"በመጨረሻ ላይ ሳትስመኝ መሄዷ ይቆጨኛል" እናት

አያንቱ ግርማይ Image copyright Social media

ኢትዮጵያ አየር መንገድ አውሮፕላን ተከስክሶ 157 ሰዎች ህይወት አልፈወል። የሟች ቤተሰቦችና ዘመዶች የአደጋው ሰለባ የሆኑ ቤተሰቦቻቸውን አስከሬን አግኝተው መቅበር ስላልቻሉ፤ ባለፈው እሁድ በቅድስት ሥላሴ ካቴድራል በአንድ ላይ የስንብት ሥነ ሥርዓት ተደርጎላቸዋል።

በሥነ ሥርዓቱም ላይ ተምሳሌታዊ የሬሳ ሳጥን ተዘጋጅቶ ወዳጅ ዘመዶች እርማቸውን እንዲያወጡ ተደርጓል። አስከሬን አግኝተው የሚወዷቸውን ልጆቻቸውንና ዘመዶቻቸውን መቅበር አለመቻል ሃዘናቸውን ከባድ ካደርገባቸው ወላጆች መካከል አንዲት እናትን አናግረናል።

"እስካሁን ሙሉ የሰውነት ክፍል ማግኘት እንደተቸገርን ለቤተሰብ እያስረዳን ነው" አቶ ተወልደ ገ/ማርያም

"እናቱ ስታየኝ 'ልጄ ያሬድ ይመጣል' እያለች ታለቅስ ነበር"- በናይሮቢ የካፒቴኑ ጸጉር አስተካካይ

ልጃቸውን በአውሮፕላን አደጋው ያጡት የበረራ አስተናጋጇ አያንቱ ግርማይ እናት የሆኑትን ወ/ሮ ክበቧ ለገሰን "አንዴ ልጃችን አምልጣናለች። እንደኛ ሌሎች ሰዎችም ቤተሰቦቻቸውን አጥተዋል። በአንድ ቦታም ስለሞቱ የቀብራቸው ሥነ ሥርዓትም በአንድ ቦታ እና በአንድነት እንዲሆን እፈልጋለሁ። እኔ ለይቼ መውሰድ አልፈልግም" ሲሉ በሃዘን በተሰበረ ድምጽ ተናግረዋል።

አውሮፕላኑ ወደ ተከሰከሰበት ቦታ ከአንዴም ሁለት ጊዜ ሄደው መመልከታቸውን የሚናገሩት ወ/ሮ ክበቧ፤ "አገኛለሁ ብዬ ተስፋ የማደርገው ነገር የለም" ይላሉ።

"እንደ ሃገራችን ባህል አንድ ሰው ሲሞት ሬሳ ታይቶ ቤተ ክርስቲያን ተወስዶ ይቀበርና ራስን ማሳመን ይቻል ነበር" ይህ ግን መሆን እንዳልቻለ ገልጸው፤ ምንም እንኳን ሥነ ሥርዓቱ የተከናወነው በባዶ ሳጥን መሆኑን አእምሯቸው ቢያውቅም "እንግዲህ እኛ ከዚህ በኋላ የሚመለስ እንደሌለ አምነን እራሳችንን አሳምነን ቤታችን ተመልሰናል።"

የካፕቴን ያሬድ ሃይማኖታዊ የሐዘን ሥርዓት ያለ አስከሬን ተፈፀመ

"አደጋውን ስሰማ በረራው ጠዋት እንዳልሆነ ራሴን አሳመንኩኝ" የረዳት አብራሪው ጓደኛ

ሞት የማይቀር እንደሆነና ሁሉም ወደዛው እንደሚሄድ እራሳቸውን ከማሳመን ውጪ ምንም ማድረግ እንደማይችሉ የሚናገሩት ወ/ሮ ክበቧ "ከዚህ በኋላ ያልሰማ ሰው መጥቶ ካላለቀሰ በስተቀር እኛ ግን አልቅሰን ወጥቶልናል" ይላሉ።

እንደወጣች የቀረችውን ልጃቸውን ሲያስታውሱ "አያንቱ ለወደፊት ህይወቷ ብዙ ራዕይ ነበራት። ከዚህ ግን ዋናው ለቤተሰቦቿ እንዲያልፍላቸው ብላ ማሰብ እና መስራት ነበር" በማለት የእሷ ህልፈት የቤተሰቡንም ተስፋ የቀጨ እንደሆነ ይናገራሉ።

ወ/ሮ ክበቧ ከአያንቱ ጋር የነበራቸውን የመጨረሻ ቆይታ ሲያስታውሱ ጠዋት ቁርስ ሰርተው ካበሏት በኋላ ሻንጣዋን መኪና ላይ ጭነውላት አይን ለአይን እንደተያዩ ያስታውሳሉ።

"ሆኖም ግን የዚያን ዕለት ትንሽ ስለረፈደባት ሌላ ጊዜ ስማኝ የምትሄደው ሳትስመኝ ሄደች። ይህ መቼም ቢሆን ከአዕምሮዬ የሚጠፋ አይደለም" ሲሉ በመጨረሻዋ ቅጽበት ያመለጣቸውን የልጃቸውን ስንብት በቁጭት ያስታውሳሉ።