የቀብር ሥነ ሥርዓት በባዶ ሳጥኖች ተከናወነ

ሃዘንተኞች Image copyright Getty Images

ተጎጂዎችን ለማስታወስ የተወሰነ አፈር አውሮፕላኑ ከወደቀበት ቦታ አፍሰው እንዲወስዱ የኢትዮጵያ መንግሥት ፍቃድ ሰጥቷል።

በኢትዮጵያ አየር መንገድ አውሮፕላን ላይ በደረሰ አደጋ ሕይወታቸውን ያጡ ሰዎች የቀብር ሥነ ሥርዓት በአዲሰ አበባ ቅድስት ሥላሴ ካቴድራል ውስጥ ትናንት ተከናውኗል።

በኢትዮጵያ ሰንደቅ ዓላማ ተሸፍነው ወደ መቃብር ሥፍራው ያመሩት የአስከሬን ሳጥኖች ሙሉ በሙሉ ባዶ የሚባሉ ነበሩ።

የሟቾችን ሙሉ አሰከሬን ማግኘት ባለመቻሉ የቀብር ሥነ ሥርዓቱ በባዶ ሳጥን ሊከናውን ግድ ብሏል። በሥነ ሥርዓቱ ላይ የሟች ቤተሰቦች ራሳቸውን ከሬሳ ሳጥኑ ላይ እስከመጣልና መሬት ላይ እስከመጋጨት የደረሰ ጥልቅ ሐዘናቸውን ሲገልጹ ተስተውለዋል።

"የሞተው የኔ ያሬድ ነው ብዬ አላሰብኩም" የካፕቴን ያሬድ የ11 አመት ጓደኛ

በተመሳሳይ የጸሎትና ሟቾችን የማሰብ ሥነ ሥርዓት በኬኒያዋ መዲና ናይሮቢ በሚገኘው የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተክርስቲያን ውስጥም ተከናውኗል።

ዲፕሎማቶችና ቤተሰቦቻቸውን ያጡ ከ30 በላይ ሀገራት ዜጎች በተገኙበት በቤተክርስቲያኑ ጸሎተ ፍትሐትና የሻማ ማብራት ሥነ ሥርዓት ተካሂዷል።

በአደጋው ሥፍራ የተገኙ የሟቾች የሰውነት ክፍል ላይ ምርመራ አድርጎ ማንነታቸውን ለማወቅ ቢያንስ ስድስት ወር እንደሚያስፈልግ ለቤተሰቦቻቸው ተገልጿል።

Image copyright Reuters

በመሆኑም ተጎጂዎችን ለማስታወስ የተወሰነ አፈር አውሮፕላኑ ከወደቀበት ስፍራ ኢንዲወስዱ የኢትዮጵያ መንግሥት ፍቃድ ሰጥቷል። ይሁንና የተጎጅ ቤተሰቦች ለቢቢሲው ሪፖርተር ፈርዲናንድ ኦሞንዲ እንደተናገሩት "አፈር ዘግኖ መውሰድ ሳይሆን የሐዘናችንን ክብደት ለመቀነስ ቢያንስ አንድ የሰውነት ክፍል አግኝተን አልቅሰን ብንቀብር ትልቅ እፎይታ ይሰማናል" ብለዋል።

የኬንያ የትራንስፖርት ሚኒስትር ጄምስ ማቻሪያ "ሁሉንም ነገር ለማድረግ ይሠራል፤ ለጊዜው ግን የሚቻለውን ማድረግ ይቀድማል" ብለዋል።

"አደጋውን ስሰማ በረራው ጠዋት እንዳልሆነ ራሴን አሳመንኩኝ" የረዳት አብራሪው ጓደኛ

በሌላ በኩል የኢትዮጵያ አየር መንገድ ሠራተኞችም በአደጋው ያጧቸውን 8 ባልደረቦቻቸውን ለማሰብ በቦሌ ዓለም አቀፍ አውሮፕላን ማረፊያ የሐዘን መገለጫ የሆነውን ነጭ አበባ አስቀምጠዋል።

በዚሁ ዝግጅትም የሃይማኖት አባቶች ተገኝተው የሟቾችን ወዳጅ ቤተሰቦችን የማጽናናትና ሃይማኖታዊ አስተምህሮ አከናውነዋል።