የኢትዮጵያ አየር መንገድ አደጋ ከኢንዶኔዢያው ጋር ተመሳሳይነት እንዳለው ተነገረ

የአውሮፕላን ስባሪ Image copyright AFP

ከኢትዮጵያ አየር መንገድ አውሮፕላን ላይ የተገኘው የበረራ መረጃ አደጋው ባለፈው ጥቅምት ወር በኢንዶኔዢያ ባሕር ላይ ከተከሰከሰው አውሮፕላን ጋር ተመሳሳይነት እንዳለው እንደሚያመለክት የኢትዮጵያ ትራንስፖርት ሚኒስትር ገለጹ።

አደጋው የገጠማቸው ሁለቱ አውሮፕላኖች ቦይንግ 737 ማክስ ኤይት የተባሉ ሲሆኑ በደረሰባቸው አሰቃቂ አደጋ በውስጣቸው የነበሩ የሁሉም ተጓዦች ህይወት አልፏል።

ባለፈው ሳምንት ከአዲስ አበባ ከተነሳ ከጥቂት ደቂቃዎች በኋላ አደጋ የደረሰበት የኢትዮጵያ አየር መንገድ አውሮፕላን ይዟቸው የነበሩት 157 ሰዎች መሞታቸው ይታወሳል።

የተከሰከሰው አውሮፕላን የመረጃ ሳጥን ወደ ፈረንሳይ ተወሰደ

የካፕቴን ያሬድ ሃይማኖታዊ የሐዘን ሥርዓት ያለ አስከሬን ተፈፀመ

የአውሮፕላኑ የበረራ መመዝገቢያ ሳጥኖች ወደፈረንሳይ ባለፈው ሳምንት ተወስደው የነበረ ሲሆን፤ የትራንስፖርት ሚኒስትሯ የበረራ መረጃው ከአውሮፕላኑ የመረጃ ማስቀመጫ ክፍል ላይ በአግባቡ እንደተሰበሰበ ተናግረዋል።

ከአውሮፕላኑ የተገኘውና አደጋው ስለደረሰበት አውሮፕላን ለሚደረገው ምርመራ ጠቃሚ መረጃ ይሆናል የተባለው የበረራ መረጃ ምርመራውን ለሚያከናውነው ቡድን መሰጠቱም ተገልጿል።

ከተሰበሰበው መረጃም "በኢትዮጵያ እየር መንገድ አውሮፕላን ላይ የደረሰው አደጋ ከወራት በፊት በኢንዶኔዢያው ተመሳሳይ አውሮፕላን ላይ ከደረሰው አደጋ ጋር ግልፅ መመሳሰል ታይቷል" ሲሉ ሚኒስትሯ ተናግረዋል።

ለ60 ዓመታት የዘለቀው የኢትዮጵያ አየር መንገድና የቦይንግ ግንኙነት

"አደጋውን ስሰማ በረራው ጠዋት እንዳልሆነ ራሴን አሳመንኩኝ" የረዳት አብራሪው ጓደኛ

የበረራ መመዝገቢያ መረጃ እንደሚያመለክቱት በሁለቱም የአውሮፕላን አደጋዎች ላይ ድንገተኛ የከፍታ መለዋወጥ እንደታየ፤ ይህም አውሮፕላኖቹ ያልተጠበቀ ከፍና ዝቅ የማለት ተመሳሳይ አጋጣሚዎች እንደተስተዋለባቸው ተገልጿል።

የኢትዮጵያ የምርመራ ባለሙያዎች በጥቂት ቀናት ውስጥ ወደሃገራቸው እንደሚመለሱና ተጨማሪ መረጃዎችን ማግኘት እንደሚቻል ጠቁመው፤ "የመጀመሪያ ደረጃ የምርመራው ውጤት በ30 ቀናት ውስጥ ይፋ ይሆናል" ብለዋል ሚኒስትሯ።

የቦይንግ ኩባንያ ሊቀመንበርና ዋና ሥራ አስፈጻሚ የሆኑት ዴኒስ ሙሊንበርግ እንደተናገሩት ድርጅታቸው በአውሮፕላን አደጋው ዙሪያ በሚደረጉ ምርመራዎች ላይ አስፈላጊውን ድጋፍ እንደሚሰጥ አረጋግጠዋል።

"የሞተው የኔ ያሬድ ነው ብዬ አላሰብኩም" የካፕቴን ያሬድ የ11 አመት ጓደኛ

ከድርጅቱ በወጣው መግለጫ ላይ ሥራ አስፈጻሚው እንዳመለከቱት በአውሮፕላኑ ውስጥ ያለውን የበረራ መቆጣጠሪያ ሥርዓት የሚመራውን ሶፍትዌር ለማሻሻል እየሰራ እንደሆነም ተገልጿል።

የኢትዮጵያ አየር መንገድ አውሮፕላንን ምን ገጠመው?

የኢትዮጵያ አየር መንገድ በረራ 302 መጋቢት 01 ቀን 2011 ዓ.ም ጠዋት ከአዲስ አበባ ቦሌ አየር ማረፊያ በመነሳት ናይሮቢ ለመድረስ ነበር ዕቅዱ።

አውሮፕላኑ ከተነሳ ከጥቂት ደቂቃዎች በኋላ አብራሪው ችግር እንደገጠመው አመልክቶ ተመልሶ እንዲያርፍ ጠየቀ።

በአየር ሁኔታ ምክንያት ዕይታን የሚያስቸግር ነገር አልነበረም የሚለው የአየር ትራንስፖርት እንቅስቃሴን የሚከታተለው ፍላይትራዳር24 "አውሮፕላኑ ከተነሳ በኋላ ወደላይ የሚወጣበት ፍጥነት የተረጋጋ አልነበረም" ብሏል።

አደጋው በተከሰተበት ስፍራ ነበርኩ ያለ የዓይን እማኝ ለቢቢሲ እንደተናገረው አውሮፕላኑ መሬት ላይ ሲወድቅ ከባድ እሳት ተፈጥሮ ነበረ።

የፈረንሳይ የአየር ትራንስፖርት ደህንነት መርማሪዎች የአውሮፕላኑን የበረራ መረጃ መመዝገቢያንና የበረራ ክፍል የድምጽ መቅጃን በመመርመር ያገኙትን ምርመራውን ለሚያከናውኑት የኢትዮጵያ ባለሙያዎች አስረክበዋል።

በኢንዶኔዢያው አውሮፕላን ላይ ምን ተከሰተ?

ጥቅምት 19/2011 ዓ.ም የላየን ኤር በረራ 610 ከኢንዶኔዢያዋ መዲና ጃካርታ ከተነሳ በኋላ በመከስከሱ የ189 ሰዎች ህይወት አልፏል።

በኋላ ላይ የአደጋ መርማሪዎች እንደደረሱበት አውሮፕላኑ ሽቅብ በጣም ከፍ ወዳለ አቅጣጫ እንዳይወጣ የሚቆጣጠረው የአውሮፕላኑ ሥርዓት ላይ ችግር እንደነበረበት አመልክተዋል።

በዚህም ሳቢያ በዚህ በረራ ወቅት የመቆጣጠሪያ ሥርዓቱ በተደጋጋሚ አውሮፕላኑን ወደታች እንዲያዘቀዝቅ ያደርገው ነበር ተብሏል።

የአውሮፕላኑ የመቆጣጠሪያ ሥርዓት ወደታች እንዲያዘቀዝቁ ከማድረጉ በፊት አብራሪዎቹ ይህንን ችግር የአውሮፕላኑን አፍንጫ ወደላይ ከፍ በማድረግ ለማስተካከል ጥረት አድርገዋል። ይህም በአውሮፕላኑ ላይ ከሃያ ጊዜ በላይ እንደተከሰተ ተገልጿል።

የኢንዶኔዢያው አውሮፕላን ከተከሰከሰ ከወራት በኋላ በተመሳሳይ ሁኔታ የኢትዮጵያ አየር መንገድ አውሮፕላን ላይ የደረሰውን አደጋ ተከትሎ በዓለም ዙሪያ ያሉ አየር መንገዶች ያሏቸውን ቦይንግ ማክስ ኤይት አውሮፕላኖችን ከበረራ ውጪ አድርገዋል።