ቁንጅና ተስፋዬ፡ ፋሽንን ከሕንፃ ንድፍ ጋር ያዛመደችው ዲዛይነር

ቁንጅና ተስፋዬ Image copyright Kunjina

ምርጫዋ ባይሆንም የኮንስትራክሽን ቴክኖሎጂና ማኔጅመንት ትምህርትን ተምራ ወደ ልብስ ንድፍ ሙያ አዘነበለች።

ቁንጅና ተስፋዬ "በዩኒቨርሲቲ የነበረኝ ቆይታ በማልፈልገው የትምህርት ዘርፍ ቢሆንም እንዲህ ፍላጎት በሌለኝ ነገር ላይ ጉልበቴንና ጊዜዬን ማፍሰስ መቻሌ የምወደውን ነገር ብሠራ ደግሞ ከዚህ በላይ ውጤታማ መሆን እንደምችል በእራሴ ላይ እምነት የፈጠረብኝ ቆይታ ነበር" ትላለች።

ቁንጅና በ2006 ዓ.ም አዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲን ስትቀላቀል ፋሽን ዲዛይን ትምህርትን የመከታተል ፍላጎቷን ዩኒቨርሲቲው ውስጥ ማሳካት ስላልቻለች የሥዕል ዝንባሌዋን ለመጠቀም ሥነ-ሕንፃ 'አርኪቴክቸር' ወይም የምህንድስና አስተዳደር 'ኮንስትራክሽን ማኔጅመንት' ለማጥናት ወሰነች። በዚህም "የፋሽን ዲዛይን ለመሥራት ጊዜ ስለሚሰጠኝ የኮንስትራክሽን ማኔጅመንትን መረጥኩኝ" ትላለች።

ታዋቂ ኢትዮጵያዊያን አርቲስቶች ለመዋብ ምን ያህል ይከፍላሉ?

"አስተማሪዎቻችን አርክቴክቶች ስለነበሩ የሕንፃ ዲዛይን እንዴት እንደሚሠራ ለማወቅ ዕድሉን ሰጠኝ" የምትለው ቁንጅና ትምህርቱ የመጀመሪያ ምርጫዋ ባይሆንም ትምህርቱ ባካተታቸው የሕንፃ ንድፍ ትምህርቶች የፈጠራና የዲዛይን ችሎታዋን በተለያየ መልኩ ማዳበር እንድትችል ዕድል እንደሰጣት ትናገራለች።

በ2010 ዓ.ም ከአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ ስትመረቅ በተመሳሳይ ዓመት ደግሞ የአፍሪካን ሞዛይክ ፋሽን ዲዛይን ውድድር በፈጠራና ተስፋ የተጣለባት ዲዛይነር በመሆን አርቲ-ቴክቸር (አርትንና አርኪቴክቸርን ያቀላቀለ ስያሜ) በተባለ ስብስቧ አሸንፋለች።

Image copyright Kunjina
አጭር የምስል መግለጫ አርቲ-ቴክቸር (አርትንና አርኪቴክቸርን ያቀላቀለ ስያሜ)

ቁንጅና "2010 ዓ.ም ሁለቱን የተለያዩ ዓለሞቼን ያጣመርኩበት ዓመት ነው" ስትል "አፍሪካ ሞዛይክ ያሸነፍኩበት ዲዛይን 'አርቲ-ቴክቸር' ብዬ የሰየምኩትም በውስጡ ሥነ -ሕንፃን ከሥዕል ጥበብ ጋር አዛምጄ ስለሠራሁት ነው" ትላለች።

አክሱምና ላሊበላ ለስራዎቹ መስፈርት የሆኑት ዲዛይነር

ልብሶቿ ከሕንፃ ዲዛይን የተዋሱትን መልክ ስትገልፅ ቀጥተኛ መስመሮች፣ ማዕዘናዊ ቅርፆችንና የሕንፃ ንድፍ ላይ የሚካተቱ የተለያዩ ምልክቶችን ትጠቅሳለች።

"የአፍሪካ ሞዛይክን ሳሸንፍና ከዩኒቨርሲቲ ስመረቅ ሁለቱንም በአንድ ላይ አጣምሬ መጠቀም እንደምችል የተረዳሁበት፤ እናም ምንም እንኳን አንዱን መርጬ የተማርኩት ባይሆንም በመንገዱ ለተሰጥዖዬ የእራሱን አስተዋፅዖ አድርጎልኝ የሁለት ስኬቶችን ደስታ ማክበር የቻልኩበት ጊዜ ነበር" ትላለች።

ተማሪዎች ዩኒቨርሲቲ ሲገቡ የሚያጠኑት ዘርፍ በፍላጎታቸው ቢሆን ብዙዎች ስኬታማ ሊሆኑ ይችላሉ ብላ የምታመነው ቁንጅና "እኔ የኮንስትራክሽን ማኔጅመንትን ስማር እኔን የሚስቡኝ የዲዛይን ክፍሎች ካልሆኑ በስተቀር ብዙዎቹን ክፍል ውስጥ ቁጭ ብዬ ሌላ ነገር ስስል ነው ያሳለፍኩት" ትላለች።

Image copyright Kunjina

ልብስ ዲዛይን የማድረግ ተሰጥዖዋን በጊዜ ማሳየት የጀመረችው ቁንጅና አጀማመርዋን ስታስታውስ፤ በማህበራዊ ሚዲያም ላይ የሠራቻቸውን ልብሶች ታቀርብ ነበር። "አንዴ ውጪ ያለች አክስቴ የሠራሁትን በፌስቡክ አይታ ወዲያውኑ የመስፊያ ማሽን ላከችልኝ፤ ከዚያም በእራሴ ቤት ውስጥ መለማመድ ጀመርኩ" ትላለች።

የመጀመሪያ ዲዛይኖቿ 12ኛ ክፍል የአካባቢ ጥበቃ ቀን በተመለከተ ከወዳደቁ ነገሮች የሠራችውና የዩኒቨርሲቲ አንደኛ ዓመት ተማሪ በነበረችበት ወቅት የተሳተፈችበት በሴቶች ቀን ላይ ያተኮረ የፋሽን ሾው እንደሆኑ ቁንጅና ታስታውሳለች።

አራተኛ ዓመት ተማሪ ሆና ለልምምድ ስትወጣ ጎን ለጎን የፋሽን ዲዛይን ትምህርትን መከታተል የጀመረችው ቁንጅና ሁለት የተለያዩ ትምህርቶችን እየተማሩ ለማስኬድ መሞከር በጣም ከባድ እንደሆነ ትናገራለች።

የኬንያ ዳኞችን አለባበስ የቀየረች ኢትዮጵያዊት

ሁለቱንም ትምህርቶቼን ውጤታማ በሆነ መልኩ ለማጠናቀቅ "የዩኒቨርስቲ ትምህርት ቦታዬ ጦር ኃይሎች መሃል አዲስ አበባ ሆኖ አፍሪካ ሞዛይክ ዲዛይን ሴንተር ደግሞ ከከተማው ውጪ ለገጣፎ ነበር፤ ብዙ ጊዜ ምሳ ያመልጠኛል ግን ያው ለፈለግሽው ነገር መስዋዕት መክፈል ብዙም አያስቸግርም" ትላለች።

ፓሪስን፣ ኒዮርክን፣ ዱባይን ... ወደ አዲስ አበባ

በአሁኑ ወቅት የመጀመሪያ መደብሯን ከፍታ ሙሉ ለሙሉ የፋሽን ዲዛይን ላይ የምትሠራው ቁንጅና፤ የፋሽን ዓለሙም የእራሱ የሆኑ ፈተናዎች እንዳሉት ትናገራለች።

"የሃገር ውስጥ ጨርቅ እጥረት፥ ከውጭ የሚገባም ጨርቅ በአንድ ዓይነት ጥራት አለማግኘትና የፋሽን ኢንደስትሪው በደንብ አለመደገፍ መሰናክሎች ናቸው" ብትልም በምትወደው ሙያ የበለጠ ስኬታማ ለመሆን ጥረቷን እንደምትቀጥል ትናገራለች።