በአውሮፕላኑ የአደጋ ስፍራ በየዕለቱ እየተገኙ የሚያለቅሱት እናት

ወይዘሮ ሙሉነሽ Image copyright Getty Images

በኢትዮጵያ አየር መንገድ አውሮፕላን ጋር በተያያዘ በስፋት ከተሰራጩትና ለአደጋው ሰለባዎች መሪር ሃዘናቸውን ከሚገልፁ ፎቶግራፎች መካከል የአዛውንቷ የወይዘሮ ሙሉነሽ በጂጋ ፎቶ አንዱ ነው።

ከዚህ አንፃር የወይዘሮ ሙሉነሽ ታሪክ የተለየ የሚሆነው ደግሞ በአደጋው የሞተ ዘመድም ሆነ በቅርብ የሚያውቁት ሰው ሳይኖር በሰውነታቸው ብቻ ስለደረሰው አደጋ አዘውትረው ማዘናቸው ነው።

'መጥፎ ዕድል' አውሮፕላኑ የወደቀበት ስፍራ ስያሜ እንደሆነ ያውቃሉ?

አዛውንቷ ወይዘሮ ሙሉነሽ ነዋሪነታቸው በመጥፎ ዕጣ የ157 ሰዎችን ሕይወት የቀጠፈው አውሮፕላን በተከሰከሰበት ስፍራ ሲሆን፤ በተመለከቱት አሰቃቂ ክስተት ሳቢያ ከዚያች ዕለት በኋላ እጅጉን አዝነው እንቅልፍ አጥተዋል። እንባቸውንም በአደጋው ለተቀጠፉት ለማያውቋቸው ሰዎች እያፈሰሱ ቀናት ተቆጥረዋል።

የቱሉ ፈራ ቀበሌ ነዋሪ የሆኑት እኚህ እናት፤ ቤታቸውም አደጋው ከደረሰበት ሁለት ኪሎ ሜትር ያክል ርቀት ቢኖረውም ከአደጋው ቀን አንስቶ አንድም ቀን ከቦታው ርቀው አያውቁም። "እስካሁን ደጋግሜ ከአደጋው ቦታ ሄጄ ባለቅስም ሃዘኔ አልወጣልኝም" ይላሉ።

"በመጨረሻ ላይ ሳትስመኝ መሄዷ ይቆጨኛል" እናት

አሁንም በየቀኑ ወደ ስፍራው ከሚመጡ የአደጋው ሰለባ ቤተሰቦች ጋር በመሆን ሃዘናቸውን ይገልፃሉ። "የሃገሪቷ ሁኔታ ነው የተበላሸው፤ ሰዎች ባህላቸውንና ወጋቸውን በመርሳታቸው የዚህ ሁሉ ሰው ደም ፈሰሰ" በማለት ጉዳዩን ከፈጣሪ ቁጣ ጋር ያያይዙታል።

"ከዚህ በፊት በአያት ቅድመ አያቶቻችን ዘመን አይተንም ሰምተንም የማናቀውን ነገር በእኛ ቀዬ ሲፈጠር በጣም አስደነገጠኝ፤ ይህም ነው ቀን ከሌሊት እንዳለቅስ ያደረገኝ" ይላሉ ወይዘሮ ሙሉነሽ።

Image copyright Getty Images

እኚህ እናት እንዲህ በሃዘን የሚንገበገቡት ለኢትዮጵያዊያኑ ብቻ ሳይሆን በአውሮፕላኑ ውስጥ ለነበሩት የሰው ልጆች ነው። "የሰው ልጅ ኢትዮጵያ ሃገራችን መጥቶ ተቃጠለ። ደማቸው ባዶ ሜዳ ላይ መፍሰሱን ሳስብ ሆዴ ይረበሻል። በዕለቱ ስለተከሰከሰው የሰው አጥንትና ስለፈሰሰው ደም አልቅሼ ሊወጣልኝ አልቻለም" ሲሉ የሃዘናቸውን ጥልቀት ይናገራሉ።

አደጋው በአውሮፕላን አብራሪዎች ላይ ምን ስሜት ፈጠረ?

አደጋው ከደረሰ በኋላ በስፍራው ስለተመለከቱት ነገርም ሲያስታውሱ፤ የአውሮፕላኑ አካል የተበተነ ወረቀት እንጂ የሰው ልጅ በውስጡ የያዘ አይመስልም ነበር። "ታዲያ ይሄ እንዴት ለእኔ እረፍት ይሰጠኛል? የእነርሱ ደም ነው የሚያቃጥለኝ" ይላሉ ወይዘሮ ሙሉነሽ።

በተለይ ደግሞ አደጋ በልጆቻቸው ላይ ደርሶ ቢሆን ኖሮስ ብለው ሲያስቡ ሃዘናቸው የሚብሰው ወ/ሮ ሙሉነሽ "እኛም ልጆች አሉን፤ ልጆቻችንም በአየር ይበራሉ። ታዲያ ከእነዚህ መካከል የእኛ ልጆች ቢኖሩስ ብዬ አስባለሁ።"

ወይዘሮ ሙሉነሽ በየዕለቱ አደጋው የደረሰበት ቦታ ይሄዳሉ። "አንድም ቀን ቀርቼ አላውቅም።" በየአጋጣሚውም እርሙን ለማውጣት ከሚመጣው ሰው ሁሉ ጋር ስለሞቱት ሰዎች ያለቅሳሉ። "ቤትም ስገባ ያ የፈሰሰው የሰው ደም ነው ትዝ የሚለኝ፤ ምግብም አስጠልቶኝ ቡናው እራሱ ቡና አይመስለኝም" ይላሉ።

ስለምንጓዝበት የአውሮፕላን አይነት እንዴት ማወቅ እንችላለን?

ይህ አደጋ በወይዘሮ ሙሉነሽ ላይ የተለየ ጥልቅ ሀዘንን ፈጥሮባቸዋል። ከዚህ በፊት በቅርብ የሚያውቋቸውና ከቤተሰባቸው አባላት መካከልም የተለያዩ ሰዎች በሞት ተለይተዋቸዋል። ነገር ግን ይህን ያህል ሃዘን ውስጥ ገብተው እንደማያውቁ የሚናገሩት ወይዘሮ ሙሉነሽ ይህ ክስተት ለእርሳቸው የተለየ ነው።

ወይዘሮ ሙሉነሽ ይህንን ሃዘናቸውን ልክ እንደ ቤተሰብ ለመግለፅ ባላቸው አቅም በአደጋው ሕይወታቸውን ላጡት ሰዎች ኃይማኖታቸው በሚያዘው መሠረት የተዝካር ሥነ-ሥርዓት ለማድረግ መዘጋጀታቸውንም ይናገራሉ።

በዚህ ዘገባ ላይ ተጨማሪ መረጃ