አሜሪካ የቦይንግ 737 ማክስ ፈቃድ ላይ ምርመራ ልታደርግ ነው

ቦይንግ 737 ማክስ Image copyright Getty Images

የአሜሪካ መንግሥት ቦይንግ 737 ማክስ አውሮፕላን ለመብረር እንዴት ፈቃድ እንዳገኘ እንዲጣራ ትዕዛዝ አስተላለፈ።

በአምስት ወራት ውስጥ ሁለቴ የተከሰከሰው ይህ አውሮፕላን በሁለቱ አደጋዎቹ ውስጥ "ተመሳሳይነት" አለ ተብሏል።

የትራንስፖርት ሚንስትር ኤሊን ቻኦ የአሜሪካ ምርመራ ክፍል የአውሮፕላኑን የበረራ ፈቃድ እንዲያጣራ ጠይቀዋል።

ሁለቱን የአውሮፕላን አደጋዎች የሚያመሳስላቸው ነገር አለ

ቦይንግ 737-8 ማክስ አውሮፕላኖቹ በሙሉ እስከ ግንቦት እግድ ተጣለባቸው

የአደጋው መርማሪዎች አንዱ ትኩረታቸውን ያደረጉት የአውሮፕላኑን ሞትር በድንገት ከመቆም የሚጠብቀውን ሥርዓት ማጥናት ሲሆን፤ አውሮፕላን አምራቹ ቦይንግ ደግሞ ሶፍትዌሩ መሻሻል አለበት ብሏል።

ቻኦ ለምርመራው ቡድን መሪ ካለቪን ስኮቭል በላኩት መልዕክት ምርመራው "የአሜሪካ ፌደራል የአየር ትራንስፖርት አስተዳደር አውሮፕላኑ የበረራ ደህንነት ማረጋገጫ ምርመራ በትክክል እንደተካሄደበት ለማረጋገጥ እንዲረዳ ነው" ብለዋል።

የጥቅምት ወሩን የላየን ኤር አውሮፕላን አደጋን ተከትሎ ባለፈው ሳምንት የኢትዮጵያ አየር መንገድ አውሮፕላን ከተከሰከሰ በኋላ የአሜሪካ ፌደራል የአየር ትራንስፖርት አስተዳደር ለምን 737 ማክስ አውሮፕላንን ከበረራ ለማገድ ይህን ያህል ዘገየ የሚል ጥያቄ ፈጥሯል።

ሬውተርስ እንደዘገበው የአሜሪካ ፍትህ ቢሮ የፌደራል የአየር ትራንስፖርት አስተዳደሩ የቦይንግ አውሮፕላንን የደህንነት ሁኔታ ለምን ችላ እንዳለ ምርመራ ጀምሯል።

ኢትዮጵያ አየር መንገድ ዛሬም ስኬታማ ነው

በአሁኑ ደረጃ አውሮፓና ካናዳ የአውሮፕላኑን ደህንነት በእራሳቸው ለማረጋገጥ መወሰናቸውን አሳውቀዋል። ይህ ውሳኔም የአውሮፕላኑን ተመልሶ በዓለም አቀፍ ደረጃ የመብረር አቅሙን ጥያቄ ውስጥ ከትቶታል።

አውሮፓውያንና ካናዳውያን መርማሪዎች ብዙ ጊዜ የአሜሪካን ፌደራል የአየር ትራንስፖርት አስተዳደር የምርመራ ውጤትን ይከተሉ ነበር።

የአውሮፓ ሕብረት የአየር ትራንስፖርት ደህንነት ኤጀንሲ (ኢሳ) በሚደረጉት ማንኛውም አይነት የንድፍ ማሻሻያን በጥልቀት ለመከታተል ቃል ገብቷል።

"ሁሉንም ጥያቄዎቻችንን በበቂ ሁኔታ መልስ የሚሰጡ ነገሮችን ካላገኘን አውሮፕላኑ ተመልሶ እንዲበር ፈቃድ አንሰጥም" የኢሳ ኃላፊ ፓትሪክ ኪ ለአውሮፓ ሕብረት የተናገሩት ማረጋገጫ ነው።

ከአሜሪካ ቀድማ አውሮፕላኑን ከበረራ ያገደችው ካናዳ፤ የአሜሪካን ፌደራል የአየር ትራንስፖርት አስተዳደር ማረጋገጫን ከመቀበል ይልቅ ወደፊት በእራሷ መርምራ 737 ማክስ አውሮፕላንን የበረራ ፈቃድ እንደምትሰጥ አሳውቃለች።

የአሜሪካ ፌደራል የአየር ትራንስፖርት አስተዳደር በካናዳና አውሮፓ ሕብረት ውሳኔ ላይ አስተያየት ከመስጠት ቢቆጠብም በሰጠው መግለጫ "አሁን በአሜሪካና በዓለም ላይ የሚታየው የበረራ ደህንነት እዚህ ስኬት ላይ የደረሰው በእኛ ጠንካራ ሥራና ከሌሎች የዓለም አየር መንገዶች ጋር በምናደርገው ትብብር ነው" ብለዋል።

አቶ ተወልደ አየር መንገዶች ሁሉ ለጊዜው ቦይንግ 737-8 ማክስን እንዳይጠቀሙ ጠየቁ

ባለፉት ሁለት አደጋዋች በአጠቃላይ 356 ሰዎች ሞተዋል። እስካሁን ሁለቱ አደጋዎች የተያያዙ መሆናቸውን የሚያረጋግጥ ማስረጃ ባይገኝም የኢትዮጵያን አውሮፕላን ጥቁር ሳጥን እየመረመሩ ያሉ የፈረንሳይ ባለሙያዎች እስካሁን ባላቸው ግኝት በሁለቱ አደጋዎች መካከል "ተመሳሳይነት" አለ ብለዋል።

ባለሙያዎች እንደሚሉት በቦይንግ አውሮፕላን ላይ አውሮፕላኑ ቁልቁል በአፍንጫው እንዳይከሰከስ ለማድረግ የተገጠመው አዲስ ቴክኖሎጂ ሁለቱም አደጋዎች ላይ ተፅዕኖ ሳይኖረው አይቀርም ይላሉ።

ቦይንግ ከኢንስፔክተር ጀነራሉ ጋር የቦይንግ 737 ማክስ አውሮፕላንን የበረራ ማረጋገጫ ለመፈተሽ እንደሚተባበር ተናግሯል።