ከአፍሪካዊያን አንድ ሦስተኛው መሰደድን ይሻል

ገበያ በኢትዮጵያ Image copyright Anadolu Agency

የአፍሪካ ሕዝብ ቁጥር እያሻቀበ ነው። እንደ አውሮውያዊያኑ በ2050 ምድር ላይ ከአራት ሰዎች አንዱ አፍሪካዊ ይሆናል። ምክንያቱም የአፍሪካ የሕዝብ ቁጥር ያኔ አሁን ካለው እጥፍ ስለሚሆን።

ምንም እንኳ የአፍሪካ አገራት በእድገት ጎዳና ላይ ናቸው ቢባልም ይህን ሁሉ ወፈ ሰማይ ሕዝባቸውን እንዴት ይመግባሉ የሚለው ለብዙዎች ጥያቄ ነው።

እርግጥ ነው ብዙ አፍሪካዊያን አሁንም ወደ ምዕራቡ የማትራሉ። ኾኖም ብዙዎቹ እንደሚያስቡት ዓለምን በስደት የሚያስጨንቋት አፍሪካዊያን አይደሉም። እንዲያውም ከ258 ሚሊዮን የዓለም ስደተኞች 14 በመቶ ብቻ ናቸው አፍሪካዊያን።

አፍሮባሮሜትር አፍሪካ ተኮር የጥናትና ምርምር ተቋም ነው። ከሰሞኑ ምን ያህል አፍሪካዊያን ልባቸው ለስደት ተነሳስቷል በሚል አንድ ጥናት አካሄዶ ነበር።

ከሦስት አፍሪካዊያኑ አንዱ ወደ ጎረቤት አገር ወይም ወደ አውሮፓ ወይም አሜሪካ መሰደድ እንደሚፈልግ ይህ ጥናት አመላክቷል። የአፍሮባሮሜትር የጥናት ቡድን ጥናቱን ያደረገው በ34 አገራት የሚኖሩ የአህጉሪቱ ሕዝቦች ላይ ነበር። በጥናቱ አንዳንድ አስገራሚ ውጤቶች ተገኝተውበታል።

ከአህጉሪቱ ሕዝቦች አንድ ሦስተኛው መሰደድ የሚፈልግ ሲሆን ከዚህ ይበልጥ አስደናቂ የሆነው ግን ወጣትና የተማሩ የሚባሉት ከሌሎች የኅብረተሰብ ክፍሎች በይበልጥ መሰደድን ይመርጣሉ።

እንደ ጥናቱ ውጤት ከሆነ "የተሻለ ሥራ ፍለጋ ነው የምሰደደው" ያለው ሕዝብ ከጠቅላላው የመጠይቁ ተሳታፊ 44 በመቶ ሲሆን "የነጣ ድህነትን ለማምለጥ" ስል ነው ስደትን የምፈልገው ያለው ግን 29 ከመቶ ነው።

Image copyright Alexander Koerner

ጥናቱ ደረስኩበት እንዳለው ከሆነ የቤተሰብ አባል ወይም ወዳጅ ዘመድ በስደት ላይ ያላቸው አፍሪካዊያን የመሰደድ ፍላጎታቸው ውጭ አገር ዘመድ አዝማድ ከሌላቸው በእጅጉ ልቆ ተገኝቷል።

በዚህ የጥናት ውጤት መሠረት ከአምስት አፍሪካዊያን አንዱ በአንድም ሆነ በሌላ መልኩ ውጭ አገር ከሚኖር ሰው የገንዘብ ድጎማን ያገኛል።

ዕድሜዬ 108 ነው የሚሉትን ኮሎኔል እንዴት እንመናቸው?

የት መሰደድ ነው የሚፈልጉት?

የሚደንቀው በቁጥር ከፍ ያሉት የጥናቱ ተሳታፊዎች ለመሰደድ የሚፈልጉት ብዙዎች እንደሚገምቱት ወደ ምዕራቡ ሳይሆን ወደ ሌላ አንድ የአፍሪካ አገር ነው። ይህ ምናልባትም ወደ አውሮፓና አሜሪካ ለመሄድ ሁኔታዎች አልጋ በአልጋ አለመሆናቸውን ከመረዳት የመጣ ሊሆን ይችላል፤ ጥናቱ በምክንያትነት ያነሳው ነገር ባይኖርም።

ከተጠኚዎች ውስጥ 29 ከመቶ የሚሆኑት ወደ ጎረቤት አገራት መሰደድ እንደሚፈልጉ፣ 7 ከመቶ የሚሆኑት ደግሞ ራቅ ብሎም ቢሆን በአፍሪካ አገራት መቆየት እንደሚሹ ተናግረዋል።

የዓለምፀሐይ፣ የፍስሃ እና የካሳሁን አዲስ ተስፋ

በተለይም ደቡብ አፍሪካ አካባቢ ያሉ አገራት ስደተኞች በዚያው በደቡብ አፍሪካ ክፍለ አህጉር ወደሚገኙ አገራት መሰደድን ይሻሉ። ነገር ግን ወደ ሰሜን አፍሪካ ከፍ እያልን ስንሄድ ይህ በክፍለ አህጉሩ ታጥሮ የመሰደድ ነገር እየቀነሰ ይሄዳል።

ከተጠኚዎች መሀል ወደ አውሮፓ መሰድድ ነው የምንፈልገው የሚሉት 27 ከመቶ ብቻ ሲሆኑ 22 በመቶ የጥናቱ ተሳታፊዎች ወደ ሰሜን አሜሪካ መንጎድን ይሻሉ። ከጠቅላላው የመጠይቁ መላሾች ብዙዎቹ ከአውሮፓና ከአሜሪካ ይልቅ ወደ አፍሪካ አገራት መሰደድን መምረጣቸው ያልተጠበቀ ሆኗል።

ኾኖም ጥናቱ እንደሚለው ከአፍሪካ ውጭ እጅግ ተወዳጁ መዳረሻ አውሮፓና ሰሜን አሜሪካ ነው።

የትኞቹ የኅብረተሰብ ክፍሎች ናቸው መሰደድ የሚሹት?

ጥናቱ እንዳስነበበው ከሆነ ትምህርት ቀመስ የሆኑ ዜጎች ካልተማሩት የበለጠ ወደ ሌሎች አገሮች መሰደድን ይሻሉ።

የኢትዮጵያዊያንና የኤርትራዊያን ሰቆቃ በየመን

እንዲሁም በከተሞች የሚኖሩ ዜጎች ገጠር ከሚኖሩት በላይ ወደ ሌሎች አገሮች ለመሰደድ ፍላጎት አላቸው። በጾታ ረገድ ደግሞ ወንዶች ከሴቶች የበለጠ ልባቸው ለስደት የተነሳሳ ነው።

Image copyright MAHMUD TURKIA

የትኞቹ አገር ዜጎች ስደትን በይበልጥ ይናፍቃሉ?

ጥናቱ እንዳስረዳው ከሦስት አፍሪካዊያን አንዱ ወይም 37 ከመቶ የሚሆኑ የአህጉሪቱ ዜጋ ስለመሰደድ አብዝተው ያስባል።

በጥናቱ ከተካተቱ አገሮች የዚምባብዌና የሌሴቶ ዜጎች በዋናነት ስደትን ናፋቂዎች ናቸው። የኬፕ ቨርዴ፣ የሴራሊዮን፣ የጋምቢያና የቶጎ ዜጎች ደግሞ እንደ ዚምባብዌ ባይሆንም ስደትን በ"ብርቱ የሚሹ" እንደሆኑ ጥናቱ ያስረዳል።

ይህ ጥናት እጅግ ብዙ ሕዝባቸውን ለስደት የዳረጉትን ደቡብ ሱዳንና ኤርትራን አላካተትም። ደቡብ ሱዳን በጦርነት ምክንያት 2.2 ሚሊዮን ዜጎቿ ወደ ጎረቤት አገራት ተሰደዋል።

የትኞቹ ሃገራት ከፍተኛ ስደተኛ አላቸው?

በስደት የሚገኙ የኤርትራ ዜጎችም ቁጥራቸው ቀላል የሚባል አይደለም። የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት በወር ቢያንስ 2ሺ 500 ኤርትራዊያን ወደ ኢትዮጵያ ያቀናሉ ይላል።

በዚህ የአፍሮባሮሜትር ጥናት ኢትዮጵያ አልተካተተችም። ከኢትዮጵያዊያን ምን ያህሉ መሰደድን ይሹ ይሆን?

ተያያዥ ርዕሶች

በዚህ ዘገባ ላይ ተጨማሪ መረጃ