'መጥፎ ዕድል' አውሮፕላኑ የወደቀበት ስፍራ ስያሜ እንደሆነ ያውቃሉ?

አቶ ባትሪ ለማ እና አቶ ደቻሳ ጉተማ
አጭር የምስል መግለጫ አቶ ባትሪ ለማ እና አቶ ደቻሳ ጉተማ

በመጥፎ አጋጣሚ መጋቢት 1 ቀን 2011 ዓ.ም ዕለተ እሁድ በኢትዮጵያ አየር መንገድ አውሮፕላን የበረራ ቁጥር ኢቲ 302 የተሳፈሩ 157 ተጓዦች አውሮፕላኑ ጊምቢቹ ወረዳ ቱሉ ፈራ ተብሎ በሚታወቅ አካባቢ ተከስክሶ አንዳቸውም አለመትረፋቸው ዓለምን አስደንግጧል።

አደጋው የደረሰበት አካባቢ ነዋሪዎች ለማያውቋቸው የአደጋው ሰለባዎች ልባቸው በሀዘን ተሰብሮ ከመጣው ጋር ሲያለቅሱና ሃዘናቸውን ሲገልጹ የሰውነት ሩህሩህነታቸውን ለዓለም አሳይተው ርዕስ ሆነው ሰንብተዋል።

ስለ አደጋው እስካሁን የምናውቀው

ከሁሉ ከሁሉ ይህን የአውሮፕላን አደጋ መጥፎ ዕጣ የደረሰበት ቦታ ስያሜ የነገሮችን ግጥምጥሞሽ አነጋጋሪ ያደርገዋል። 'ቱሉ ፈራ' የሚለው የኦሮሚኛ ስያሜ 'መጥፎ ዕድል' እንደማለት እንደሆነ የይነገራል።

በእርግጥም የዚህ ተራራ ስያሜ ከመጥፎው አጋጣሚ ጋር የሚመሳሰል መሆን አለመሆኑንና እንዴትስ ስያሜውን እንዳገኘ ለማወቅ ቢቢሲ የአካባቢውን አዛውንቶች አነጋግሯል።

አቶ ባትሪ ለማ በአካባቢው ከሚኖሩ አዛውንት አንዱ ናቸው። "ቱሉ ፈራ ይህን ስም ያገኘው በአካባቢው ባለው የአየር ሁኔታ ነው" ይላሉ።

ቦታው ከፍታማ ስለሆነ የንፋሱ አቅጣጫ ወዴት እንደሚነፍስ ለማወቅ ያስቸግራል የሚሉት አቶ ባትሪ "በስፍራው ያለው ቅዝቃዜው ኃይለኛ ከመሆኑ የተነሳ ሰዎች በተራራው ላይ መኖር ሲያቅታቸው ቱሉ ፈራ ብለው ሰየሙት። በአማርኛ የመጥፎ እድል ማለት ነው" በማለት ነው ይላሉ።

ሁለቱን የአውሮፕላን አደጋዎች የሚያመሳስላቸው ነገር አለ

እንደ አቶ ባትሪ አገላለፅ የአካባቢው ቦታዎች በሙሉ የተሰየሙት ባለው የአየር ሁሌታ ላይ ተመስርተው ነው። ለምሳሌ አውሮፕላን የወደቀበት ቦታ ሃማ ይባላል። ይህ ማለት ክፉ ወይም መጥፎ ማለት ነው።

በአካባቢው የሚገኝ ተራራ ደግሞ ፈራ ተራራ ይባላል። አውሮፕላኑ ከወደቀበት ቦታ ቀጥሎ ያለው ደግሞ ነኑ እኩቢ ሲባል የበሽታ አካባቢ ማለት እንደሆነ አቶ ባትሪ ያስረዳሉ።

በኦሮሚኛ ቱሉ ፈራ የሚሉት ቃላት በቀጥታ ሲተረጎሙ "መጥፎ ዕድል" የሚል ትርጉምን ይይዛሉ። በእርግጥም በአካባቢው ያጋጠመው አደጋ ሰለባዎች መጥፎ እድል ገጥሟቸው ሃዘኑ ከሃገር አልፎ ለዓለም ተርፏል።

አጭር የምስል መግለጫ የቱሉ ፈራ

ይሁን እንጂ ከአካባቢው ስያሜ አመጣጥ ጋር የተለያዩ ትርጉም የሚሰጡ ታሪካዊ ዳራዎችን የሚየጠቅሱ የአካባቢው አዛውንቶች አልጠፉም።

ለዚህም ሌላኛው የጊምቢቹ ወረዳ አዛውንት አቶ ደቻሳ ጉተማ የሃማ ቁንጥሹሌ ቀበሌ ነዋሪ ሲሆኑ፤ የፈራ ተራራ ስያሜ ምንጩ ሌላም ታሪክ እንዳለው ይጠቅሳሉ።

"እስካሁን ሙሉ የሰውነት ክፍል ማግኘት እንደተቸገርን ለቤተሰብ እያስረዳን ነው" አቶ ተወልደ ገ/ማርያም

እሳቸው እንደሚሉት ከሆነ ተራራዎች ስያሜያቸውን ያገኙት በጥንት ዘመን አካባቢውን ሲያስተዳድሩ ከነበሩ ነገሥታት ጋር ተያይዞ እንደሆነ ይናገራሉ።

"የፈራ ተራራ ስያሜውን ያገኘው በአፄ ዘረ ያዕቆብ ዘመን ነው። ለምሳሌ አንዱ የወቅቱ የአካባቢው አስተዳዳሪ የነበሩት መሪ ስም ቦካ ይባል ነበር። እሳቸውም ይኖሩበት የነበረውን ተራራ በስማቸው ጋራ ቦካ በማለት ሰይመውታል" ይላሉ አቶ ደቻሳ።

በተመሳሳይ የፈራ ተራራ ስያሜ ከአህመድ ግራኝ ወረራ ጋር ተያያዥነት አለው ይላሉ። "ከአባቶቻችን እንደሰማነው ግራኝ አህመድ ወታደሮቹን ይዞ አካባቢውን መውረር ሲጀምር ለቦካ መልዕክት ላከ። መልዕክቱ 'ጭካኔን እንደ እናቴ መከታዬን ደግሞ እንደ አባቴ ሆኜ እየመጣሁልህ ነውና ተዘጋጅተህ ጠብቀኝ' የሚል ነበር" ይላሉ።

ኢትዮጵያ አየር መንገድ ዛሬም ስኬታማ ነው

አቶ ደቻሳ እንደሚሉት ቦካ የአህመድ ግራኝን መልዕክት እንደተቀበሉ ለሌላኛው የአካባቢው አስተዳዳሪ ለአቶ ቱሉ እየመጣብን ያለውን ጦርነት አብረን እንመክት ብሎ ጥያቄ አቀረቡ።

መልዕክት አድራሹም ከአቶ ቱሉ ጋር ሲመለስ እንዴት እንደተሰማቸው ቦካ ሲጠይቁት ጦርነቱ እንዳስፈራቸውና እንዳሳሰባቸው ተገንዝቤአለሁ አላቸው ይላሉ አቶ ደቻሳ።

ቦካም ይህንን ሲሰሙ 'አዪ! ቱሉ ፈራ ማለት ነው' በማለት የተራራው ስም ከዚያ በኋላ ቱሉ ፈራ ተብሎ እንደቀረ እንደተነገራቸው ያስረዳሉ።

ሁለቱም አዛውንቶች ለስፍራው ለተሰጠው ለተሰጠው ስያሜ የተለያየ ምክንያት ቢሰጡም የሚስማሙበት አንድ ሃሳብ ግን ቱሉ የሚባል የአካባቢው አስተዳዳሪ በተራራው ላይ ይኖሩ እንደነበር ነው።

አቶ ባትሪ ግን ሆን ተብሎ የተራራው ስያሜ ከአካባቢው የአየር ሁኔታ የመነጨ እንደሆነ አጠንክረው ይከራከራሉ። እንደሳቸው አባባል የአካባቢው አስተዳደር የነበሩት ሁሉ ጦርነት የሚፈሩ አልነበሩም።