ጌዲዮ በዐቢይ ጉብኝት ማግስት

እቴነሽ አበበ ልጇን የተገላገለችው መንገድ ላይ በሽሽት ላይ ሳለች ነበር
አጭር የምስል መግለጫ እቴነሽ አበበ ልጇን የተገላገለችው መንገድ ላይ በሽሽት ላይ ሳለች ነበር

ባለፈው ሳምንት ጠቅላይ ሚኒስትሩ ያደረጉትን የጌዲዮ ጉብኝትን ትከትሎ ተፈናቃዮች በመንግሥት ላይ ተስፋቸው ከፍ ያለ ይመስላል። የቢቢሲ ዘጋቢዎች በስፍራው ተገኝተው ያዩትን፣ የችግሩን ስፋትና አሳሳቢነት እንዲህ ይተርካሉ።

የዓይናለም ከፍያለው ምጥ

በሃያዎቹ መጀመሪያ የምትገኘው ዓይናለም ከፍያለው አራተኛ ልጇን የተገላገለችው በጌዲዮ ዞን፥ ገደብ ወረዳ ጎቲቲ ቀበሌ ከሚገኙ ስድስት የተፈናቃይ መጠለያዎች በአንደኛው ውስጥ ነው።

ተያይዘው ከተደረደሩ ጠባብ የድንኳን መጠለያዎች በአንደኛው ውስጥ፥ የረባ ምንጣፍ እንኳ ባልለበሰ አቧራማ መሬት ላይ የሦስት ቀን ዕድሜ ያለው ጨቅላ ልጇን አቅፋ ተቀምጣለች።

"ምጥ ሲይዘኝ አጠገቤ ማንም አልነበረም፤ እዚሁ መሬት ላይ ነው የወለድኩት" ትላለች ድካም በበረታበት ድምፅ።

በወርሃ ታኅሣሥ መጀመሪያ ትኖርበት የነበረውን የምዕራብ ጉጂ ዞን የኋሊት ጥላ፥ ይደርስብኛል ብላ የሰጋችውን ጥቃት ሽሽት ወደጌዲዮ ዞን ስታቀና ጉዞ የዋዛ እንዳልነበር ለቢቢሲ ታስታውሳለች።

"ብዙ ሩጫ ነበር። እኔ ደግሞ እርጉዝ ነበርኩ። እና ስወድቅ ስነሳ ነው እዚህ የደረስኩት። ስወድቅ ጉዳት ደርሶብኛል። አሁን ብታዩት ሦስት አራት ቦታ ታስሯል ወገቤ። ሩጫ ላይ ስለወደቅኩ።" በቀድሞ መኖሪያዋ በቡና እና እንሰት እርሻ ትተዳደር እንደነበር ለቢቢሲ ዘጋቢ የገለፀችው ዓይናለም፥ "እዚያ እያለን፥ ቆጮ በጎመን፥ ቆጮ በሥጋ እየበላን ጠግበን ነበር የምናድረው።

ምንም የምግብ ችግር አልነበረም። ኑሯችን ጥሩ ነበር። እዚህ ከመጣን በኋላ ግን ኑሮው ምንም ሊመሳሰል አልቻለም። ሌት ተቀን እየራበን ሲመጣ የምግብ ፍላጎቱም እየቀነሰ መጣ" ስትል ትናገራለች።

ከወሊድ በኋላ ምግብ ለመመገብ የተቸገረች በመሆኑ ጨቅላ ልጇንም ጡት ማጥባት አልቻለችም።

"በመጥፎ የጤና ሁኔታ ውስጥ ነው ያለሁት። ያገኘሁት ምንም ዓይነት ሕክምና የለም" ትላለች::

ዓይናለም በጎቲቲ ቀበሌ ከሠፈሩ በዐሥር ሺህዎች የሚቆጠሩ ተፈናቃዮች መካከል አንደኛዋ ናት።

ተፈናቃዮቹ በአብያተ ክርስትያናት ውስጥ እና በአካባቢው በሚገኙ አንድ አንድ ቦታዎች ላይ በድንኳን፣ ሌሎች ቦታዎች ላይ ደግሞ በጭራሮ እና ቅጠላ ቅጠሎች እንደነገሩ በተሸፋፈኑ ጠባብ ማደሪያዎች ውለው ያድራሉ።

ለወራት ያህል ማንም ዞር ብሎ አላየንም ሲሉ በምሬት የሚናገሩት ተፈናቃዮቹ ባለፉት ሁለት ሳምንታት ለውጥ መኖሩን ይመሰክራሉ።

የተለያዩ የዜና ዘገባዎች እና የማኅበራዊ ሚዲያ ዘገባዎች የችግሩን ጥልቀት ካመላከቱ በኋላ በግለሰብም ይሁን በተቋም ደረጃ እርዳታ የማሰባሰብ እንዲሁም ወደ ስፍራው የማድረስ ጥረቶች ተጠናክረው ተስተውለዋል።

ምግብ እና አልባሳትን ይዘው ወደመጠለያዎቹ የሚያቀኑ አካላትም ከወራት በፊት ከነበረው ተሽሎ ታይቷል።

ይሁንና የሚቀርበው እርዳታ፥ ለተረጂዎቹ ከሚያስፈልገው ጋር ሊመጣጠን ቀርቶ ሊቀራረብ እንኳ እንዳልቻለ የቢቢሲ ዘጋቢዎች በስፍራው ያነጋገሯቸው በጎ ፈቃደኞች እና የምግባረ ሰናይ ድርጅት ሠራተኞች ይገልፃሉ።

በመጠለያ ጣብያዎቹ ከምግብ እጥረት እና ከንፅህና ጉድለት ጋር በተገናኘ የተለያዩ በሽታዎች መስፋፋታቸው ከእስካሁኑም የከፋ መዘዝ እንዳያመጣ ስጋታቸውን የገለፁልን ባለሞያዎችም አሉ።

የእቴነሽ አበበ ስቃይ

የሠላሳ ሁለት ዓመቷ እቴነሽ አበበ ስምንት ልጆች አሏት።

ያቀፈችውን የመጨረሻ ልጇን የወለደችው ከሁለት ወራት በፊት ከምዕራብ ጉጂ ዞን በምትሸሽበት ወቅት መንገድ ላይ ነው።

"ስወልድ ከፍተኛ ችግር ነበር። አንደኛ ከኋላ እያባረሩን ነው። ከፍተኛ ደም እየፈሰሰኝ ነበር። ባሌ አብሮኝ ነበር። ሁለት ጉርድ ልብስ ነበር፤ በእርሱ እያሰርን፥ እያስታገስን ነው ወደዚህ የመጣነው" ትላለች ሁኔታውን ስታስታውስ።

በጎቲቲ ቀበሌ ግንባታ ላይ ባለው ቃለእየሱስ ቤተክርስትያን ውስጥ በሚገኘው ጊዜያዊ የመጠለያ ጣብያ ከገባች በኋላ ተገቢውን የጤና እንክብካቤ ማግኘት ቀርቶ የሚላስ የሚቀመስ እንኳ ብርቅ ሆኖባታል።

እንዲያም ቢሆን "ከሁሉም ነገር ሕይወት ስለምትበልጥ እስካሁን ሕይወቴ አለች" ስትል ለቢቢሲ ተናግራለች።

ለትምህርት የደረሱት ልጆቿ ከመደበኛ ትምህርት ተለያይተዋል፤ በዕድሜ ከፍ ያሉት አምስቱ በተለያዩ ቤቶች ውስጥ ሥራ በመቀጠራቸው ርቀዋታል።

ሦስቱ ግን አብረዋት በመጠለያ ጣብያው ውስጥ አሉ።

ታዲያ ከምንም በላይ የሚያሳስባት የሁለት ወር ጨቅላ ልጇ የጤና እክል ነው፤ "ያስመልሳታል፥ ትኩሳት አላት፥ ያስቀምጣታል።"

ካለፈው ሰኞ መጋቢት ዘጠኝ አንስቶ አነስተኛ የሕክምና ባለሞያዎች ቡድን በመጠለያ ጣብያው ውስጥ የሕክምና አገልግሎት መስጠት ጀምሯል።

"በአጭር ጊዜ ውስጥ ማከም የምንችለውን በሽታ ለማከም ነው የመጣነው" ይላሉ ቡድኑን የሚያስተባብሩት እና በቋሚነት በዲላ ዩኒቨርስቲ ሪፈራል ሆስፒታል የሚሠሩት ዶክተር መላኩ ጌታሁን።

የቆዳ ላይ እከክ (ስኬቢስ) እና ከፍተኛ የምግብ እጥረት በተለይ እስከ አምስት ዓመት ባሉ ሕፃናት ላይ የሚስተዋሉ የጤና እክሎች ሲሆኑ፤ ሁሉም ሕፃናት ሊባል በሚችል ደረጃ የዓይን በሽታ (ኮንጃክቲቫይተስ) ተጠቂዎች መሆናቸውን ዶክተር መላኩ ያስረዳሉ።

እርሳቸው በነበሩበት የአንድ ሳምንት ጊዜ ውስጥ አንድ ሕፃን ከምግብ እጥረት ጋር በሚያያዙ የጤና ችግሮች ምክንያት ሕይወቱ ማለፉንም ጨምረው ለቢቢሲ ተናግረዋል።

አደጋው ስፍራ በየቀኑ እየሄዱ የሚያለቅሱት እናት ማን ናቸው?

የዓለሙ ዋቆ ተስፋ

በመጠለያ ጣብያዎቹ ውስጥ በርካታ ነብሰ ጡሮች በመኖራቸው፥ የተቻለውን ያህል አይረን እና ፎሊክ አሲድ ለማቅረብ እየሞከሩ፥ የቲቢ በሽተኞችንም ለመለየት ሥራ መጀመራቸውን የሚናገሩት ሐኪሙ፤ የችግሩ መጠን እና የቡድኑ

አቅም ያለመመጣጠን፥ ከቡድኑ ጊዚያዊነት ጋር ተደማምሮ ለከፋ የጤና ችግር መፈልፈል ምክንያት እንዳይሆን ስጋት አላቸው።

በመጠለያ ጣብያው ውስጥ ወራትን ያሳለፉት ተፈናቃዮች በበሽታ የሞቱ ሰዎች ቁጥር ጥቂት የማይባል እንደሆነ ይናገራሉ።

በጎ አድራጊዎች የድጋፍ እጃቸውን ባይዘረጉለት ኖሮ የሁለት ዓመት ተኩል ልጁን በሞት ይነጠቅ እንደነበር የሚናገረው ዓለሙ ዋቆ ነው።

የአርባ አምስት ዓመቱ ዓለሙ በሽሽት መሀል ከሚስቱ ጋር ከተጠፋፋ በኋላ ሕይወቷ ማለፉን ሰምቷል።

"የፀጥታ ችግር ሲነሳ ሁላችንም ሕይወታችንን ለማትረፍ እየሮጥን ነበር። እርሷም በዚያውም መልክ ሸሽታ ነበር። ምሥራቅ ጉጂ ውስጥ ነው የሞተችው። በምን እንደሞተች፥ ማን እንደገደላት ግን አላውቅም።"

ስምንት ልጆቹን ይዞ በጎቲቲ ጊዜያዊ መጠለያ ጣብያ በሚኖርበት ጊዜ ነው የመጨረሻ ልጁ የሰናይት ጤና ይታወክ የያዘው።

የክልል እንሁን ጥያቄ እዚህም እዚያም?

አምስት ነጥቦች ስለጌዲዮ ተፈናቃዮች

"ያስመልሳታል፥ ቆዳዋን ያሳክካታል፥ ያስቀምጣታል" ይላል በይርጋ ጨፌ ከተማ ላገኛቸው የቢቢሲ ዘጋቢዎች።

አካሏ ክፉኛ ተጎሳቁሎ፥ ሰውነቷ ተመናምኖ እጅጉን መጠውለጓን ያዩ በይርጋ ጨፌ ከተማ አንድ ክሊንክ ያላቸው የሕክምና ባለሞያ ልጁን ይዞ እንዲመጣ ካደረጉ እና የጤና ክብካቤ በነፃ ማቅረብ በጀመሩበት ጊዜ ሰናይት ከሞት አፋፍ ላይ እንደነበረች ይገልፃል።

በጎቲቲ ካሉ የመጠለያ ጣብያዎች በአንደኛው የምትገኛው ሌላኛው ሴት ልጁ በላይነሽ በተመሳሳይ የጤና ችግር ክፉኛ መያዟን ዓለሙ ይናገራል።

ቀድሞ የሚኖርበትን ስፍራ ለቅቆ ከሸሸ በኋላ መተዳደሪያውን ግብርናን መተውን የሚያስረዳው ዓለሙ "በድጋፍ የምናገኘውን እንበላለን እንጅ ከዚህ ሌላ ምንም ገቢ የለንም" ይላል።

"መንግሥት የሚያደርገውን ነገር ተስፋ አድርጌ እየጠበኩኝ ነው። ሌላ ምንም ተስፋ የለኝም።"

ተያያዥ ርዕሶች