነው" አቶ ተወልደ ገ/ማርያም

በስፍራው የእርዳታ እህል ክፍፍል እየተደረገ ነበር የደረስነው፡፡ ሕጻናት፣ ነፍሰ ጡር ሴቶች ፣ አዛውንት፣ ወጣቶች መጠለያ ለማለት በሚያስቸግር ሁኔታ በእንጨት ግድግዳ ብቻ የቆሙ ጅምር ቤቶች ታዛ ስር ተኮልኩለዋል፡፡

ከወደ አንድ ጥግ በእድሜ የገፉ እናት ጋር ተጠጋን፤ እናት ካሴ ይባላሉ፡፡

እድሜያቸውን እንኳን በውል አያውቁትም፤ ማቄን ጨርቄን ሳይሉ ወደ መጠለያው የመጡት አንድ የልጅ ልጃቸውን ይዘው ነው፡፡

"የሞተው የኔ ያሬድ ነው ብዬ አላሰብኩም" የካፕቴን ያሬድ የ11 አመት ጓደኛ

ቀሪው የቤተሰብ አካል ግጭቱን ሸሽተው እንደወጡ በዚያው ቀርተዋል ይላሉ፡፡ ለእኝህ እናት ይህ የዘወትር ጸሎታቸው ከሆነ ሰነባብቷል፡፡

"አንተ ይቅር በለነ፣

የወጣውን የሚገባውነ በቸር የሚቆይ አርገነ፣

ከቤት ከጥቀርሻችን የሚያወጣ፣

ውጡ ከቤት ተነቀሉ ከመሬት የሚለነ፣

ምድጃ የሚያስለቅቅ አታምጣብነ፣

የሚሰማ መንግስት ስጠነ"

በጸሎታቸው 'ጥቀርሻ' ሲሉ የሚጠሩትን ቤታቸውን ናፍቀዋል፡፡ የነበራቸው ሀብትና ንብረት በምን ሁኔታ ላይ እንደሚገኝ ባያውቁም አሁንም ግን ደጃቸውን የሚረግጡበትን ቀን እየተጠባበቁ እንደሆነ ገልጸውልናል፡፡

ወጣት ሙሉ አስምረው ይኖበት የነበረውን አንከራ ደዛ ቀበሌ ከነ ቤተሰቡ ለቆ ከወጣ 2 ወራት ሆኖታል፡፡ ችግር ሸሽተው ቢመጡም በመጠለያው ጣቢያ የገጠማቸውም ያው መከራ እንደሆነ ይናገራል፡፡

"ህጻናትና ሴቶች ለብርድና ለርሃብ እየተዳረጉ ነው መጸዳጃ ቤት የለም፤ የጤና ባለሙያ አንድ ቀን መጥቶ ጎብኝቶን አያውቅም" የሚለው አስምረው በስፍራው አንድ የመድሃኒት መሸጫ ቢኖርም የመድሃኒት አቅርቦት የለም፡፡

በአንድ ቤት በርካታ ሰዎች በመኖራቸው ለከፋ ወረርሽኝ ይዳረጋሉ፤ ህጻናትና ሴቶችም ለጥቃት ይጋለጣሉ የሚል ስጋትም አለው፡፡

"የሚሰጠው ምግብ በቂ አይደለም፤ አርሶ ለሰው ሲተርፍ የነበረው አርሶ አደር በዚህ ሁኔታ በእርዳታ በመኖሩ ለስነ ልቦና ችግር ተዳርጓል" ሲልም ያክላል፡፡

እርሱ እንደሚለው በግጭቱ ሕይወታቸው ያለፈው አልበቃ ብሎ አሁንም በመጠለያው ጣቢያው በህመም ምክንያት የሰዎች ሕይወት ማለፉን እንባ እየተናነቀው ነግሮናል፡፡

አስምረው ወደቀዬው የመመለስ ፍላጎት ቢኖረውም አሁንም ግጭቱን የሚቀሰቅሱ ግለሰቦች በቁጥጥር ስር ካልዋሉ መመለሱ ለውጥ እንደማይኖረው ያስረዳል፡፡

"ከዚህ ቀደም መንግሥት ግጭት የሚፈጥሩ ግለሰቦችን በቁጥጥር ስር እንዳዋለ ቢገልጽም የተያዙት በጣም ጥቂት ናቸው" ሲል ይከሳል፡፡

ሌላኛዋ ያነጋገርናት ተፈናቃይ የአምስት ወር ነፍሰጡር ስትሆን የ3 ዓመት ልጇን ይዛ ነው የመጣችው፡፡ ከቤት ስትወጣ ከለበሱት ልብስ በስተቀር ይዘውት የወጡት ንብረት እንደሌለ ትናገራለች፡፡

የተከሰከሰው አውሮፕላን የመረጃ ሳጥን ወደ ፈረንሳይ ተወሰደ

እርሷ እንደምትለው እዚህ ከመጡም በቂ ማደሪያ እንኳን አላገኙም፡፡ ይህም ብቻ ሳይሆን የቅድመ ወሊድ ክትትሏን ለማቋረጥ ተገዳለች፡፡

"ሲያመኝ ችዬው ሲተወኝ ይተወኛል ከዚያ ውጭ የማደርገው የለም፤ ህጻናቱም ሲርባቸው ሲላቀሱ ነው የሚውሉት" ትላለች፡፡

የማዕከላዊ ጎንደር ዞን አደጋ መከላከልና ምግብ ዋስትና ተጠሪ ጽ/ቤት ኃላፊ አቶ መንበሩ አውደውን ቢሯቸው አቅንተን በተለይ በጊዜያዊ መጠለያ ጣቢያው ተፈናቃቹ ስላነሱት በቂ ያልሆነ የምግብ አቅርቦትና ሌሎች መሰረታዊ ፍላጎት አለመሟላት አነጋግረናቸው ነበር፡፡

እርሳቸው እንደሚሉት ለተፈናቃዮቹ የሚሰጣቸው ምግብ በዓለም አቀፍ ደረጃ ለአንድ ሰው ያስፈልገዋል የሚባለው መጠን እንደሆነ ያስረዳሉ፡፡ 8 ኪሎ ፊኖ ዱቄት፣ 4 ኪሎ ሩዝ፣ 11 ኪሎ ስንዴ፣ 3 ኪሎ ፋፋ ይደርሳቸዋል፡፡ ከዛ ውጭ የምናደርግላቸው የለም ሲሉ ይመልሳሉ፡፡

አካባቢው በቂ ውሃ የሌለው በመሆኑ ከጎንደር ከተማ በቀን 20 ሺህ ሊትር ውሃ ማጓጓዝ ግድ ሆኖብናል የሚሉት ኃላፊው የሳሙና እና ሌሎችም የንጽህና መጠበቂያ ቁሳቁሶች እጥረትም አለ፤መጠለያው ጣቢያ ከመጡ ሳሙና ያላገኙ እንዳሉ አልሸሸጉም፡፡

"አደጋውን ስሰማ በረራው ጠዋት እንዳልሆነ ራሴን አሳመንኩኝ" የረዳት አብራሪው ጓደኛ

"በመጠለያው ጊዜያዊ ጤና ኬላ ቢቋቋምም ስር የሰደዱ በሽታዎችን ለማከም ወደ ጎንደር ሆስፒታል ለመላክ ተገደናል" ብለዋል፡፡ የመድሃኒት እጥረትም በመጠለያው ፈተና ሆኗል፤ ይሁን እንጂ ችግሩን ለመፍታት ጥረት እያደረጉ እንደሆነ ገልጸዋል፡፡

እርሳቸው እንዳሉት ተፈናቃዮቹን በዘላቂነት ለማቋቋም ቀዳሚው የአካባቢውን ሰላም ማረጋገጥ በመሆኑ የክልሉ መንግስት ጸጥታ የማስከበር ስራ እየሰራ ነው፤የህዝብ ለህዝብ ግንኙነት ስራም ተጀምሯል፡፡

ለመቋቋም የሚያስፈልጋቸው የእርሻ ቁሳቁሶችና ፈጥነው የሚደርሱ ምርቶችን ተለይተው ታውቀዋል፡፡

ኃላፊው በግጭቱ 4361 ቤት መቃጠሉን ጠቅሰው የወደሙትን መልሶ ለመገንባት በክልሉ ከ1.5 ቢሊዮን ብር በላይ በማዕከላዊ ጎንደር ዞን ደግሞ 800 ሚሊየን ብር ገንዘብ እየተሰባሰበ ይገኛል፡፡ እስካሁን ለቤት መስሪያ የሚውል የቆርቆሮ ግዥ ተፈጽሟል፤ ጎን ለጎን የሰዎችን ስነ ልቦናና ማህበራዊ ቀውስ ለማስተካከልም እየተሰራ ነው ሲሉ አክለዋል፡፡

በአይምባ የመጠለያ ጣቢያ 9809 ተፈናቃዮች ተጠልለዋል፡፡ አይምባን ጨምሮ ትክል ድንጋይ፣ ጯሂት፣ ቆላ ድባ፣ አርባባ፣ ምስራቅ በለሳ፣ ስላሬ በሚገኙ መጠለያ ጣቢያዎች በአጠቃላይ 49700 ተፈናቃዮች ይገኛሉ፡፡ የተፈናቃዮቹ ቁጥርም ከጊዜ ወደ ጊዜ እየጨመረ መምጣቱን ኃላፊው ለቢቢሲ ገልጻዋል፡፡

ተያያዥ ርዕሶች

በዚህ ዘገባ ላይ ተጨማሪ መረጃ