የሩስያ የጦር አውሮፕላኖች ቬኔዝዌላ ገቡ፤ ጦርነት እንዳይቀሰቀስ ተሰግቷል

የራሺያ አውሮፕላን ካራካስ ደርሷል Image copyright Reuters

ቅዳሜ ሁለት የሩስያ የጦር አውሮፕላኖች ቬኔዝዌላ ዋናው አየር መንገድ ገብተዋል። አውሮፕላኖቹ በርካታ መሣሪያዎችንና ተዋጊዎችን ጭነው ነው ካራካስ የደረሱት።

አውሮፕላኖቹ 'ለአንዳንድ ቴክኒካዊ ድጋፍ' ነው የገቡት ብሏል አንድ የሩስያ ዜና ወኪል።

ማዮርካ የተባለ የቬኔዝዌላ ጋዜጠኛ በትዊተር ሰሌዳው እንደፃፈው ከሆነ ቢያንስ መቶ የሚሆኑ ወታደሮችን በርከት ካሉ የጦር መሣሪያዎች ጋር መመልከቱን ተናግሯል።

ይህ የሆነው ሁለቱ ሃገራት የጋራ ወታደራዊ ንግግር ካደረጉ ከሦስት ወር በኋላ መሆኑ ነው።

ቬንዙዌላ በተቃዋሚ መሪው ላይ የጉዞ እገዳ ጣለች

ሩስያ የቬኔዝዌላ አጋር ከሆነች ሰንበትበት ብሏል። በተይም ለነዳጅ ሃብቷ ማበልፀጊያና ለጦር ሠራዊቷ ማዘመኛ የሚሆኑ በቢሊዮኖች የሚቆጠሩ ብድሮችን ለማዱሮ መንግሥት ሰጥታለች።

ፕሬዚዳንት ኒኮላስ ማዱሮን የሚቃወሙ የምዕራብ መንግሥታትን በመገሰፅም ትልቅ ሚናን ስትጫወት ቆይታለች፣ ሩስያ።

በፀጥታው ምክር ቤት ቬኔዝዌላ ለመቅጣት የሚወጡ ውሳኔዎችን በመቀልበስም አጋርነቷን አስመስክራለች።

ቬኔዝዌላዊው ጋዜጠኛ ማዮርካ እንደሚለው ከሆነ አንቶኖቭ አየር ኃይል-124 ካርጎ ትንንሽ ጀቶችንና የጦር መሣሪያዎችን ይዞ ነው ካራካስ የደረው። ቡድኑን ይዘው የመጡትም የሩስያ ጄኔራል ቫሲሊ ቶንኮሽኩሮቭ ናቸው።

Image copyright Getty Images

ሩስያ ምዕራባዊያን በቬኔዝዌላ ጉዳይ እጃቸውን እንዳያስገቡ እያስጠነቀቀች ቆይታለች።

አሜሪካ በበኩሏ ኒኮላስ ማዱሮን ሥልጣናቸውን እንዲለቁ ግፊት ከማድረግም አልፋ ዲፕሎማሲያዊ ግንኙነቶችንም አቋርጣ ቆይታለች። ለማዱሮ ተቃዋሚ ጓይዶ ሙሉ ድጋፍ በመስጠት ሁሉን አቀፍ ዲፕሎማሲያዊ እርዳታ ስታደርም ነበር።

እጅግ ተወዳጅ እንደነበሩ የሚነገርላቸው ፕሬዝዳንት ሁጎ ቻቬዝ በ2013 ከዚህ ዓለም በሞት ሲለዩ እንዲተኳቸው ያዘጋጇቸው ሰው ኒኮላስ ማዱሮን ነበር።

ዋና የደስታ አስፈፃሚ ሥራ ምንድን ነው?

ማዱሮ ወደ ሥልጣን ከመጡ ወዲህ ግን የቬኔዝዌላ ምጣኔ ሀብት ተንኮታኩቶ ቆይቷል። ሃገሪቷም በዋጋ ግሽበት ቁም ስቅሏን ስታይ ነበር። እጅግ ሰፊ የነዳጅ ሃብት ያላት ቬኔዝዌላ ሕዝቦቿ በችግር ተተብትበው አንዳንዴም የሚላስ የሚቀመስ ያጡበት ሁኔታ ተፈጥሮ ያውቃል።

ባለፉት ሳምንታት እንኳ አብዛኛው የሃገሪቱ ክፍል መብራት በፈረቃ ለማድረግ ተገዶ ነበር።

በርካታ ቬኔዝዌላዊያን ችግሩ ሲጠናባቸው ወደ ጎረቤት ሃገራት መሸሽ ጀምረዋል። እስከዛሬ ከ3 ሚሊዮን የማያንሱት ዜጎች ከሃገር መውጣታቸው ተዘግቧል።

አሁን ሩስያ የጦር አውሮፕላኖችን ወደ ካራካስ መላኳ ምናልባት ኃያላኑ ቬንዝዌላን የጦር አውድማ እንዳያደርጓት ተሰግቷል።

ሩስያ ለመውደቅ ጫፍ ደርሶ የነበረውን የሦሪያ መንግሥትን በመደገፍና በምዕራባዊያን ከሚደገፉ ኃይሎች ጥቃት በመከላከል የአሳድን አስተዳደር ከመንኮታኮት በመታደግ የተሳካ ተግባርን ማከማወኗ አይዘነጋም።