አምስት ነጥቦች ስለጌዲዮ ተፈናቃዮች

የጌድዮ ተፈናቃዮች Image copyright MAHEDER HAILESELASSIE TADESE

ጉጂ ኦሮሞዎች እና የጌድዮ ማህበረሰብ ለዘመናት በጉርብትና አብረው ኖረዋል። እነዚህ ሁለት ማህበረሰቦች በንጉሡ ጊዜ በሲዳሞ ጠቅላይ ግዛት ስር በአንድ ላይ ይተዳደሩም ነበር። በደርግ ዘመንም እንዲሁ በሲዳሞ ክፍለ ሃገር ስር መተዳደራቸውን ቀጥለው ነበር።

ሁለቱ ማህበረሰቦች፤ አሁን ወደሚገኙባቸው ክልሎች የተካለሉት ኢህአዴግ ወደ ስልጣን ሲመጣ ባዋቀረው የፌደራል አከላለል መሰረት ነው።

በዚህም ጉጂዎች በኦሮሚያ ክልል፤ ጌዲዮዎች ደግሞ በደቡብ ክልል ውስጥ ተካተው የየራሳቸው ዞኖች እንዲኖራቸው ተደርጓል።

ደቡብ ክልል አዲስ ለተፈናቀሉ 54 ሺህ ጌድዮዎች የፌደራል መንግሥትን ድጋፍ ጠየቀ

በጉጂዎችና በጌዲዮዎች መካከል ቀደም ባሉት ጊዚያትም ቢሆን ማህበረሰባዊ ግጭቶች እንደነበሩ ይገለጻል። ነገር ግን በየትኞቹም አጎራባች ማህበረሰቦች መካከል እንደሚያጋጥመው፤ ከተፈጥሮ ሃብት ጋር የተያያዙ ግጭቶች እንደነበሩ አጥኚዎች ጽፈዋል።

የመፈናቀ መንስዔ ምንድን ነው?

ለአሁኑ ሰብአዊ ቀውስ ምክንያት የሆነው መፈናቀል የጀመረው፤ ባለፈው ዓመት በጉጂ እና በጌዲዮ ተወላጆች መካከል ግጭት መቀስቀሱን ተከትሎ ነው።

ባለፈው ዓመት ሚያዝያ ወር ላይ፤ በሁለቱም ማህበረሰቦች መካከል በተነሳ ግጭት ሰዎች መሞታቸው፣ ቤቶች መቃጠላቸው እና በአስር ሺዎች የሚቆጠሩ ሰዎች ቀዬያቸውን ጥለው መሰደዳቸው ተዘግቦ ነበር።

ለተወሰኑ ሳምንታት ግጭቱ ጋብ ብሎ ቢቆይም እንደገና በግንቦት ወር ያገረሸው ግጭት ችግሩን አባባሰው። ብዙዎች መሞታቸው፣ መኖርያ ቤቶችና የንግድ ተቋማት እንዲሁም ተሽከርካሪዎች መቃጠላቸው በዜና ተነግሯል።

በጉጂ እና ጌዲዮ ግጭት ከ200 ሺህ በላይ ሰዎች ተፈናቀሉ

ይህን ተከትሎም ሰዎች ቤት ንብረታቸውን ጥለው ተሰደዱ። ብዙ የጌዲዮ ተወላጆችም ከምዕራብ ጉጂ ዞን ተፈናቅለው ጌዲዮ ዞን ወደሚገኙ አካባቢዎች ገብተው መጠለል ጀመሩ።

ከጉጂዎች በኩልም የተፈናቀሉ እንዳሉም ይነገራል።

ተፈናቃዮቹ ምን ያል ናቸው?

ዓለም አቀፉ የስደተኞች ድርጅት (አይኦኤም) ከግጭቱ በኋላ ባወጣው መግለጫ፤ በምዕራብ ጉጂና በጌዲዮ አዋሳኝ አካባቢዎች በተቀሰቀሰው ግጭት 970 ሺህ የሚደርሱ ሰዎች መፈናቀላቸውን ገልጾ ነበር።

በተባበሩት መንግሥታት ድርጅት የሰብዓዊ ጉዳዮች ማስተባበሪያ ጽ/ቤት በበኩሉ፤ በግጭቱ ምክንያት የተፈናቀሉት ሰዎች ቁጥር 818 ሺህ እንደሆነ ይጠቅሳል።

ከእነዚህም መካከል 642,152 ተፈናቃዮች በጌዲኦ ዞን የሚገኙ መሆናቸውን፤ 176,098 ያክሉ ደግሞ በምዕራብ ጉጂ ዞን እንደሚገኙ ተገልጾ ነበር።

በተፈናቃዮች ብዛት ኢትዮጵያ ከዓለም ቀዳሚ ሆነች

የኢትዮጵያ መንግሥት የብሔራዊ የአደጋ ስጋት ሥራ አመራር ኮሚሽን ባለፈው ሳምንት ለቢቢሲ እንደገለጸው 800 ሺህ ከሚበልጡት ተፈናቃዮች መካከል አብዛኞቹ ወደ መጡበት ሲመለሱ 208 ሺዎቹ በመጠለያ ካምፕ ውስጥ ቀርተዋል።

ሰብአዊ ቀውሱ አስከፊነ ምን ይመስላል?

ለእነዚህ ተፈናቃዮች ተገቢው የሰብአዊ እርዳታ ምላሽ እየተሰጣቸው አይደለም የሚለው እሮሮ የጀመረው ገና ከመነሻው ነበረ። ባለፈው ሃምሌ ወር ዓለም አቀፉ ማኅበረሰብ ይህን ቀውስ ጆሮ ዳባ ልበስ ብሎታል ሲል የዓለም አቀፉ ቀይ መስቀል ማኀበር ወቀሶ ነበር።

ተፈናቃዮቹ ያሉበት ሁኔታ ሰብአዊ ክብራቸውን ለማስጠበቅ እንኳ የሚመች እንዳልሆነና በትምህርት ቤቶች፣ በቢሮዎች፣ በአብያተ-ክርስቲያናት ወለሎች ላይ እየተኙ ነው፤ የሚለብሱት ነገር እንኳን የላቸውም ብለው ነበር።

"የጌዲዮና ጉጂ ተፈናቃዮች ቸል ተብለዋል" የዓለም ቀይ መስቀል ማኀበር

ተፈናቃዮቹ ምግብና ንጹሕ ውሃ ማግኘት እንዳልቻሉም ተገልጾ ነበር።

ሰሞኑን ደግሞ፤ ሰብኣዊ ቀውሱ ተባብሶ ተፈናቃዮቹ ተርበው ለሞትና ለበሽታ መዳረጋቸውን በመገናኛ ብዙሃን እና በማህበራዊ መገናኛዎች ጭምር ሲገለጽ ሰንብቷል።

የጀርመን ድምጽ ራዲዮ በጌዲዮ ዞን ተጠልለው ከሚገኙት ተፈናቃዮች መካከል በየቀኑ ከ 3 እስከ አራት ሰው እንደሚሞት ከአካባቢው አንድን የሃይማኖት መሪ በመጥቀስ የዘገበ ሲሆን፤ ዘ ጋርድያን በበኩሉ መንግሥት ተፈናቃዮቹ ወደ መኖርያቸው ወደ ምዕራብ ጉጂ እንዲመለሱ ሲል ሰብአዊ ድጋፍ እስከማቋረጥ መድረሱን አስነብቧል።

ይህም ለሰብአዊ ቀውሱ መባባስ ምክንያት እንደሆነ ተፈናቃዮቹን እርዳታ ባለማግኘታቸው ለረሃብ መጋለጣቸው ሲገለጽ ሰንብቷል። እነዚህን አስተያየቶች ተከትሎም፤ የሰላም ሚኒስትርዋ ወይዘሮ ሙፈሪያት ካሚል "ለተፈናቃዮቹ ምንም አይነት ሰብአዊ እርዳታ እንዳልደረሳቸው የሚሰጠው አስተያየት ስህተት" ነው የሚል መግለጫ ሰጥተዋል።

ቢሆንም፤ ሰብአዊ ቀውሱን መንግሥት ችላ ብሎታል የሚለው ወቀሳ በርትቶ፤ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐብይ አህመድም ተፈናቃዮቹን እንዲጎበኙ ግድ ብሏቸዋል።

ተፈናቃዮቹ ለምን ወደቀያቸው መመለስ አልፈለጉም?

አይኦኤም ህዳር ወር ላይ ያወጣው ሪፖርት እንዳመለከተው ተፈናቃዮቹ ወደቀያቸው ላለመመለሳቸው በተደጋጋሚ የሚቀርበው ምክንያት ቤታቸው መውደሙን ነው። ቤቶች በእሳት ቃጠሎ ወድመዋል።

የብሔር ግጭት የሚንጣት ሀገር

ሌላኛው ምክንያት ደግሞ የደህንነት ስጋት ነው። በርካቶች ወደቀያቸው የሚመለሱ ከሆነ ለህይወታቸው እንደሚያሰጉ ተናግረዋል።

ለምን መንግሥት ትችት ይቀርብበታል?

ዘጋርዲያን በጌዲዮ ውስጥ ያለውን ቀውስ ሲገልጸው "በጠቅላይ ሚኒስትር ዐብይ አስተዳደር ላይ ጥቁር ነጥብ ነው" ሲል አስፍሯል።

በርካቶችም መንግሥት ለችግሩ ምላሽ ለመስጠት በጣም ዘግይቷል ሲሉ ይተቻሉ። አንዳንዶች ጠቅላይ ሚኒስትሩ ወደ ጌዲዮ በመጓዝ ጉብኝት ያደረጉት ጉዳዩ በማህበራዊ ሚዲያዎች ላይ ዋነኛ ርዕስ ከሆነ በኋላ ነው ይላሉ።

በተጨማሪም የሰብአዊ እርዳታ እንዲቋረጥ የተደረገው ተፈናቃዮቹ ወደ መጡበት እንዲመለሱ ጫና ለመፍጠር ነው ሲል ዘ ጋርዲያን ጠቁሟል።

የሰላም ሚኒስትሯ ወ/ሮ ሙፈሪያት ካሚል ለዚህ ክስ በሰጡት ምላሽ ላይ "ይህ የመገናኛ ብዙሃን ፕሮፓጋንዳ ነው። ሰብአዊነትና ፖለቲካ ሁለት የተለያዩ ነገሮች ናቸው" ብለዋል።

አክለውም ሃገሪቱን ለማናጋት የሚፈልጉ ኃይሎች ይህንን አጋጣሚ እየተጠቀሙበት እንደሆነም ገልጸዋል።