ስለምንጓዝበት የአውሮፕላን አይነት እንዴት ማወቅ እንችላለን?

አውሮፕላን Image copyright Getty Images

ባለፈው ዕሁድ ጉዞውን በጀመረ በጥቂት ደቂቃዎች ውስጥ ተከስክሶ ከ150 በላይ ሰዎችን ህይወት የቀጠፈው የኢትዮጵያ አየር መንገድ ንብርት የሆነው አውሮፕላን አደጋ መንስዔው እየተጣራ ቢሆንም በበርካታ ሃገራት ከአገልግሎት ውጪ እንዲሆን ተደርጓል።

በጥቅምት ወር የቦይንግ ሥሪት የሆነ አንድ አይነት ስያሜ ያለው ሌላ አውሮፕላን በተመሳሳይ ሁኔታ ተከስክሶ በርካቶችን ለህልፈት መዳረጉ ሲታወስ የአውሮፕላኑን አስተማማኝነት ጥያቄ ውስጥ ጥሎታል።

ስለ አደጋው እስካሁን የምናውቀው

የኢትዮጵያ አየር መንገድ ቦይንግ 737 ማክስ ኤይት የሚባለው ዘመናዊ አውሮፕላን ካላቸው የዘርፉ ቀዳሚ ተቋማት መካከል አንዱ ሲሆን ከአደጋው በኋላ ይህ አውሮፕላን ከአገልግሎት ውጪ ሆኖ እንዲቆይ ከወሰኑት መካከልም ቀዳሚው ነው።

የኢትዮጵያ አየር መንገድን ውሳኔ በመከተልም የቦይንግ አውሮፕላኖች አምራች የሆነችው አሜሪካንን ጨምሮ ከ50 በላይ ሃገራት ቦይንግ 737 ማክስ ኤይት አውሮፕላን ከበረራ ውጪ እንዲሆን ወስነዋል።

ይህም ከአውሮፕላኑ አደጋ ጋር በተያያዘ የሚደረገው ምርመራ እስኪጠናቀቅና ለሁለቱ አደጋዎች ምክንያት ናቸው የተባሉ ነገሮች ተለይተው በአስተማማኝ ሁኔታ መፍትሄ እስኪሰጣቸው ድረስ እንደሆነ የአየር ትራንስፖርት ባለሙያዎች ይናገራሉ።

ኢትዮጵያ አየር መንገድ ዛሬም ስኬታማ ነው

የተለያዩ ሃገራትና የበረራ አገልግሎት የሚሰጡ ድርጅቶች ግን አሁንም ይህንን ቦይንግ 737 ማክስ ኤይት አውሮፕላንን እየተጠቀሙበት ይገኛሉ።

በዚህ ወቅትም የቦይንግ 737 ማክስ ኤይት የበረራ ደህንነት ሁኔታ አስተማማኝ ስላልሆነ በርካታ የአየር ትራንስፖርት አገልግሎት ተጠቃሚዎች በዚህ አውሮፕላን ከመጓዝ ተቆጥበዋል።

እኛስ ቦይንግ 737 ማክስ ኤይትን ብቻ ሳይሆን በምን አይነት አውሮፕላኖች እንደምንጓዝ ለማወቅ ብንፈልግ ከመሳፈራችን በፊት እንዴት መለየት እንችላለን?

ማድረግ ያለብን

የምንጓዝበት የአውሮፕላን አይነትን ትኬት ስንቆርጥ ወይም ወንበር ስንመርጥ በቀላሉ ማወቅ እንችላለን። ካልሆነም የበረራ ቁጥሩን ኢንተርኔት ላይ በማስገባትም መለየት ይቻላል።

በተጨማሪም የአውሮፕላኑን አይነት ለማወቅ የሚረዱ (FlightStats.com, SeatGuru.com, Expertflyer.com, FlightAware, Flightview.com) የመሳሰሉ የተለያዩ ድረ-ገፆችን በመጠቀም መለየት ይቻላል።

እነዚህን መንገዶች ተጠቅመን ስለምንጓዝበት አውሮፕላን የምንፈልገውን መረጃ ማግኘት ካልቻልን፤ ወደ አገልግሎት ሰጪው አየር መንገድ በመደወል የምንፈልገውን መረጃ መጠየቅ እንችላለን።

ለ60 ዓመታት የዘለቀው የኢትዮጵያ አየር መንገድና የቦይንግ ግንኙነት

ነገር ግን በመጀመሪያ ላይ ስለምንጓዝበት አውሮፕላን የምናገኘው መረጃ በመጨረሻ ደቂቃ ላይ በቴክኒክ ምክንያት ሊቀየር እንደሚችልም መዘንጋት የለብንም።

ምናልባት የሚጓዙበት አየር መንገድ ቦይንግ 737 ማክስ ኤይት አውሮፕላንን በአሁኑ ወቅት እየተጠቀመ ከሆነና በዚሁ አውሮፕላን የመጓዝ ተራው የእርስዎ ቢሆን ምን ያደርጋሉ? የጉዞ ዕቅድዎን ይሰርዛሉ ወይስ ትኬትዎን ይቀይራሉ?

የአየር ጉዞ አማካሪ የሆነው ሄንሪክ ዚልመር እንደሚለው "ተጓዦች ጉዟቸውን መሰረዝ ይችላሉ፤ ነገር ግን ውሳኔው ከእራሳቸው በኩል የሚመጣ በመሆኑ ገንዘባቸው እንዲመለስ መጠየቅ አይችሉም" ይላል።

"የሞተው የኔ ያሬድ ነው ብዬ አላሰብኩም" የካፕቴን ያሬድ የ11 አመት ጓደኛ

ስለዚህ በአሁኑ ወቅት ያለው ዋነኛው አማራጭ ለደህንነት አስጊ የሆኑ አውሮፕላኖችን ከአገልግሎት ውጪ ያደረጉትን አየር መንገዶችን መጠቀም እንደሆነ የአየር ትራንስፖርት ባለሙያዎች ይመክራሉ።