ቻይና 300 የኤርባስ አውሮፕላኖችን ልትገዛ ነው

ዢ ፒንግና ኢማኑኤል ማክሮን Image copyright Getty Images

ቻይና ኤርባስ ከተሰኘው አውሮፕላን አምራች ኩባንያ 300 አውሮፕላኖችን ለመግዛት ውል ፈፀመች። ግዥው 30 ቢሊዮን ዩሮ የሚገመት ነው።

የግዥው ውል የተፈፀመው የቻይናው ፕሬዝዳንት ዢ ጂፒንግ ፓሪስን በጎበኙበት ወቅት ሲሆን ግዥው ባለፈው ሳምንት ፕሬዚዳንቱ አውሮፓን በጎበኙበት ወቅት ያደረጓቸው ስምምነቶች አካል ነው።

ኤርባስ ይህን የመሰለ የሽያጭ ውል ያደረገው ሁለቱን ከባድ አደጋዎች ተከትሎ ተፎካካሪው ቦይንግ 737-8 ማክስ አውሮፕላኖቹን ከአገልግሎት ውጭ ባደረገ ማግስት ነው።

ለ60 ዓመታት የዘለቀው የኢትዮጵያ አየር መንገድና የቦይንግ ግንኙነት

ብዙ አገራት 737-8 ማክስ አውሮፕላኖቹ በአየር ክልላቸው እንዳይበር ላገዱበትና አጣብቂኝ ውስጥ ለገባው ቦይንግ ይህ የኤርባስ የግዥ ውል ዱብ እዳ እንደሚሆን እየተገለፀ ነው።

የቻይና አቪዬሽን አቅርቦት ከኤርባስ ከሚገዛቸው ውስጥ 290 እና A320 አውሮፕላኖች እንዲሁም ዐሥር A350 XWB ጀቶች እንደሚገኙበት ታውቋል።

የኤርባስ የንግድ አውሮፕላኖች ሽያጭ ዘርፍ ፕሬዝዳንት ጉይላም ፋውሪ ግዥውን በማስመልከት "ዘመናዊ በሆኑ አውሮፕላኖቻችን የቻይና ሲቪል አቪዬሽንን እድገት መደገፍ በመቻላችን ክብር ይሰማናል" ብለዋል።

ይህ ከቻይና ጋር የፈፀሙት የግዥ ውል በቻይና ገበያ ላይ ያላቸውን መተማመን እንዲሁም እንደ ቻይና ላሉ አጋሮች ያላቸውን የአገልጋይነት ፅናት ደረጃ የሚያሳይ እንደሆነም ገልፀዋል።

ቦይንግ 737-8 ማክስ አውሮፕላኖቹ በሙሉ እስከ ግንቦት እግድ ተጣለባቸው

ተያያዥ ርዕሶች