"አደጋውን ስሰማ ክው ነበር ያልኩት..." አቶ ተወልደ ገ/ማርያም

አቶ ተወልደ ገብረማሪያም በአፍሪካ ግዙፉንና ስኬታማው የኢትዮጵያ አየር መንገድን ለዓመታት በዋና ሥራ አስፈጻሚነት ሲመሩ ቆይተዋል። በስኬቱና ከሚያገኛቸው ሽልማቶ ጋር በተያያዘ በተደጋጋሚ በመናኛ ብዙኃን የሚነሳው ድርጅታቸው በቅርቡ ባጋጠመው አደጋ መነጋገሪያ ሆኗል።

ከአደጋው ከሁለት ሳምንት በኋላ እንኳን አጀንዳ እንደሆነ የቀጠለው የኢትዮጵያ አየር መንገድ በረራ ቁጥር 302 አደጋን መጀመሪያ ከሰሙት መካከል የአየር መንገዱ ዋና ሥራ አስፈጻሚ አቶ ተወልደ ወልደማሪያም እስካሁን ድንጋጤው ከውስጣቸው አልወጣም::

ዓለምን ከጫፍ ጫፍ ያስደነገጠው ይህ አደጋ የተለየ እንደሆነ የሚናገሩት አቶ ተወልደ "የአደጋውን መድረስ ዜና የሰማሁት ጧት ነው። በእርግጥም በጣም ክው አድርጎኛል። በጣም፤ እጅግ በጣም ነው ያሳዘንኩት" ሲሉ መጋቢት አንድ ቀን ጠዋት የተፈጠረባቸውን ስሜት ያስታውሳሉ::

በእርግጥ የአብራሪዎቹ ስልጠና ከአደጋው ጋር ይያያዛል?

አቶ ተወልደ አሳዛኙን ዜና እንደሰሙ የድርጅታቸው አውሮፕላን ከ157 ሰዎች ጋር ክፉኛ ወድቆ ወደተከሰከሰበት ቦታ ለመሄድ ጊዜ አላጠፉም። "አውሮፕላኑ የወደቀው የእርሻ ቦታ ላይ ነው፤ በሚያስደነግጥ ሁኔታ የአውሮፕላኑ አካል ሙሉ በሙሉ ከመሬት በታች ገብቷል" የሚሉት አቶ ተወልደ፤ ከውጭ ሲታይ ትንሽ ጭስ የሚመስል ነገር ቆፍሮ በገባበት ቦታ ላይ ይታይ ነበር እንጂ የአውሮፕላኑ ምልክት በቦታው ላይ አልነበረም ይላሉ።

ይህ የሥራ ባልደረቦቻቸውንና የድርጅታቸውን ደንበኞች ሕይወት የቀጠፈ አደጋ የፈጠረው መሪር ሐዘናቸው እስካሁንም እንዳለ ነው።

"የምናውቃቸው የሥራ ባልደረቦቻችንን አጥተናል። በጣም ነው ያዘንነው። በሐዘንም ነው የሰነበትነው። እነሱንም በጀግና ሽኝት ነው የሸኘናቸው። ምክንያቱም የኢትዮጵያ አየር መንገድን ሥራ እየሠሩ ነው የሞቱት። ጀግኖች ናቸው። ሐዘናችን አሁንም እንዳለ ነው" ይላሉ።

አደጋው በአየር መንገዱ ላይ ምን አስከተለ?

አደጋው ወትሮውኑም ውስብስብና ከባድ የሆነውን የአየር መንገዱን ሥራ በእጥፍ እና ከዚያም በላይ እንደጨመረው ነው የሚናገሩት ሥራ አስፈጻሚው። ምክንያቱም ሐዘን ውስጥ ያለው የድርጅቱ አመራርና ሠራተኛ ፋታ ከማይሰጠው የዕለት ከዕለት ሥራ በተጨማሪ በሐዘን ውስጥ ሆነው ሐዘኑን እያስተናገዱ በአደጋው የተጎዱ ቤተሰቦችን በመርዳትና በማጽናናት ላይ ናቸው።

"በሌላ በኩል ደግሞ የአደጋው ምርመራ አለ። ለምርመራው አስፈላጊውን ትብብር ማድረግ አለብን። በተጨማሪም ሥራ ሳይስተጓጎል፣ ደንበኞች የሚጠብቁትን መስተንግዶ እንዲያገኙ፣ አውሮፕላኖች በተያዘላቸው የጊዜ ሰሌዳ እንዲበሩ ማድረግ ራሱም ትልቅ ሥራ ነው" ይላሉ አቶ ተወልደ።

በደረሰው ከባድ አደጋ ሠራተኛው ውስጥ መደናገጥ እንዳይፈጠር ማረጋጋት፣ ማነጋገርና በቅርብ ሆኖ መደገፍ ሌላው ሥራቸው ነው። ይህንንም ከባልደረቦቻቸው ጋር ሆነው በደንብ እየተወጡት እንደሆነ ያምናሉ። ለዚህ ደግሞ ምስክሩ "በረራዎች ምንም ዓይነት መስተጓጎል ሳይደርስባቸው፤ በአደጋው ዕለት ራሱ ከሦስት መቶ በላይ በረራዎች አካሂደናል።"

ከአደጋው በኋላ ያለው ጊዜ የአየር መንገዱ ሠራተኞችና አመራሮች የተፈተኑበት ጊዜ እንደሆነ የሚናገሩት አቶ ተወልደ "ድርጅቱ ባለው ጠንካራ የሥራ ባህል ፈተናውን በድል የተወጣንበት ጊዜ ነው" በማለት ይናገራሉ።

'መጥፎ ዕድል' አውሮፕላኑ የወደቀበት ስፍራ ስያሜ እንደሆነ ያውቃሉ?

የአደጋው ተጽዕኖ የት ድረስ ነው?

ይህ በኢትዮጵያ አየር መንገድ አውሮፕላን ላይ የደረሰው አደጋ ተጽእኖው ቀላል እንዳልሆነ ከአደጋው በኋላ በዓለም ዙሪያ የተወሰዱ እርምጃዎች ያመለክታሉ። በዚህም አደጋው በበረራው ዘርፍ ላይ የጎላ ተጽእኖን ሊያሳድር ችሏል።

አደጋው በዓለም የአየር ትራንስፖርት ኢንዱስትሪ ውስጥ ለየት ያለ እንደሆነ የሚናገሩት ዋና ሥራ አስፈጻሚው፤ ምርመራውም እንዲሁ ለየት ያለ ነው። ቦይንግ 737 ማክስ አውሮፕላን አዲስ አውሮፕላን መሆኑን እና የኢትዮጵያ አየር መንገድም አደጋ ያጋጠመውን አውሮፕላን ከተቀበለ ገና አራት ወሩ መሆኑን በምክንያትነት ያስቀምጣሉ።

በተመሳሳይ የኢንዶኔዢያውን ላየን ኤር አውሮፕላንም እንዲሁ አዲስ አውሮፕላን ነበር። አምስት ወር ባልሞላ ጊዜ ነው አደጋው ያጋጠመው።ስለዚህም አደጋዎቹ ብዙ የሚያመሳስሏቸው ነገሮች አሉ።

"ዓለም ደግሞ ይሄን በማየት፤ እኛ እሑድ ጧት አውሮፕላኖቹን ለማቆም ስንወስን እሑድ ማታ ደግሞ ቻይና ይሄንን ተከትላ አውሮፕላኖቹ እንዲቆሙ አድርጋለች።"

አንድ መቶ የሚጠጉ ተመሳሳይ አውሮፕላን ያላት የግዙፍ ኢኮኖሚ ባለቤት የሆነችው ቻይና እዚህ ውሳኔ ላይ ስትደርስ ችግሩ ቀላል እንዳልሆነ አመላካች ነው።

"ዘጠና ሰባት አውሮፕላኖች እንዲቆሙ መወሰን ቀላል አልነበረም። ግን የአደጋዎቹን መመሳሰል ስላዩ ነው ይሄ አውሮፕላን ችግር አለው ብለው ውሳኔ ላይ የደረሱት። ሌሎች አገሮችም ይህን ተከትለው ወስነዋል" ይላሉ።

ይህ ክስተት በአየር ትራንስፖርት ዘርፉ ውስጥ ከባድ ውጤት ከነበራቸው ሁኔታዎች አንጻር ጉልህ ተጽዕኖ እንዳለው የሚናገሩት አቶ ተወልደ፤ ስለአደጋው ምርመራ እየተካሄደ ያለው በዓለም ዙሪያ ወደ 380 የሚሆኑ ቦይንግ 737 አውሮፕላኖች ከበረራ ውጪ እንዲሆኑ ተደርገው መሆኑን ይገልጻሉ።

"ይህም በአየር መንገዱ ታሪክ ብቻ ሳይሆን በአቪዬሽን ታሪክ በአጠቃላይ አውሮፕላን ቆሞ ምርመራ እየተደረገበት ያለው ከኮንኮርድ ቀጥሎ ይሄ አውሮፕላን ብቻ ነው። ይህም በጣም አስቸጋሪ ምርመራ ነው የሚሆነው። ይሄንን ያልኩበት ምክንያት ደግሞ አውሮፕላኑ ላይ ብዙ ጥያቄዎች ስላሉ ነው። መልስ ለማግኘት ደግሞ በትዕግስት መጠበቅ አለብን።"

አወዛጋቢው ዘገባና የምስለ በረራ ስልጠና ከአደጋው ጋር በተያያዘ ለአብራሪዎች የሚሰጠው የምስለ በረራ ልምምድ ጉዳይ የአየር መንገዱን ስም እንዲነሳ እያደረገው ነው። አቶ ተወልደ ግን ከዚህ አኳያ የሚነሱት ነገሮች "መሠረት የሌላቸው ሃሰትን የተንተራሱ ናቸው" ይላሉ።

ስልጠናን በተመለከተ የኢትዮጵያ አየር መንገድን አብራሪዎች በዓለም ዙርያ ተመራጭ እና ተደናቂ የሚያደርጋቸው፤ ለየት ባለ ሁኔታ በጣም ረጅም ጊዜ ተወስዶ በርከት ያለ ስልጠና ስለሚሰጣቸው ነው። ስልጠናና ልምምዱ ከሌላው ዓለም የበለጠ እንጂ ያነሰ እንዳልሆነ የሚናገሩት አቶ ተወልደ "ይሄን ዘገባ ያወጡት ሰዎች እና ድርጅቶች ሌላ ዓላማ ሊኖራቸው ይችላል" በማለት ግምታቸውን ያስቀምጣሉ።

አክለውም የአየር መንገዳቸውን አሠራር ከሌሎች ጋር እያነጻጸሩ ሲያስረዱ፤ "በሌሎች የዓለማችን የአየር መንገዶች አንድ አብራሪ ረዳት አብራሪ ሆኖ በዚያው አውሮፕላን ላይ የተወሰነ ሰዓት ከበረረ ሙሉ ዋና አብራሪ መሆን ይችላል። የኢትዮጵያ አየር መንገድ ግን ይሄንን አይፈቅድም።"

የኢትዮጵያ አየር መንገድ ምንም እንኳን የስልጠና ወጪውን የሚያንርበት ቢሆንም አዲስ አብራሪዎች ሁለት ዓመት ከአብራሪዎች ማሰልጠኛ ትምህርት ቤት ተምረው ከወጡ በኋላ በተለያዩ አውሮፕላኖች ላይ በረዳት አብራሪነት የሚጠበቅባቸውን ሰዓት ሲያሟሉ አሁም ረዳት አብራሪ ሆነው ወደ 787 ወይም 777 እንደሚያድጉ ይናገራሉ። በቂ ሰዓት እዚያ ላይ ካገኙ በኋላም ሙሉ አብራሪ ለመሆን እንደገና ተመልሰው ወደ ትንሿ አውሮፕላን ይሄዳሉ።

የገጠር አስተማሪው አንድ ሚሊዮን ዶላር አሸነፉ

አቶ ተወልደ ድርጅታቸውን ከሌሎች አየር መንገዶች ጋር ሲያነጻጽሩ "ለምሳሌ የአውሮፓ ወይንም የአሜሪካ አየር መንገዶችን ብንወስድ በ737 ረዳት አብራሪ የሆነ ሰው እዚያው የተወሰነ ሰዓት ከበረረ በኋላ ዋና አብራሪ ይሆናል። እኛ ይሄንን ስለማንፈቅድ አብራሪዎቻችን በሥራ ክንውናቸው ዓለም ያደነቃቸው ናቸው። የትም አገር ሄደው ሲሠሩ ከማንም በላይ የሚመረጡ እና የሚደነቁ አብራሪዎች እንዲሆኑ አድርጓቸዋል።"

የምስለ በረራ (ሲሙሌተር) ልምምድን በሚመለከት የወጣውን ዘገባ አንስተውም "በአቪየሽን ላይ ምንም ዕውቀት የሌለው ሰው ያወጣው ዘገባ ነው" ይላሉ። ሲያብራሩም "መጀመሪያ በዓለም ላይ ስንት የ737 ማክስ ምስለ በረራዎች እንዳሉና ምን ያህል አብራሪዎች እንደሰለጠኑ መጠየቅ ያስፈልጋል።"

ምስለ በረራው በቅርቡ የመጣ እንደሆነ የሚናገሩት አቶ ተወልደ፤ የኢትዮጵያ አየር መንገድ ከአፍሪካ የመጀመሪያ ሆኖ እንዳመጣው ይጠቅሳሉ።

"ነገር ግን አንድ አብራሪ በ737 ማክስ እና በ737 ኤንጂ ምስለ በረራ ከሰለጠነ ልዩነት አያመጣም። ስለዚህ ሁለቱ አብራሪዎችም ሆነ ሌሎቹም አብራሪዎች በ737 ኤንጂ ስልጠና ወስደዋል" ይላሉ።

ለዚህም ምክንያቱን ሲያስቀምጡ "የ737 ማክስ ምስለ በረራን አሁን ነው ያገኘነው፤ በተጨማሪም ከ737 ኤንጂ ጋር ልዩነት የለውም" በማለት በቅርቡ አየር መንገዱ ያስመጣው የ737 ማክስ ሲሙሌተር እንኳን "አሁን አውሮፕላኖቹ ከገጠማቸው ችግር አንጻር ከበረራ ውጪ እንዲሆኑ ያደረገውን ችግር አስመስሎ ሊያሳይ (ሲሙሌት ሊያደርግ) አይችልም" ሲሉ ጉዳዩ ከምስለ በረራ ስልጠና ጋር እንደማይገናኝ አቶ ተወልደ ገብረ ማሪያም ገልጸዋል።